የእግር ኳሱ ንጉሥ ቅጽል ስም ‘ፔሌ’፣ ‘ልዩ’ በሚል አቻ ትርጉም በመዝገበ ቃላት ተካተተ

የእግር ኳሱ ንጉስ ፔሌ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቅርቡ በሞት የተለየው ብራዚላዊው የእግር ኳስ ንጉሥ ቅጽል ስም፣ ፔሌ “ልዩ፣ ወደር የሌለው፣ የተለየ” የሚሉ አቻ ቃላት ተሰጥተውት በመዝገበ ቃላት ተካተተ።

ፔሌ የሚለውን ቃል አዲስ ቅጽል አድርጎ በበይነ መረብ ሕትመቱ ውስጥ ያካተተው በብራዚል ታዋቂ የሆነው የፖርቹጋል ቋንቋ መዝገበ ቃላት ሚካኤሊስ ዲክሽነሪ ነው።

ቅጽል ቃሉ በመዝገበ ቃላቱ የተካተተው ፔሌ ፋውንዴሽን ለእግር ኳሱ ኮከቡ ክብር ለመስጠት በሚል ባካሄደው ዘመቻ ከ125 ሺህ በላይ ፊርማ ካሰባሰበ በኋላ ነው።

ዝነኛው ብራዚላዊ የእግር ኳስ ተጫዋች በ82 ዓመቱ ባለፈው ታኅሣሥ ወር ላይ ከዚህ ዓለም መለየቱ ይታወሳል።

የዓለም ዋንጫን ሦስት ጊዜ ያነሳ ብቸኛው ተጫዋች ፔሌ፣ በእግር ኳሱ ታሪክ ምርጡ ተጫዋች ነው።

በአውሮፓውያኑ 2000 የፊፋ የክፍለ ዘመኑ ኮከብ ተጫዋች ተብሎም ተመርጧል።

ፔሌ ለሁለት አስርተ ዓመታት በቆየበት የእግር ኳስ ሕይወቱ፣ ለብራዚል ብሔራዊ ቡድን ሳንቶስ እና ለአሜሪካው ‘ኒው ዮርክ ኮስሞስ’ ክብረ ወሰን የተባለ 1 ሺህ 281 ጎሎችን አስቆጥሯል።

ፔሌ ባጋጠመው የአንጀት ካንሰር ሕይወቱ ካለፈ በኋላ የቀድሞ ክለቡ ሳንቶስ፣ የስፖርት ቻናሉ ስፖርቲቪ እና ፔሌ ፋውንዴሽን የእግር ኳስ ኮከቡ ስም በመዝገበ ቃላት እንዲካተት ጥረት ሲያደርጉ ነበር።

በዚህም ረቡዕ ዕለት የሚካኤሊስ መዝገበ ቃላት አሳታሚ፣ ቃሉ በፖርቹጋል ቋንቋ መዝገበ ቃላት ዲጂታል ዕትም ላይ ወዲያውኑ እንዲሁም በሚቀጥለው ዕትም የመጽሐፍ ሕትመቱ ላይ እንደሚካተት አስታውቋል።

መዝገበ ቃላቱ “ፔሌ” የሚለውን ቅጽል ቃል እስከ አነባበቡ ያስቀመጠ ሲሆን፣ ልክ ፔሌ በሚል ቅጽል ስሙ እንደሚታወቀው እና የምንጊዜም ምርጥ፣ የተለየ እና ወደር የለሽ ስፖርተኛ ኢድሰን አራንትስ ዶ ናሲሜንቶ፣ ባለው ብቃት፣ ዋጋ ወይም የበላይነት ከተለመደው ወጣ ያለ፣ ከማንም ከምንም ጋር የማይወዳደር፣ የሚል አቻ ትርጉም ሰጥቶታል።

የእግር ኳስ ተጨዋቹን ታሪክ ጠብቆ ለማቆየት የተመሠረው ግብረ ሰናይ ድርጅት ፔሌ ፋውንዴሽንም ቃሉ በመዝገበ ቃላት መካተቱ “ለንጉሡ የሚገባ ክብር ነው” ብሏል።

“በማንኛውም ነገር ላይ የተሻለ የሆነን ሰው ለማመልከት ጥቅም ላይ በዋለው አገላለጽ በመዝገበ ቃላቱ ገጽ ላይ “ሕያው ሆኗል” ሲል ፋውንዴሽኑ በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል።