በጃፓኑ አየር ማረፊያ መቀስ በመጥፋቱ ምክንያት በርካታ በረራዎች ተሰረዙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፈው ቅዳሜ በአንድ የጃፓን አየር ማረፊያ የነበሩ ሊካሄዱ የነበሩ 36 በረራዎች ሲሰረዙ 201 ደግሞ እንዲዘገዩ ግድ ሆኗል።
ይህ የሆነው ወደ አውሮፕላኑ መሣፈሪያ አካባቢ ከሚገኝ ሱቅ አንድ መቀስ መጥፋቱን ተከትሎ ነው።
ባፈለው ቅዳሜ ነው የሀካይዶ ኒው ቺቶዜ አየር ማረፊያ የደኅንነት ሰዎች የሀገር ውስጥ በረራዎቹን ለሁለት ሰዓት ተኩል ያክል እንዲዘገዩ ያደረጉት። በዚህ ምክንያት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአየር ማረፊያው ተጎልተው ቆይተዋል።
በአየር ማረፊያው መጠባበቂያ ሥፍራ የነበሩ መንገደኞች ድጋሚ እንዲፈተሹ መደረጉን ተከትሎ ግርግር እና ሁከት ተከስቷል።
የአየር ማረፊያው ባለሥልጣናት የጠፋውን መቀስ ለማግኘት ብዙ አሰሳ ካደረጉ በኋላ በበነጋው እዚያው ጠፋ የተባለበት ሱቅ ውስጥ ተገኝቷል።
ምንም እንኳ መቀሱ ቅዳሜ ዕለት ባይገኝም አየር ማረፊያው ከሰዓታት ቆይታ በኋላ በረራዎችን እንደገና ለማስጀመር ተገዷል።
የኒው ቺቶዜ አየር ማረፊያ አስተዳዳሪ የሆነው ሀካይዶ አየር ማረፊያ ሰኞ ዕለት በለቀቀው መግለጫ መቀሱ እሑድ ዕለት በሱቁ ሠራተኛ አማካይነት ተገኝቷል ብሏል።
ባለሥልጣናቱ መግለጫ ለመስጠት ለምን እንደቆዩ ሲያስረዱ የጠፋው መቀስ እና የተገኘው መቀስ ተመሳሳይ መሆናቸውን ለማጣራት ጊዜ ስለወሰደባቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
አብዛኛዎቹ መቀስ በመጥፋቱ ምክንያት በረራቸው የዘገየባቸው መንገደኞች ዓመታዊውን የጃፓን ቦን በዓል አክብረው ወደቤታቸው እየተመለሱ የነበሩ ናቸው።
“[ከመጠበቅ ውጭ] ምንም አማራጭ ያለን አይመስለኝም” ሲሉ አንድ መንገደኛ ለአካባቢው መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
አንድ ሌላ መንገደኛ ደግሞ “ዘንድሮ በጣም ብዙ ነገር ያስጨንቃል። ማለቂያ የለውም። ቤቴ እስክስደርስ ድረስ ደኅንነት አይሰማኝም” ብለዋል።
የመሬት፣ መሠረተ-ልማት፣ ትራንስፖርት እና ቱሪዝም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ለሀካይዶ አየር ማረፊያ በላከው መልዕክት ጉዳዩን ምርመር እንዲደረግበት እና ድጋሚ እንዳይከሰት ጥንቃቄ እንዲደረግ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
“ሱቁ ውስጥ ባለፈው የሰው ኃይል እጥረት እና የአስተዳደር ሲስተም ችግር ምክንያት ይህ እንደተከሰተ እናውቃለን” ብሏል ሀካይዶ አየር ማረፊያ።
በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ሐሳባቸውን የሰጡ ሰዎች የአየር ማረፊያውን እርምጃ አድንቀው በጃፓን አየር ትራንስፖርት ደኅንነት ያላቸውን መተማመን ፅፈዋል።
“ይህ ክስተት የጃፓን አቪየሽን ደኅንነትን የሚያሳይ ነው” ሲሉ አንደ የኤክስ ተጠቃሚ ተናግረዋል።
ኒው ቺቶዜ በጃፓን ከሚገኙ እጅግ በርካታ በረራዎችን ከሚያስተናግዱ አየር ማረፊያዎች አንዱ ነው። አልፎም በዓለማችን ሁለተኛው በርካታ በረራ የሚካሄድበት የቶኪዮ-ሳፖሮ መንገድ መገኛም ነው ይላል ኦኤጂ የተሰኘው የአቪየሽን ተንታኝ ኩባንያ።
በአውሮፓውያኑ 2022 ከ15 ሚሊዮን በላይ መንገደኞች አየር ማረፊያውን ተጠቅመዋል።












