በናይጄሪያ ማዕድን ማውጫ ውስጥ 30 ሰዎች በመርዛማ ጋዝ ታፍነው ሞቱ

በሟቾች የቀብር ሥነ ስርዓት ለይ የተገኙ ሰዎች
የምስሉ መግለጫ, በሟቾች የቀብር ሥነ ስርዓት ለይ የተገኙ ሰዎች
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በማዕከላዊ ናይጄሪያ በዚንክ ማዕድን ማወጫ ስፍራ በካርቦንሞኖኦክሳይድ ታፍነው ነው የተባሉ 33 ሰዎች መሞታቸውን የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ተናገሩ።

አደጋው የደረሰው ሶሊድ ዩኒቲ ናይጄሪያ የተባለ የማዕድን ኩባንያ በሚያስተዳድረው እና ዋሴ ከምትባል ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ስፍራ ነው።

መርዛማ ጋዙ በማዕድን ቁፋሮው በሚካሄድበት ጉድጓድ ውስጥ በመከማቸቱ የታፈኑ ሰዎች የምሽት ፈረቃቸው ከማለቁ በፊት ራሳቸውን መሳታቸው ተነግሯል።

የማዕድን ቆፋሪዎቹ መሞታቸው የታወቀው የጠዋት ፈረቃ ሠራተኞች ለሥራ በሚገቡበት ወቅት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ከ20 በላይ ሠዎችን ማትረፍ እና ወደ ሆስፒታል መውሰድ ተችሏል።

የጸጥታ ሠራተኞች የማዕድን ማውጫውን ያሸጉ ሲሆን መርዛማ ጋዙ በማዕድን ጉድጓድ ውስጥ እንዴት ሊከማች ቻለ የሚለውን ምርመራ እያደረጉ ነው።

የግዛቲቱ ባለሥልጣናት በጸጥታ ስጋት ምክንያት እስካሁን ድረስ አደጋው የደረሰበትን ስፍራ ያልጎበኙ ሲሆን የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ምላሽም በጣም ዘገምተኛ ነው ተብሏል።

በአካባቢው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የታጠቁ ዘራፊ ቡድኖች ይንቀሳቀሳሉ።

ማለዳ ወደ ሥራ ቦታው ሲመጣ የሥራ ባልደረቦቹ ሞተው ያገኘው ሳፊያኑ ሃሩና ለቢቢሲ እንደተናገረው የተወሰኑ በጉድጓድ ውስጥ የነበሩ ማዕድን ቆፋሪዎች መትረፍ በመቻላቸው በዋሴ ወደሚገኝ የሕክምና ተቋም ተወስደዋል።

እንደ ሃሩና ከሆነ አደጋው የደረሰው ከማለዳው 12፡30 ሲሆን 37 የማዕድን ቆፋሪዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

የማዕድን ቆፋሪዎቹ ጠዋት ፀሎታቸውን አድርሰው የሥራ ሰዓታቸውን ለማጠናቀቅ ወደ ማዕድን ማውጫው ጉድጓድ መመለሳቸው ነበር።

የፕላቱ ግዛት አስተዳዳሪ የመጀመርያ ደረጃ ምርመራ ውጤት በሚል ያወጣው መግለጫ 33 ሰው በደረሰ ፍንዳታ የተነሳ መሞታቸውን ገልጿል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዓይን እማኞች ግን የማዕድን ቆፋሪዎቹ በፍንዳታ ምክንያት አለመሞታቸውን ተናግረዋል።

"ካርቦንሞኖኦክሳይድ ነው አፍኖ የገደላቸው" ይላል ሃሩና።

አክሎም "ምንም የሕይወት አድን ጥረት አልነበረም በወቅቱ፤ ምክንያቱም ማለዳ ፈረቃቸውን ለመጀመር የሚመጡ ሠራተኞች በሙሉ አልደረሱም ነበር" ብሏል።

"ሕይወታቸወን ለማሸነፍ የሚጣጣሩ 37 ሰዎችን ማጣት በጣም ያሳዝናል። በአደጋው በጣም ተረብሸናል።"

በአደጋው የሞቱት ሰዎች እድሜያቸው ከ20 እስከ 40 የሚገመት ሲሆን በአካባቢው ባህል መሠረት አደጋው በደረሰ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ቀብራቸው መፈጸሙን ሌላ የአካበቢው ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በናይጄሪያ በተደጋጋሚ በማዕድን ማውጫ ስፍራዎች በሚደርስ አደጋ የሰዎች ሕይወት ያልፋል።

የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ በኒጀር ግዛት የሚገኝ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ተደርምሶ በርካቶች ሞተዋል።

የአካባቢው ባለሥልጣናት አደጋው የደረሰው በወቅቱ ጥሎ በነበረው ዝናብ የተነሳ መሆኑን ተናግረው ነበር።

አሁን የደረሰው አደጋ በናይጄሪያ የማዕደን ማውጫ ጉድጓዶች ውስጥ ተግባራዊ የሚደረጉ የደህንንት መስፈርቶች ላይ ጥያቄ አስነስቷል።