ብራዚላዊው የእግር ኳስ ፈርጥ ፔሌ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

ፔሌ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከዓለም ኮከብ ተጫዋቾች ቀዳሚው እንደሆነ የሚነገርለት ብራዚላዊው እግር ኳሰኛ ፔሌ በ82 ዓመቱ ሕይወቱ አለፈ። 

በ21 ዓመታት የእግር ኳስ ህይወቱ 1363 ጨዋታዎችን አድርጎ 1281 ጊዜ ኳስን እና መረብን በማገናኘት ክብረ ወሰኑን ጨብጧል። 

ለቢጫ ለባሾቹ ብራዚሎች 92 ጊዜ ተሰልፎ 77 ጎሎችን አስቆጥሯል። 

ሦስት የዓለም ዋንጫዎችን ያነሳ ብቸኛው ተጫዋች ፔሌ ነው። ከ1958፣ 1962 እና 1970 ድሎቹ በተጨማሪ በፈረንጆቹ 2000 የፊፋ የክፍለ ዘመኑ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል። 

የቀድሞው እግር ኳሰኛ በኩላሊት እና ፕሮስቴት ችግሮች ያለፉትን ጥቂት ዓመታት ሆስፒታል ሲመላለስ ቆይቷል። 

መስከረም 2021 ዕጢ ለማስወጣት የተሳካ ቀዶ ህክምና በሳኦ ፖሎው አልበርት አንስታይን ሆስፒታል አከናውኗል።

በድጋሚ ባለፈው ወር ወደዚሁ ሆስፒታል ለተጨማሪ ህክምና መግባቱ ታውቋል። 

ልጁ ኬሊ ናሲሜንቶ የጤንነቱን ሁኔታ ከተኛበት ሆስፒታል ለወዳጆቹ በማህበራዊ ሚዲያዎች ስታደርስ ቆይታለች።

ሐሙስ ዕለት የቤተሰቡ አባላት እጆች የፔሌእጆች ላይ ያረፉበትን ምስል ለጥፋ “ማድረግ የምንችለው አንተን ማመስገን ነው። ለዘለዓለሙ እንወድሃለን። በሠላም እረፍ” ስትል ጽፋለች።

“የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቹ ሥራ በማቆማቸው ምክንያት” ፔሌ ሕይወቱ ማለፉን ሆስፒታሉም አረጋግጧል።

የብራዚል እግር ኳስ ኮንፈደሬሽን ደግሞ “ፔሌ ከምንግዜውም ምርጥ የስፖርት ሰውም በላይ ነው” ሲል ገልጾታል።

"ችግር ሲገጥመው በጭራሽ የማይፈራው የእግር ኳስ ንጉሳችን ለድል አድራጊዋ ብራዚል ትልቁ መገለጫ ነበር። ለአባቱ የዓለም ዋንጫን እንደሚያሸንፍ ቃል ገብቶለት አንድ ሳይሆን ሦስት አሳክቶልናል። "ንጉሱ አዲስ ብራዚል አስረከበን። ለዚህም ምስጋናችን የላቀ ነው። እናመሰግናለን ፔሌ" ብሏል።

የፔሌን ሞት ተከትሎ ፕሬዝዳንትጃዬር ቦልሶናሮሦስት ብሔራዊ የሐዘን ቀናት አውጀዋል።

የፔሌ የቀድሞ ክለብ ሳንቶስ የቀብር ሥነ ሥርዓቱን መርሃ ግብር ይፋ አድርጓል።

ሰኞ ጠዋት አስከሬኑ ከሆስፒታል ወደ ክለቡ ኢስታዲዮ ኡርባኖ ካልዴራ ያመራል። አስከሬኑ መሃል ሜዳ ሆኖ ህዝቡ የክብር አሸኛነት ያደርግለታል።

ማክሰኞ በሳኦ ፖሎው ሳንቶስ ጎዳና ተጉዞ ቤተሰቡ የግል የቀብር ስነ ስርዓት ያካሂዳል።

ፔሌ በመባል የሚታወቀው ኤዲሰን አራንቴስ ዶ ናሲሜንቶ በ17 ዓመቱ ብራዚል የስዊዲኑን የዓለም ዋንጫ በ1958 እንድታነሳ በመርዳቱ የዓለም ኮከብ መሆኑን ማስመስከር ቻለ።

ፔሌ በ1970 (እአአ) የዓለም ዋንጫ ግብ ካስቆጠረ በኋላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፔሌ በ1970 (እአአ) የዓለም ዋንጫ ግብ ካስቆጠረ በኋላ

ፔሌ እና የ1958ቱ የዓለም ዋንጫ

ድንቅ የስፖርት ሰው ፔሌን ለተቀረው ዓለም ያስተዋቀው የ1958ቱ የዓለም ዋንጫ ነበር።

ብራዚል ለ1958ቱ የዓለም ዋንጫ ወደ ስዊድን ስታቀና ፔሌ ገና የ17 ዓመት ጎረምሳ ነበር።

ብራዚል ዋንጫውን ለመጀመሪያ ጊዜ ለማንሳት ስትጫወት ወጣቱ ፔሌ በመጀመሪያዎች ሁለት የምድብ ግጥሚያዎች ተሰልፎ የመጫወት ዕድል ሳይሰጠው ቀረ።

በሦስተኛው የምድብ ጨዋታ ብራዚል ከሶቪየት ኅብረት ስትጫወት ዕድል አግኝቶ ወደ ሜዳ ገብቶ አስደናቂ አቋም አሳየ። በሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ደግሞ ብራዚል ዌልስን 1 ለ 0 ስታሸንፍ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ጎል ሲያስቆጥር ትኩረትን መሳብ ቻለ።

ከዚያማ ፔሌን የሚያስቆመው አልተገኘም።

በግማሽ ፍጻሜው ፈረንሳይ ላይ ሦስት ጎሎችን አስቆጥሮ ብራዚል 5 ለ 2 በሆነ ውጤት አሸንፋ ወደ ፍጻሜው አመራች። ከዚያም በፍጻሜው ስዊድን ላይ ሁለት ግብ አስቆጥሮ አገሩ ብራዚል ዋንጫውን ለመጀመሪያ ጊዜ እንድታነሳ አስቻለ።

ፔሌ በእግር ኳስ ሕይወቱ በሦስት የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ ተሳትፏል። ቺሊ ባሰናዳችው የ1962 ዓለም ዋንጫ ሁለት ጨዋታዎች ብቻ ተሰልፎ በጉዳት ከውድድሩ ውጪ ሆነ።

በ1970 የዓለም ዋንጫ ፔሌ ድንቅ አቋሙ የታየበት ነበር። በዚህ መድረክ የፍጻሜው ጨዋታን ጨምሮ 4 ጊዜ ጎል አስቆጥሮ ነበር።

ፔሌ

ፔሌ ለክለቡ ሳንቶስ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያከናወነው በ15 ዓመቱ ነው። በዚህ ጨዋታ ኮረንቲያስ ደ ሳንቶ አንደሬን 7 ለ 1 ሲያሸንፉ ኳስ እና መረብ ለማገናኘት ቻለ።

የብራዚል እግር ኳስ ኮንፈደሬሽን ፔሌ በ1367 ዋታዎች 1283 ጎሎችን አስቆጥሯል ይላል። የፊፋ ቁጥር ከዚህ የተለየ ነው። ፊፋ በ1366 ጨዋታዎች 1281 ጎሎችን ከመረብ አሳርፏል ሲል ይገልጻል።

በ1962ቱ የዓለም ዋንጫ ድንቅ ጎል ሜክሲኮ ላይ ያስቆጠረው ፔሌ ቀሪዎቹን ጨዋታዎች በጉዳት አልተሰለፈም።

ቢጫ ለባሾቹ በ1970 ዋንጫ ሲያነሱ በፍጻሜ ጨዋታ ጎል አስቆጥሯል።

ኒልተን ሳንቶስ ደረት ላይ ካፈሰሰው እንባ ጀምሮ ፔሌ በርካታ ዘመን ተሻጋሪ ጉዳዮች ከመታወስ ባለፈ ስፖርቱንም እስከወዲያኛው ቀይሮታል።

ጫማውን የሰቀለው ለአሜሪካው ኒው ዮርክ ኮስሞስ ቡድን ከተጫወተ በኋላ ነው።

“ለሙዚቃ ቤትሆቨን እና ሌሎችም እንዳሉላት፤ ለእግር ኳስ ደግሞ ፔሌ እና ሌሎችም አሉላት” ሲል በአንድ ወቅት ተናግሮ ነበር።

ቢቢሲ ስፖርት በ2020 ባደረገው የሕዝብ አስተያየት ፔሌ ከሊዮኔል ሜሲ፣ ክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ ዲኣጎ ማራዶና እና ዮሃን ክራይፍ ቀድሞ የምንግዜም ኮከብ ተጫዋች ተብሏል።