በግብፅ የተገኙት የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ኢትዮጵያ ሊጓዙ ነው

የሩሲያ እና የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የሩሲያ እና የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች

ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስጥ የምትገኘው የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን በግብፅ ጀመሩ።

ላቭሮቭ ከግብፅ ጉብኝት በኋላ ወደ ኮንጎ ብራዛቪል አቅርንተዋል። በማስከተልም ወደ ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ እንደሚጓዙ ተገልጿል።

ጉዟቸውን በካይሮ የጀመሩት ላቭሮቭ ከግብፁ አቻቸው ሳሚ ሹኩሪ ጋር ተገናኝተው የተነጋገሩ ሲሆን፤ ሩሲያ ለግብፅ የምታቀርበውን ስንዴ አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ በከፈተችው ጦርነት የአረቡ ዓለም አገራት እና አፍሪካ በእህል አቅርቦት እጥረት ክፉኛ ተጎድተዋል።

በግብፅ ለአረብ ሊግ አምባሳደሮች ንግግር ያደረጉት ላቭሮብ፣ በአገራቸው ላይ የተጣለው ማዕቀብ በዓለም የምግብ ዋስትና ላይ እያሳደረ ስላለው ተጽእኖ የምዕራባውያን አገራት እውነታውን እያጣመሙ ነው ብለዋል።

"ምዕራባውያን አገራት የበላይነታቸውን በሌሎች ላይ ለመጫን እየሞከሩ ነው" ሲሉም ከሰዋል። እንዲሁም ሞስኮ የዓለምን የምግብ ቀውስ አስከትላለች የሚለውን ወቀሳ አጣጥለውታል።

ምዕራባዊያኑ በሩሲያ ላይ እያደረሱ ያሉትን ዲፕሎማሲያዊ ጫናን ለመመከት ወደ አፍሪካ ጉዞ ማድረግ የጀመሩት ላቭሮቭ፤ ጨምረውም በአገራቸው ላይ የጣሏቸው ማዕቀቦች ዓላማቸው "ስለ ዩክሬን ሳይሆን ወደፊት ዓለምን ስለመቆጣጠር ነው" ሲሉ ተናግረዋል። "እያንዳንዱ ሰው ሕግን መሠረት ያደረገ የዓለም ሥርዓትን መደገፍ አለበት'' ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ሕጎቹም የተፃፉት የምዕራባውያንን ፍላጎት በሚጠቅም መልኩ እና ልዩ ሁኔታዎች ላይ በመመስረት ነው ብለዋል።

ዩክሬን እና ሩሲያ ከ40 በመቶ በላይ የሚሆነውን የአፍሪካን ስንዴ ፍላጎት እንደሚያቀርቡ የአፍሪካ ልማት ባንክ መረጃ ያሳያል። ግብፅ ከፍተኛ የዩክሬን ስንዴ ተጠቃሚ ስትሆን እ.ኤ.አ. በ2019 ከማንኛውም አገር በበለጠ 3.62 ሚሊዮን ቶን ስንዴ ከዩክሬን ገዝታለች።