ናሳ በጉጉት ሲጠበቅ በነበረው አዲስ ሪፖርቱ ስለ ዩፎዎች ምን አለ?

ናሳ ከመረመረው ምሥል አንዱ
የምስሉ መግለጫ, ናሳ ከመረመረው ምሥል አንዱ

ናሳ በመቶዎች የሚቆጠሩ ከዩፎ (ምንነታቸው ያልታወቀ በራሪ ነገሮች) ጋር የተያያዙ ሁነቶችን መርምሯል።

እነዚህ ሁነቶች ዩፎዎች ታይተዋል የተባሉባቸው ሲሆኑ፣ ናሳ ባደረገው ምርመራ ከሁነቶቹ ጀርባ ዩፎዎች ስለመኖራቸው ማስረጃ ባይኖርም ሙሉ በሙሉ ከዩፎች ጋር የሚገናኘው ዕድል የለም ብሎ መደምደምም አይቻልም።

ለረዥም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው የናሳ 36 ገጽ ሪፖርት ዩፎዎች ስለመኖራቸው ወይም ስላለመኖራቸው ተጨባጭ ማስረጃ አላቀረበም።

የናሳ ኃላፊ ቢል ኔልሰን እንዳሉት የአሜሪካ አየር ኃይል በጉዳዩ ዋና ባለድርሻ ቢሆንም መረጃ ይለዋወጣሉ።

የናሳ ዋና ዋና ግኝቶች ምንድን ናቸው?

ዩፎ የሚባሉትን ናሳ ዩኤፒ ሲል ነው የሚጠራቸው። ይህ መጠሪያ UAP ወይም በዝርዝሩ ‘Unidentified Anomalous Phenomena’ ነው።

ናሳ ከመረመራቸው ሁነቶች ጀርባ ዩፎዎች ስለመኖራቸው ማስረጃ ባያገኝም “እነዚህ ቁሶች መሬት ላይ ለመድረስ ሥርዓተ ፀሐይን ዞረዋል” ይላል።

ባዕድ አካላት ስለመኖራቸው ሪፖርቱ ማረጋገጫ ባይሰጥም ምንነቱ ያልታወቀ በእንግዳ አካላት (alien) የተሠራ ቴክኖሎጂ የመሬትን ምሕዋር እየዞረ ሊሆን የሚችልበት ዕድል እንዳለ ግን አልካደም።

የናሳ የሳይንስ ተልዕኮ ተባባሪ ኃላፊ ኒኮላ ፎክስ፣ በቂ መረጃ አለመገኘቱ የዓለማችን ምሥጢራዊው ጉዳይ አድርጎታል።

“ስለ ዩኤፒ አመጣጥና ተፈጥሮ አስተማማኝ ሳይንሳዊ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ በቂ መረጃ የለም” ብለዋል።

ናሳ ጉዳዩን የሚመረምር አዲስ ዳይሬክተር ሾሟል።

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሠራሽ አስተውሎት) እና ማሽን ለርኒንግ በመጠቀም ምርመራም ያደርጋሉ።

የሜክሲኮው ‘ዩፎ’

ከሰሞኑ በሜክሲኮ የዩፎዎች ናቸው የተባሉ ፎቶዎች ታይተዋል።

ራሱን የዩፎ ተመራማሪ የሚለው ጄሚ ማውሳን በምክር ቤት ውይይት ላይ ጥንታዊ “ሰው ያልሆኑ” እንግዳ አካላት ቅሪተ አካል አሳይቷል።

1,800 ዓመታት አስቆጥረዋል የተባሉት ቅሪተ አካሎቹ የተገኙት ፔሩ፣ ካሱኮ ውስጥ እአአ በ2017 ነውም ብሏል።

ሆኖም የእነዚህ ቅሪተ አካሎች ምሥሎች በሳይንሱ ማኅበረሰብ ጥያቄ አጭረዋል።

ከዚህ ቀደም በዚሁ ሰው ስለ እንግዳ አካላት የቀረበ ትንታኔ ሐሰተኛ ተብሎ ተፈርጇል።

የናሳ ሳይንቲስት ዶ/ር ዴቪድ ስፔርጋል ለቢቢሲ “የቅሪተ አካሎቹን ናሙና ለሳይንስ ማኅበረሰብ ያቅርብና ምንነታቸውን እንመርምር” ብለዋል።

ዩፎ ተብሎ የቀረበው
የምስሉ መግለጫ, የእነዚህ ቅሪተ አካሎች ምሥሎች በሳይንሱ ማኅበረሰብ ጥያቄ አጭረዋል

የዩፎ ተመራማሪዎች

የናሳ የጥናት ክፍል ምክትል ኃላፊ ዶ/ር ዳንኤል ኢቫንስ እንደሚሉት፣ ዩኤፒ የሚያጠኑ ባለሙያዎች ማስፈራራት ይደርስባቸዋል።

ናሳ አዲስ ለዘርፉ የሚሾመውን ዳይሬክተር ይፋ ከማድረግ የተቆጠበውም ለዚህ ይሆናል።

ስለ ዩኤፒ የተሻለ መረጃ ለማግኘት በበይነ መረብ ከበርካታ ሰዎች መረጃ ለመሰብሰብ (crowdsourcing) ናሳ አቅዷል።

በመላው ዓለም ያሉ ሰዎች መረጃ ማጋራት የሚችሉበት መተግበሪያ መዘርጋት አንዱ መንገድ ነው።