አሜሪካ ግብፅ እና ሶማሊያን ጨምሮ ከ30 አገራት ከፍተኛ ዲፕሎማቶቿ ወደ ዋሺንግተን እንዲመለሱ አዘዘች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የትራምፕ አስተዳደር ያለ ምንም ማብራሪያ በተለያዩ የዓለም አገራት ውስጥ የሚገኙ ወደ 30 የሚጠጉ አምባሳደሮችን እና ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ሥራቸውን አቁመው ወደ አሜሪካ እንዲመለሱ አዘዘ።
"ቅድሚያ ለአሜሪካ" ከሚለው የዶናልድ ትራምፕ መርህ ጋር በተያያዘ በአገሪቱ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ውስጥ የፕሬዝዳንቱ አስተዳደር ለውጥ ማድረግ በፈለገባቸው እና ከፍተኛ ሚና የላቸውም ከተባሉ አገራት ዲፕሎማቶቹ እንዲወጡ ተደርጓል።
ለአሜሪካ መንግሥት ውሳኔ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ወደ 30 የሚጠጉት ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ያለምንም ማብራሪያ የተመደቡባቸውን አገራት ለቅቀው ወደ ዋሺንግተን እንዲመለሱ በስልክ ተነግሯቸዋል።
ይህ የማሰናበት የሚመስለው መልዕክት ለአምባሳደሮቹ መድረስ የጀመረው ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ መሆኑን አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) የዜና ወኪል ዘግቧል።
ከተመደቡባቸው አገራት እንዲመለሱ የተነገራቸው የአሜሪካ ዲፕሎማቶች በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ውስጥ የሚሆናቸውን አዲስ የሥራ መደብ እንዲፈልጉ መመከራቸውን አንድ ባለሥልጣን ተናግረዋል።
በዚህ ውሳኔ ከተመደቡባቸው የአሜሪካ ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎች ለቅቀው ወደ ዋሺንግተን እንዲመለሱ ከተነገራቸው ዲፕሎማቶች መካከል አብዛኞቹ ከአፍሪካ አገራት ሲሆኑ፣ አምባሳደሮቹ ግን በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ አገራት ነው።
የአሜሪካ አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች እንዲወጡ የተደረጉባቸው ናቸው ብሎ ኤፒ ባወጣው ዝርዝር ውስጥ 28 አገራት የተጠቀሱ ሲሆን፣ ግማሾቹ የአፍሪካ አገራት ናቸው።
ከእነዚህም ውስጥ የአሜሪካ ወዳጅ የሆነችው ግብፅ እና በአፍሪካ ቀንድ የአልቃይዳ አጋር የሆነው አልሻባብ የሚንቀሳቀስባት ሶማሊያ ተጠቅሰዋል።
ግብፅ ከአረብ አገራት መካከል ከአሜሪካ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላት ከመሆኑ በተጨማሪ በየዓመቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ወታደራዊ ድጋፍን ታገኛለች።
አሁን አሜሪካ ዲፕሎማቷን ለምን ከግብፅ እንደጠራች ባይታወቅም ከአገሪቱ ጋር ያላትን ደረጃ ዝቅ ለማድረግ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም።
ሌላኛዋ አገር ሶማሊያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖች ላይ ተደጋጋሚ የአየር ጥቃት የምትፈጽመው አሜሪካ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችበት ምክንያት አስካሁን አልታወቀም።
በውሳኔ ወደ ዋሺንግተን ከተጠሩት በአፍሪካ የአሜሪካ አምባሳደሮች በተጨማሪ ስድስት ከእስያ፣ አራት ከአውሮፓ፣ ሁለት ከመካከለኛው ምሥራቅ፣ ሁለት ከደቡብ እና ማዕከላዊ አሜሪካ እንዲሁም ተጨማሪ ሁለት ከምዕራባውያን አገራት መሆናቸው ተጠቅሷል።
በዚህ ውሳኔ ምን ያህል አምባሳደሮች ከምድባቸው እንደሚነሱ ከመናገር የተቆጠቡ አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባለሥልጣን በዲፕሎማቶች ላይ የሚደረግ ለውጥ በየትኛውም የአሜሪካ "አስተዳደር ወቅት የሚካሄድ መደበኛ አሠራር ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ጨምረውም በባሕር ማዶ አገራት ውስጥ የሚመደቡ የአሜሪካ አምባሳደሮች "የፕሬዝዳንቱ የግል ተወካይ በመሆናቸው የተነሳ ቅድሚያ ለአሜሪካ የሚለውን አጀንዳውን የሚያስፈጽም ግለሰብ የመመደብ መብት አለው" ሲሉ ባለሥልጣኑ ተናግረዋል።
ነገር ግን የትራምፕ አስተዳደር እርምጃን የሚተቹ ሰዎች ውሳኔው አሜሪካ በውጪው ዓለም ያላትን ታማኝነት የሚያዳክም ነው ብለውታል።
የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ማኅበር ቃል አቀባይ ኒኪ ጋመር መንግሥት እየወሰደ ያለውን እርምጃ "ወጥነት የሌለው" በማለት "ድንገተኛ፣ ማብራሪያ የሌለው በመሆኑ በሞራል እና በውጤታማነት ላይ ተጽዕኖ ያለው ነው" በማለት ተችተውታል።
ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ዙር የሥልጣን ዘመን ወደ ፕሬዝዳንትነታቸው ከተመለሱ በኋላ የአሜሪካን በውጭ ፖሊሲ ላይ ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ጉዳዮች በብሔራዊ ደኅንነት ተቋማት ውስጥ ባሉ ቦታዎች ላይ ታማኝ ሰዎችን ሲመድቡ ቆይተዋል።
የአሜሪካ የምክር ቤት አባላት እና ዲፕሎማቶች ይህ የትራምፕ እርምጃ አገሪቱ በመላው ዓለም በዲፕሎማሲው መስክ ያላትን ተጽእኖ ለቻይና እና ለሩሲያ አሳልፎ የሚሰጥ ነው በማለት እየተቹ ነው።















