በግሪክ የተከሰከሰው አውሮፕላን ፈንጂዎችና የጦር መሳሪያዎች ጭኖ ነበር ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሰሜናዊ ግሪክ ውስጥ በምተገኘው ካቫላ ከተማ አቅራቢያ ወድቆ የተከሰከሰው የጭነት አውሮፕላን ፈንጂዎችን ጨምሮ 11 ቶን የጦር መሳሪያዎችን ወደ ባንግላዴሽ ለማድረስ የጫነ እንደነበር ባለሥልጣናት ተናገሩ።
በዚህም ሳቢያ የጭነት አውሮፕላኑ ከወደቀበት ስፍራ በሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል።
ዩክሬን ውስጥ የሚገኝ ኩባንያ የሚያስተዳድረው አንቶኖቭ-12 የተባለው የጭነት አውሮፕላን ቅዳሜ ዕለት አደጋ ሲደርስበት በውስጡ የነበሩ ስምንት ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።
ከአደጋው በኋላ የወጡ የቪዲዮ ምስሎች እና የዐይን ምስክሮች አውሮፕላኑ ወደ መሬት እየቀረበ ሳለ በእሳት እንደተያያዘና ወዲያውኑ መሬት ላይ ሲከሰከስ ከባድ ፍንዳታ መከሰቱን አሳይተዋል፣ ተናግረዋል።
ለጥንቃቄ ሲባልም ዕሁድ ጠዋት ላይ አደጋው የደረሰበትን ቦታ ለመቃኘት ድሮኖች ተሰማርተው ነበር።
የግሪክ መንግሥት ቴሌቪዥን እንደዘገበው የአገሪቱ ሠራዊት፣ የፈንጂ ባለሙያዎች እና የአውቶሚክ ኃይል ኮሚሽን ሠራተኞች የአደጋው ስፍራ ለደኅንነት አስጊ አይደለም አስኪባል ድረስ ወደ ቦታው አልተጠጉም።
አውሮፕላኑ ወድቆ ከመከስከሱ በፊት አብራሪው የሞተር ችግር እንዳጋጠመውና በድንገተኛ ሁኔታ ለማረፍ የካቫላ አየር ማረፊያን ጠይቆ ነበር። ነገር ግን አደጋው የደረሰው አየር ማረፊያ ከመድረሱ አስቀድሞ ነው።
አደጋው በተከሰተበት አካባቢ ባሉ ነዋሪዎች ምሽት ላይ የታየው አውሮፕላን በመኖሪያ አካባቢ ባለመውደቁ ዕድለኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኤይሚሊያ ሳፕታኖቫ የተባለችው ነዋሪም አውሮፕላኑ ዝቅ ብሎ ሲጓዝ እንዳየችውና በመኖሪያ ቤቶች ላይ አለመውደቁ በእጅጉ እንዳስደነቃት ተናግራለች።
“በጭስ ተሸፍኖ ነበር፣ ለመግለጽ የማልችለው አይነት ድምጽ እያሰማ ከተራራው አልፎ ሄደ” ብላለች። ጨምራም አውሮፕላኑ ተራራውን አልፎ ከዞረ በኋላ ሜዳ ላይ መከስከሱን ገልጻለች።
“እሳት ስለነበረው በጣም ፈርተን ነበር። በርካታ የእሳት አደጋ ማጥፊያ መኪኖች ቢመጡም፣ ያልተቋረጠ ፍንዳታ ስለነበረ ወደሚቃጠለው አውሮፕላን መጠጋት አልቻሉም” ብላለች።
የሰርቢያ የመከላከያ ሚኒስትር ኔቦይሳ ስቴፋኖቪች እንደተናገሩት፣ የተከሰከሰው አንቶኖቭ ኤኤን-12 የጭነት አውሮፕላን ወደ 11 ቶን የሚደርስ ክብደት ያላቸው ሰርቢያ ውስጥ የተሰሩ የጦር መሳሪያዎችን ወደ ባንግላዴሽ እያጓጓዘ ነበረ።
አውሮፕላኑ የመጨረሻ ማረፊያው ከነበረችው የባንግላዴሽ ዋና ከተማ ዳካ ከመድረሱ በፊት በዮርዳኖስ፣ በሳዑዲ አረቢያ እና በሕንድ ለማረፍ ዕቅድ ይዞ ነበር።
አደጋው የደረሰበት የጭነት አውሮፕላን ሜሪዲያን በተባለ የዩክሬን የጭነት አገለግሎት ሰጪ የአየር መንገድ የሚተዳደር ሲሆን፣ አደጋውን በተመለከተ ከድርጅቱ በኩል አስካሁን የተባለ ነገር የለም።
የግሪክ መንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያ የሆነው ኢአርቲ አደጋውን ተከትሎ እንደዘገበው አውሮፕላኑ 12 ቶን የሚመዝን "አደገኛ ሊሆን የሚችል" ያለውን ጭነት ይዞ ነበር ብሏል።
“ምሽት ላይ በቅርብ በሚሰማው የአውሮፕላን ሞተር ተገርሜ ወደ ውጪ በመውጣት ስመለከት የአውሮፕላኑ ሞተር ላይ እሳት አየሁ” ሲል ጂዮርጂዮስ አርኮንቶፖለስ የተባለው የአካባቢው ነዋሪ ለአገሪቱ ቴሌቪዥን ተናግሯል።
በርካታ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች እንዳመለከቱት የዐይን እማኞች የአውሮፕላኑን መውደቅ ተከትሎ ፍንዳታ መስማታቸውን ገልጸዋል።
የአውሮፕላኑን መከስከስ ተከትሎ የአካባቢው ባለሥልጣናት ወደ አደጋው ስፍራ ሰባት የእሳት አደጋ ማጥፊያ ተሽከርካሪዎችን ቢልኩል፣ በተከታታይ በነበረው ፍንዳታ ምክንያት የእሳት አደጋ ሠራተኞች አውሮፕላኑ ወደ ወደቀበት ቦታ መቅርብ አለመቻላቸውን ተናግረዋል።












