በድሆች መንደር ትምህርት ቤት በመክፈት አንድ ሚሊዮን ዶላር ያሸነፈችው መምህርት

በኮላባ የሚገኘው ማዕከል ግድግዳዎቹ ላይ ቆሻሻን ስለማስወገድ የሚየገልፅ ሥዕል አለው
የምስሉ መግለጫ, በኮላባ የሚገኘው ማዕከል ግድግዳዎቹ ላይ ቆሻሻን ስለማስወገድ የሚየገልፅ ሥዕል አለው
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በሕንድ ሙምባይ ከተማ ኮላባ ገበያ አካባቢ በቀጭን መንገድ አካባቢ በአነስተኛ ኮንክሪት የተሠሩ አራት ማዕዘን ቤቶች ይታያሉ።

በአካባቢው ዙሪያ ከዝቅተኛ ግብዓቶች የተገነቡ ቤቶች በደማቅ ቀለሞች አሸብርቀዋል። በቀይ፣ ሰማያዊ፣ አረንጓዴ እና ቢጫ ቀለሞች ደምቀዋል።

መንደሩ በአብዛኛው በፅዳት ሠራተኞች እና በቤተሰባቸው የተሞላ ነው፤ እዚያው ይኖራሉ እዚያው ይሠራሉ።

በዚህ መካከል ሽጉጥ ያለ አነስተኛ የትምህርት ማዕከል መሠረታዊ ሒሳብ እና የቋንቋዎች ነፃ ትምህርት ያቀርባል። ሕፃናትን ለመጀመሪያ ጊዜ መደበኛ ትምህርት እንዲያገኙ ወይም ትምህርት ካቋረጡ በኋላ እንዲመለሱ ያግዛል።

ማዕከሉ ለትርፍ ባልተቋቋመ ድርጅት ይመራል። ማዕከሉ ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የተገለሉ ማኅበረሰቦች ትምህርት እንዲያገኙ በምትሠራው በ45 ዓመቷ አርቲስት ሩቤል ናጊ በገንዘብ ይደገፋል።

ሩቤል ናጊ በትምህርት ማዕከሏ
የምስሉ መግለጫ, ሩቤል ናጊ በህንድ ትምህርት ላይ ላበረከተችው አስተዋፅኦ የ2016 ዓለም አቀፍ የመምህራን ሽልማትን አሸንፋለች

በዚህ ወር መጀመሪያ ናጊ ቫርኪ ፋውንዴሽን ከዩኔስኮ ጋር በመተባበር ለሙያው ልዩ አበርክቶ ለተጫወቱ መምህራን የሚሸልመውን ሽልማት ከአንድ ሚሊዮን ዶላር ጋር አሸንፋለች።

ናጊ ከ139 አገራት የተውጣጡ ከአምስት ሺህ ዕጩዎች እና አመልካቾች ነው የተመረጠችው።

የዓለም አቀፍ መምህራን ሽልማት እንዳለው ናጊ ሩቤል ናሂ አርትስ ፋውንዴሽን በተባለው መንግሥታዊ ባልሆነው ድርጅቷ በመላው ሕንድ ከ100 በላይ በተገለሉ ማኅበረሰቦች እና መንደሮች 800 የመማሪያ ማዕከላትን መሥርታለች።

ናጊ ራቅ ላሉ ማኅበረሰቦች ትምህርትን ለማቅረብ ያደረባት ፍላጎት ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ባልታሰበ መንገድ የተጀመረ ነው።

ጥንስሱ የተጀመረው ሞምባይ የሥነ ጥበብ መሥሪያዋ ውስጥ አንድ ልጅ ሰተት ብሎ ሲገባ ነው። ሕፃኑ በደሆች መንደር እንደሚኖር እና ትምህርት ቤት ለመሄድ አቅም እንደሌለው ተረዳች።

ናጊ ከሕፃኑ ጋር ያደረገችው ቆይታ መኖሪያውን እንድታይ እንደገፋፋት እና የቤቶች ግድግዳ ላይ ሥዕል ለመሳል ጥያቄ እንድታቀርብ እንዳደረጋት ትናገራለች።

"ሥዕል የምንስልበት አካባቢ ላይ ሕፃናት መሰባሰብ ጀመሩ። ተረት መስማት ይፈልጉ እንደሆነ ጠየኳቸው። ሁሉም አዎ አሉ" ትላለች በማስታወስ።

በደሃ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት መማር እንደሚፈልጉ እና የትምህርት ፍላጎታቸውን በሥነ ጥበብ ማነሳሳት እንደምትችል ያኔ እንደገባት ናጊ ትናገራለች።

ባለፉት ዓመታት ናጊ እና ቡድኗ በመላው ሕንድ በርካታ ከተሞች ላይ ፅንሰ ሀሳብን ቀለል ለማድረግ መምህራን ሥነ ጥበብን መሠረት ያደረገ ትምህርት እንዲያስተምሩ የሚደረግበት የትምህርት ማዕከላትን ከፍተዋል።

ስዕል የተሳለበት ሱቅ ውስጥ ህፃን ቁጭ ብሎ
የምስሉ መግለጫ, የናጊ ፋውንዴሽን በደሆች መንደር ግድግዳዎች ላይ አስተማሪ ስዕሎችን ይስላል

በጎ ፈቃደኞች ክህሎት መሠረት ያደረጉ ትምህርቶችን ለመስጠት ይሰባሰባሉ፤ ልገሳዎች ደግሞ ልጆች መጻሕፍት፣ ቦርሳዎች እና ሌሎችን የትምህርት ቁሳቁሶችን ለማቅረብ ያግዛል።

አንዳንድ ጊዜ ትምህርቱ ተማሪዎች በመንደሩ ክፍት ቦታ ላይ ምንጣፎች ላይ ተቀምጠው ይሰጣል።

"ትምህርት የትም ቦታ ሊሰጥ ይችላል። መሳጭ እንዲሆን ማድረግ [ግን] ያስፈልጋል" ትላለች ናጊ።

ይሁን እንጂ እነዚህን ማዕከላት ማስተዳደር ፈተናም አለው። ናጊ አብዛኞቹ ሕፃናት ችግር ካለበት ቤተሰብ የሚመጡ በመሆናቸው መምህራት ሚናቸውን እንደ አማካሪ እና ጠባቂ ከፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

"አንድ ልጅ ለሳምንት በአንደኛው ማዕከላችን የማይገኝ ከሆነ በጎ ፈቃደኛ ቤቱ ሄዶ ይጠይቃል" ስትል ናጊ ታብራራለች።

ወላጆች በልጆቻቸው ትምህርት ላይ ፍላጎት እንዲያሳድሩ መደበኛ ውይይት እንደምታደርግም ትናገራለች። ይህ ብዙዎቹን ተማሪዎቿ ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ እና ከማዕከሉ በኋላ ኮሌጅ ትምህርትም እንዲከታተሉ ማገዙን ትገልፃለች።

ማዩር ስዕል እየሳለ
የምስሉ መግለጫ, የቀድሞ የማዕከሉ ተማሪ ማዩር

ማዩር የቀድሞ ተማሪ ሲሆን አሁን የራሱን የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት እና አነስተኛ የህትመት ሥራ ከፍቷል። ከተመሳሳይ ማኅበረሰብ የሚወጡ ልጆች እርሱ ያገኘውን ዕድል እንዲያገኙ ቅዳሜ እና እሁድ በናጊ ፋውንዴሽን በጎ ፈቃደኛ ሆኖ ያገለግላል።

"በእንደዚህ ዓይነት ስፍራዎች ስትሠራ ከልጆቹ ብቻ ሳይሆን ከሁሉም ማኅበረሰብ ጋር ግንኙነት መመሥረት አለብህ። ይህ በገንዘብ እርዳታ፣ በአስቸጋሪ ጊዜ እጅ መስጠት ወይም ለጨነቀው ሰው ጆሮ መስጠት ሊሆን ይችላል። እምነታቸውን እና የማኅበረሰቡን ድጋፍ ካገኘን መልካም ሥራችንን መቀጠል እንችላለን" በማለት ናጊ ታብራራለች።

ናጊ በቆሻሻ የተከበቡ ሰፈራዎችን ወደ ክፍት የመማሪያ ክፍሎችን በሚቀይረው ፋውንዴሽኗ ተምሳሌታዊ ሥራ ጥልቅ ስሜት እንዳላት ትናገራለች።

ከሳይንስ እስከ ንፅህና፤ ከአካባቢያዊ ግንዛቤ እስከ ማኅበራዊ ኃላፊነት ድረስ የሚዘልቁ ርዕሶች ያሏቸው ትምህርታዊ ሥዕላትን በግድግዳዎች ላይ ይሳላሉ።

ናጊ እነዚህ የግድግዳ ሥዕሎች በነዋሪዎች ዘንድ የማወቅ ጉጉት እንደሚፈጥሩ እና ባህሪ እና አስተሳሰብን ለመቀየር መርዳት እንደሚችሉ ትናገራለች።

ሁለት ሕፃት ተማሪዎች ክፍል ውስጥ
የምስሉ መግለጫ, ኩሺ (በስተግራ) ስታደግ መምህርት መሆን እንደምትፈልግ ትናገራለች

በአንድ ሚሊዮን ዶላር የሽልማት ገንዘቡ ናጊ የፋውንዴሽኗን ሥራዎች በማስፋፋት በተጨማሪ የሕንድ አካባቢዎች ማዕከላቱን የመክፈት ተስፋ አላት።

የኮላባ ሰፈራ ግድግዳዎች በሥዕሎች እና በአነቃቂ ጥቅሶ የተሞሉ ናቸው። የትምህርት ማዕከላቱ ግድግዳዎችም በደማቅ ቀለሞች እና ከዕፀዋት እስከ እንስሳት በሥዕል ያሸበረቀ ነው።

የሰባት ዓመቷ ኩሺ በማዕከሉ ተማሪ ናት። ትምህር ቤት መመጣት እንደሚያስደስታት እና መምህር የመሆን ህልም እንዳላት ትናገራለች። የቤት ሠራተኛ የሆነችው እናቷ የቤተሰቡ ብቸኛ አስተዳዳሪ ናት።

ሌሎች በርካታ ልጆች ከተመሳሳይ የኢኮኖሚ ደረጃ የሚመጡ ቢሆኑም፤ ሁሉም ትልቅ ህልም አላቸው። እና የናጊ ትምህርት ቤቶች ይህን ህልም እውን ለማድረግ ሚና እንደሚጫወቱ ተስፋ ሰንቀዋል።