የእንግሊዘኛ ቋንቋ ፈተና በጣም ከባድ በመሆኑ የደቡብ ኮሪያው የፈተና ኃላፊ ሥራ ለቀቁ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሱኔንግ በሚባለው የደቡብ ኮሪያ የኮሌጅ መግቢያ ፈተና ላይ የተሰጠው የእንግሊዝኛ ፈተና በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ አንዳንድ ተማሪዎች ጥንታዊ ቋንቋን እንደመተርጎም ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ "እብደት" ሲሉ ገልጸውታል።
በዘንድሮው ፈተና ዙሪያ ከፍተኛ ትችት በመሰንዘሩ ለተፈጠረው "ግርግር" ኃላፊነቱን በመውሰድ ፈተናውን በበላይነት የመሩት ከፍተኛ ባለሥልጣን ሥራቸውን ለቅቀዋል።
"የጥያቄዎች አስቸጋሪነት... ተገቢ እንዳልሆነ የሚገልጸውን ትችት ከልብ እንቀበላለን" ሲሉ የሱኔንግ ዋና ኃላፊ ኦህ ሴንግ-ጊኦል ተናግረዋል። በርካታ የአርትዖት ሥራ ቢከናወንም ፈተናው "ተገቢ አልነበረም" ሲሉ አክለዋል።
በጣም ከባድ ከነበሩት ጥያቄዎች መካከል የአማኑኤል ካንትን የሕግ ፍልስፍና የሚመለከተው እና ከቃላት ጨዋታ ጋር የሚገናኙት ይጠቀሳሉ።
የቃላት ጨዋታው ሦስት ነጥብ ያለው ሲሆን ተማሪዎች አንድን ዓረፍተ ነገር በተሰጣቸው አንቀጽ ውስጥ የት እንደሚገባ እንዲመርጡ የሚጠይቅ ነው።
ብዙዎች ጥያቄውን እና ሌሎች በርካታ ቃላትን የጻፉበትን መንገድ ተችተዋል።
ተማሪዎች ለ45 ጥያቄዎችን 70 ደቂቃዎች ተሰጥቷቸዋል። ከዘንድሮው ተፈታኞች ውስጥ ከ3 በመቶ በላይ የሚሆኑት የእንግሊዝኛ ፈተናውን አልፈዋል። ባለፈው ዓመት 6 በመቶዎቹ ነበሩ ያለፉት።
"[ጥያቄዎቹን] ለመረዳት ረዥም ጊዜ ፈጅቶብኛል። ጽሑፎቹን መረዳት አስቸጋሪ ነበር... [አንዳንድ] መልሶች ተመሳሳይ ነበሩ። ስለዚህ እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ እርግጠኛ አልነበርኩም" ሲል የሃንዬንግ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነው ኢም ና-ሂ ተናግሯል።
የእንግሊዝኛ ቋንቋ ፕሮፌሰር የሆኑት ጁንግ ቻኢ-ኩዋን የእንግሊዝኛ ፈተናውን ከባድ ብሎ መጥራት ስህተት ነው ይላሉ።
"ጽሑፎቹ የግድ የማይቻል አይደሉም፣ ግን... በጣም ግራ የሚያጋቡ ናቸው። ትክክለኛውን ትምህርት ዋጋ ቢስ ስለሚያደርገው ሕመም ነው" ብለዋል በኢንቼዮን ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩት ፕሮፌሰር ጁንግ።
"መምህራን እንግሊዝኛ ከማስተማር ይልቅ የፈተና ዘዴዎች ላይ ያተኩራሉ… ብልሃቶቹን ካወቁ ውጤት ለማግኘት ሙሉውን ጽሑፍ ማንበብ እንኳን አያስፈልግዎትም" ብለዋል።
አንዳንዶች በጥያቄዎቹ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋሉ በርካታ አንቀጾች ከመጻሕፍት ውስጥ ተወስደው ከአውድ ውጭ ሆነው መቅረባቸውን ጠቁመዋል። ይህም ለመረዳት አስቸጋሪ ያደርገዋል ብለዋል።
ሌሎች ግን የፈተናው አስቸጋሪነት የታሰበውን ዓላማ ያንጸባርቃል ብለው ያምናሉ።
"የተማሪዎችን የማንባብ ብቃት እና በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚጠብቃቸውን ደረጃ መወጣት ይችሉ እንደሆነ ይለካል" ሲሉ ሴኡል በሚገኘው የሃንኩክ የውጭ ጥናት ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ ሥነ ጽሑፍ ፕሮፌሰር የሆኑት ኪም ሱ-ዮን ተናግረዋል።
የተመረጡት ጽሑፎች "የተወሰነ ደረጃ" ስላላቸው ፈተናው የመረዳት ክህሎቶችን ለመገምገም ያስችላል ሲሉ ለኮሪያ ታይምስ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በኅዳር ወር የሚካሄደው የደቡብ ኮሪያው ሱኑንግ ፈተና፤ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት መቻላቸውን ብቻ ሳይሆን የሥራ ተስፋቸውን፣ የገቢያቸውን እና የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን የሚወስን ለስምንት ሰዓታት በተከታታይ የሚሰጥ ነው።
ተማሪዎች ኮሪያኛ፣ ሒሳብ፣ እንግሊዝኛ፣ ማኅበራዊ እና የተፈጥሮ ሳይንስን ጨምሮ በተለያዩ ትምህርቶች ላይ ወደ 200 የሚጠጉ ጥያቄዎችን ይሞክራሉ።
ብዙ ታዳጊዎች ሕይወታቸውን ሙሉ ለእነዚህ ፈተናዎች ሲዘጋጁ ያሳልፋሉ። አንዳንዶቹ ከአራት ዓመት ዕድሜያቸው ጀምሮ "ክራም ትምህርት ቤቶች" በመባል ወደሚታወቁ የግል አስጠኚ ማዕከላት ይላካሉ።
ሱኑንግ ፈተና ብቻ ሳይሆን አገሪቱን ለአንድ ቀን ያህል ከመደበኛ እንቅስቃሴዋ የሚገታት አጋጣሚ ነው።
የግንባታ ሥራዎች ይቆማሉ፣ አውሮፕላኖች ቆመው ወታደራዊ ሥልጠና እንዲቋረጥ ይደረጋል። ይህም ለተመቻቸ የፈተና አካባቢን ለመፍጠር የሚደረግ ነው።
ፈተናው እአአ በ1993 መሰጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ12ቱ የሱኑንግ ኃላፊዎች መካከል አራቱ ብቻ የሦስት ዓመት የሥልጣን ዘመናቸውን አጠናቀዋል።
አብዛኛዎቹ በፈተና ጥያቄዎች ላይ በተፈጠሩ ስህተቶች ምክንያት ከሥልጣን ቢለቁም፣ ኦህ ግን በፈተናው አስቸጋሪነት ምክንያት ከሥልጣን የለቀቁት የመጀመሪያው ሰው ሆነዋል።















