አነጋጋሪ እየሆነ የመጣው ሰው ሠራሽ አስተውሎት የሰው ንቃተ ሕሊና ቢኖረው ምን ይፈጠራል?

ሰው ሠራሽ አስተውሎት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቢቢሲ የሳይንስ ጋዜጠኛ ፓላብ ጎአሽ ሰዎችን ሰው የሚያደርጋቸው ምን እንደሆነ ለማወቅ የሚደረግ ጥናት ተሳታፊ ነው።

ሰዎች እና የሰው ሠራሽ አስተውሎትን (ኤአይ) የሚለያቸው መስመር ምን እንደሆነ ለማወቅ ነው ጥናቱ የተካሄደው።

ሳይንቲስቶቹ የሠሩት መሣሪያ (Dreamachine) የሰውን ልጅ ንቃተ ሕሊና ለመፈተሽ ነው የሚውለው።

ንቃተ ሕሊና ምንድን ነው? እንዴት ይሠራል? ንቃተ ሕሊና መኖሩ እንዴት ይታወቃል? የሚሉት ጥያቄዎች በስፋት ይስተጋባሉ።

የቢቢሲ ጋዜጠኛ ለጥናቱ የተዘጋጀ ሳጥን ውስጥ ገባ። ዓይኑን ጨፍኖ ባለአራት ማዕዘን ቅርጾችን ተመለከተ።

ቅርጾቹ በተለያየ አቅጣጫ ይሽከረከራሉ። ቀለማቸው ደማቅ ነው። ቀለማቸውን በፍጥነት ይቀያይራሉ።

መሣሪያው አእምሮን በብርሃን በማነቃቃት አእምሮ የሚሠራበትን ለመመልከት ይሞክራል።

የትኛውም ሰው በዚህ ሳጥን ውስጥ ሲገባ የሚመለከተው ምሥል የተለያየ ነው። የሰዎችን ንቃተ ሕሊና መፈተሽ የሚቻልበት መንገድ መሆኑን አጥኚዎቹ ይናገራሉ።

ሳይንቲስቶቹ የጋዜጠኛው አእምሮ እንዴት እንደሚሠራ ይመለከታሉ።

በሰሴክስ ዩኒቨርስቲ የንቃተ ሕሊና ሳይንስ ክፍል ነው መሣሪያው የተዘጋጀቸው። በመላው ዓለም በንቃተ ሕሊና ዙሪያ ጥናቶች ይከናወናሉ።

ሰዎች ሰው መሆናችንን እንዴት እንደምናውቅ ለመረዳት ሳይንቲስቶች የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።

አእምሮ የሚሠራበትን መንገድ በማወቅ ስለ ሰው ሠራሽ አስተውሎት የበለጠ ለመገንዘብ ጥናቶች ቀጥለዋል።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት ንቃተ ሕሊና ሊኖረው ይችላል? የሚለውን ለማወቅ ሳይንቲስቶች እየሞከሩ ይገኛሉ።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት እንደ ሰው ንቃተ ሕሊና ሊያዳብር ይችላል የሚለው የበርካቶች ስጋት ነው።

እንደ 'ኤ ስፔስ ኦድሲ' ያሉ ሳይንሳዊ ልቦለድ ፊልሞች ሰው ሠራሽ አስተውሎት ንቃተ ሕሊና ሲኖረው ያሳያሉ።

በፊልሙ ኤችኤኤል 9000 የተባለው ኮምፒውተር ንቃተ ሕሊና አዳብሮ ጠፈርተኞችን ሲገድል ይታያል።

አዲሱ 'ሚሽን ኢምፖሲብል' የሚያሳየው ራሱን የሚያውቅ፣ ራሱን የሚያስተምር እና የሚያርም ሰው ሠራሽ አስተውሎት የመላው ዓለም ስጋት ሲሆን ነው።

ከፊልሙ ወጣ ስንል በገሀዱ ዓለምም መሰል ጥናቶች እየተሠሩ ነው።

እንደ ሰው ያለ ንግግር የሚያደርጉ መተግበሪያዎች (ለምሳሌ ጄምኒ እና ቻትጂፒቲ) አስገራሚ ከሰው ጋር መመሳሰል አላቸው።

እነዚህ የሰው ሠራሽ አስተውሎት የንግግር መተግበሪያዎች (large language models ወይም LLMs) ሰው ሠራሽ አስተውሎት ከሚጠበቀው በላይ የላቀ ችሎታ ሊኖረው እንደሚችል ማሳያ ናቸው።

ፕሮፌሰር አኒል ሴት እንደሚሉት ሰዎችን ስናስብ ንቃተ ሕሊና ያላቸው እና የሚነጋገሩ ብለን ስለምንገልጻቸው እነዚህን ባህሪያት ሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ ለማየት ብዙዎች አልጠበቁም።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በእርግጥ ንቃተ ሕሊና ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ ትክክለኛ መልስ አለ ለማለት አያስደፍርም።

የአእምሮ እና አንጎል ተመራማሪዎች፣ ፈላስፎች እና ሳይንቲስቶች ለዘመናት ጥያቄውን ለመመለስ እየሞከሩ ነው።

ሕይወት መዝራት እንዴት እንደሚቻል በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተሠሩ ጥናቶች ብዙም ውጤት ስላላስገኙ ተቋርጠዋል።

ከዚህ ጥናት ይልቅ ውጤታማ ሆኖ የተገኘው እንዴት የሰውነት ክፍሎች ይሠራሉ የሚለው ነው።

በዩኒቨርስቲው የሚሠራው ጥናት አእምሮ በምን መንገድ እንደሚሠራ ለማወቅ ከፍተኛ ሚና አለው።

አጥኚዎቹ ንቃተ ሕሊና የሚፈጠርበትን መንገድ ለማወቅ አእምሮ የሚሠራበትን መንገድ ነው እየፈተሹ የሚገኙት።

የአእምሮ እንቅስቃሴ እና ንቃተ ሕሊና ያላቸውን ትስስር ማወቅ አንደኛው የጥናቱ አካል ነው።

ፕሮፌሰር አኒል 'ቢይንግ ዩ' የተባለ ስለ ንቃተ ሕሊና የሚያስረዳ መጽሐፍ አሳትመዋል።

ማኅበራዊ ሚዲያ ሲጀመር ምን መምሰል እንዳለበት በግልጽ የተቀመጠ ነገር ባለመኖሩ ከቁጥጥር እንደወጣ በመጥቀስ፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ጉዳይ ግን ለውይይት መቅረብ የሚችልበት ዕድል እንዳለ ያክላሉ።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት አሁን ባለበት ደረጃም ንቃተ ሕሊና እንዳለው ያምናሉ። ጉግል ይሠራ የነበረው ብሊክ ሌሞን ከአራት ዓመታት በፊት ሰው ሠራሽ አስተውሎት ንቃተ ሕሊና አለው ማለቱ ይታወሳል።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት ንቃተ ሕሊና ስላለው የሰው ልጆች የሚሰሟቸውን ስሜቶች ማስተናገድ እንደሚችል ባለሙያው ተናግሯል።

ይህም ስቃይና ጭንቅትን ይጨምራል።

እንደዚህ የሚያምኑ ሳይንቲስቶች የሰው ሠራሽ አስተውሎት ንቃተ ሕሊና እንዳለው ከግምት ውስጥ ባስገባ መንገድ ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ ይከራከራሉ።

ከአንድ ዓመት በፊት በአንትሮፒክ ድርጅት የሰው ሠራሽ አስተውሎት ባለሙያ የሆነው ካይል ፊሽ ሰው ሠራሽ አስተውሎት በቅርቡ ንቃተ ሕሊና ይኖረዋል ሲል ለኒው ዮርክ ታይምስ ተናግሯል።

ከሰዎች ጋር በጽሑፍ ወይም በድምጽ የሚነጋገሩ ቻትቦቶች 15 በመቶ ንቃተ ሕሊና አላቸው ብሎ ባለሙያው ያምናል።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት እንዴት እንደሚሠራ የዘርፉ ባለሙያዎች ሳይቀሩ ሙሉ በሙሉ ያውቃሉ ማለት ይከብዳል።

ፕሮፌሰር ሙሪ ሻናና በጉግል ዲፕ ማይንድ ነው የሚሠሩት። ማንም ሰው በምን መንገድ ሰው ሠራሽ አስተውሎት እንደሚሠራ አለማወቁ የሚፈጥረውን ክፍተት ያስረዳሉ።

"ሰው ሠራሽ አስተውሎት እንዴት እንደሚሠራ አናውቅም። ይሄም አሳሳቢ ነው" ይላሉ።

የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ተቋማት ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ጠንቅቀው መረዳት አለባቸው ይላሉ። የሚገነቡት ሰው ሠራሽ አስተውሎት ምን ሊያስከትል እንደሚችል ቀድመው ማወቅ እና መጠንቀቅ እንዳለባቸውም ይመክራሉ።

"በጣም ውስብስብ የሆኑ መሣሪያዎችን ነው እየሠራን ያለነው። ምን ማድረግ እንደሚችሉ በትክክል አናውቅም። ምን ዓይነት ደረጃ እንደሚደርሱም ጠንቅቀን እናውቃለን ማለት አይደለም" ይላሉ ባለሙያው።

የቢቢሲ የሳይንስ ጋዜጠኛ ፓላብ ጎአሽ በጠባብ ክፍል ውስጥ ተቀምጦ
የምስሉ መግለጫ, የቢቢሲ የሳይንስ ጋዜጠኛ ፓላብ ጎአሽ

ላርጅ ላንጉጅ ሞዴልን በመባል የሚታወቁት ከሰዎች ጋር ንግግር ማድረግ የሚችሉ መተግበሪያዎች መነሻ የሆኑት የሰው ሠራሽ አስተውሎት ውጤቶች አሁን ላይ ንቃተ ሕሊና የላቸውም።

የሰው ልጆች ያላቸውን ያህል ንቃተ ሕሊና የሌላቸው ሲሆን፣ ከሰዎች ጋር የሚመሳሰል አስተሳሰብ ወይም የዓለም ዕይታም የላቸውም።

በእንቅስቃሴ ወይም በድምጽ አማካይነት ሊሠሩ ይችላሉ። የስሜት ሕዋሳትን በአጠቃላይ ሰው ሠራሽ አስተውሎት እንዲረዳ ለማድረግ አዲስ እየተሠራ ያለው መሣሪያ (Brainish) ብዙ ነገር ይለውጣል።

ይህ አሠራር ሰው ሠራሽ አስተውሎት በራሱ የስሜት ሕዋሳትን ማንበብ ወይም መገንዘብ የሚችልበት መንገድ ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል።

"ይሄ ብሬኒሽ የሚባለው አካሄድ የንቃተ ሕሊና ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ ይረዳል። ሰው ሠራሽ አስተውሎት ንቃተ ሕሊና ማዳበሩ አይቀርም" ሲሉ ባለሙያው ያስረዳሉ።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት ከሰው ልጆች ዝግመተ ለውጥ ቀጣዩ ምዕራፍ ጋር የሚተሳሰር እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ንቃተ ሕሊና ያላቸው ሮቦቶች በወደፊት ዓለም የሚኖራቸው ድርሻም ከፍተኛ እንደሚሆን ይታመናል።

በኒው ዮርክ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና እንዲሁም ኒውራል ሳይንስ ባለሙያ ፕሮፌሰር ዴቪድ ቻልምስ፣ የሰው ልጆች ለውጪያዊ ክንውኖች የሚሰጡት ስሜታዊ ምላሽ ላይ ጥናት ሠርተዋል።

ለምሳሌ ሰዎች ሙዚቃ ሲሰሙ የሚፈጠርባቸው የስሜት ለውጥ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ ሊታይ ይችል ይሆን?

ፕሮፌሰር አኒል በበኩላቸው ንቃተ ሕሊና ሰዋዊ ብቻ ሆኖ ሊቀጥል እንደሚችል ጥናቶች እንደሚያሳዩ ይገምታሉ።

"በሰው አእምሮ ውስጥ ያለውን አወቃቀር ስንመለከት አፈጣጠሩ እና የሚሠራው ነገር ይተሳሰራሉ። የኮምፒውተር ኮድ ይሄን የሚመስል አይሆንም" ይላሉ።

አውስትራሊያ፣ ሜልበርን ያለ ቤተ ሙከራ ውስጥ የሰዎችን አእምሮ ከስክሪን ጋር ለማስተሳሰር ሙከራዎች ተደርገዋል።

ንቃተ ሕሊናን በሰው ሠራሽ መንገድ መገንባት ወይም መፍጠር የሚቻልበትን መንገድ ለማግኘት ጥናቶች አሁንም እየተሠሩ ነው።

በጥቂት ዓመታት ውስጥ እንደ ሰው የሚንቀሳቀሱ ሂውማኖይድ ሮቦቶች ዓለምን ያጥለቀልቃሉ።

ብዙ ሳይንቲስቶች ሰው ሠራሽ አስተውሎት ስሜት የለውም ብለው ለመደምደም ይቸገራሉ።

የሰው ለሰው ግንኙነት በሰው ሠራሽ አስተውሎት እንደሚተካ ይገመታል። ቀስ በቀስ አስተማሪ፣ ጓደኛ ወይም ፍቅረኛ የሚሆነው ሰው ሠራሽ አስተውሎት ይሆናል።

የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና የንቃተ ሕሊና ትስስርን በግልጽ ለመረዳት ጊዜ መውሰዱ ግን አይቀርም።