ኢትዮጵያ ለምን የአሰብ ወደብን ልትጠቀም አልቻለችም?

የፎቶው ባለመብት, Eritrea Media Network
በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ቀንድ ዲፕሎማሲያዊ እና የፀጥታ ስጋት እንዲሁም ውጥረቶች ሰፍነው ይታያሉ። ከእነዚህም መካከል በኢትዮጵያ ወደብ የምግኘት ፍላጎት ምክንያት የተቀሰቀሰው ውጥረት አንዱ ነው።
የወደብ ተደራሽነት እና የወደብ አገልግሎት ጉዳይ ከአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ ለሆነችው ኢትዮጵያ ዋነኛ ፍላጎት ከመሆኑ አንጻር በአካባቢው ይፋ የወጣ መነጋገሪያ ከሆነ ሰነባብቷል።
እያደገ ያለው ከ120 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ሕዝቧ ፍላጎት መጨመር እና የጂቡቲ የወደብ አገልግሎት መወደድ ኢትዮጵያ ተጨማሪ የባሕር በር ተረዳሽነት እና ወደብ ለማግኘት ጥረት እያደረገች ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ የባሕር በር እና የወደብ አገልግሎት ባለቤት ለመሆን ያላትን ፍላጎት በማንጸባረቅ የሰጧቸው መግለጫዎች በአንዳንድ የቀጠናው አገራት ዘንድ ስጋት ፈጥሯል።
የኤርትራ እና የሶማሊያ ወደቦች (በሶማሌላንድ በኩል) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዐይናቸውን ካሳረፉባቸው የባሕር መተላለፊዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
የአሰብ ወደብ ከመቶ ዓመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ የኢትዮጵያ ዋና የንግድ መተላለፊያ ሆኖ አገልግሏል። የኤርትራ ፍላጎት 98 በመቶ የሚሆነው የሚገባውም በዚህ ወደብ በኩል ነው።
በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የድንበር ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ንግዷ ከሞላ ጎደል የጂቡቲን ወደብን ስትጠቀም ቆይታለች። የጂቡቲ ወደብ በዓመት ከ5.8 ሚሊዮን ቶን በላይ ደረቅ ጭነት እና ወደ 300,000 የሚጠጉ ኮንቴይነሮችን ያስተናግዳል።
አሰብ ‘ነጻ ወደብ’ ለኢትዮጵያ
እስከ 1995 (እኤአ) ድረስ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው በአሰብ በኩል የሚገቡ እና የሚወጡ ዕቃዎች የኢትዮጵያ እንደነበሩ ሰነዶች ያመለክታሉ። በተጨማሪም ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆነው በምጽዋ ወደብ የሚገባና የሚወጣ ጭነት የኢትዮጵያ ነበረ።
“የአሰብ ወደብ የኢትዮጵያ ነፃ ወደብ ነበር፣ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ነበረው፣ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ እና ከኢትዮጵያ የሚላኩ ዕቃዎች ከኤርትራ ጉምሩክ ቁጥጥር ውጪ ነበሩ” ሲል በአውሮፓውያኑ 1995 የወጣ የአይኤምኤፍ ዘገባ ያመለክታል።
በተጨማሪም ሁለቱ አገራት ባደረጉት ስምምነት መሠረት በአሰብ የሚገኘው የነዳጅ ማጣሪያ በኢትዮጵያ ነዳጅ ኮርፖሬሽን እየተዳደረ ድፍድፍ ነዳጅ ያጣራ ነበር።
ኤርትራም የሚያስፈልጋትን ነዳጅ ከኮርፖሬሽኑ በብር ትገዛ ስትገዛ በአንፃሩ ለምትሰጠው የትራንስፖርት እና የወደብ አገልግሎት ከኢትዮጵያ በብር ይከፈላት ነበር።
ነገር ግን ለ20 ዓመታት በዘለቀው ጦርነት እና ባስከተለው ፍጥጫ ምክንያት የአሰብ ወደብ አገልግሎት የዓለም ባንክ እንደሚለው ከ1998 (እአአ) ወዲህ “ያበቃለት” ጉዳይ ሆኗል።
የየመን ጦርነት እና አሰብ
እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በየመን የተፈጠረው ቀውስ በአጠቃላይ በኤርትራ በተለይም ከየመን የባሕር ዳርቻ ብዙም በማይርቀው የአሰብ ወደብ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን ጨምሮ በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ወታደራዊ ጥምረት በሰሜናዊ የመን ለሚካሄደው የጦርነት እንቅስቃሴ የድጋፍ ወደብ ያስፈልገው ነበር።
ኤርትራ ለወታደራዊ ጥምረቱ ድጋፍ በመስጠቷ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የአሰብ ወደብን እንድትጠቀም እና የጦር ካምፕ እንድትገነባ ፈቅዳ የነበረ ሲሆን፣ በ2021 ኤምሬትስ ካምፑን ለቃ እንደወጣች ይነገራል።
የአሰብ ወደብ በቀይ ባሕር ደቡባዊ ጫፍ ካለው ፈታኝ የፀጥታ ችግር ብዙም የራቀ አይደለም። በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነትም በቀይ ባሕር የሚያልፉ መርከቦችን ደኅንነት ስጋት ከፍ አድርጎታል።
የየመን ሁቲ ታጣቂዎች በዚህ ወሳኝ ዓለም አቀፍ የንግድ መስመር በኩል በሚያልፉ መርከቦች ላይ ጥቃት እየፈፀሙ ከፍተኛ ስጋት እና መስተጓጎል ሲፈጥሩ መቆየታቸው ይታወቃል።
አሰብ ከስምምነት በኋላ
በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል ከ20 ዓመታት በላይ የዘለቀውን ፍጥጫ በአሥመራ እና በጅዳ በተፈረሙ ስምምነቶች መቋጨቱ ይታወሳል።
ብዙም ሳይቆይ ኢትዮጵያን እና ኤርትራን ከሚያገናኙት አራት መንገዶች አንዱ የሆነው በአፋር ክልል ወደ አሰብ የሚወስደው የቡሬ - ደባይሲማ (አሰብ) መስመር የተከፈተ ሲሆን፣ ከትግራይ ክልል ጋር የሚዋሰኑ መንገዶች በሙሉ ለጥቂት ወራት ተከፍተው ሲዘጉ የአሰብ መንገድ ለአንድ ዓመት ያህል ክፍት ሆኖ ቆይቶ ነበር።
የድንበር መተላለፊያዎቹ ከተዘጉ ከአንድ ዓመት በኋላ ኤርትራ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን የተሰለፈችበት የትግራይ ጦርነት ተቀሰቀሰ።
ነገር ግን የአሰብ መንገድ ከትግራይ ርቆ በአፋር በኩል የሚያልፍ ከመሆኑ በተጨማሪ የመንገድ ጥገና እየተከናወነ መሆኑ፣ እንዲሁም የኤርትራ ባለሥልጣናት ወደቡ መደበኛ ሥራውን ለመጀመር ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸው ተገልጾ ነበር።
በተጨማሪም ከአሰብ ወደ አዲስ አበባ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር እንደሚዘረጋ የሚገልጹ ዘገባዎች ሲወጡ የነበረ ቢሆንም ወደቡ ለምን ለኢትዮጵያ አገልግሎት እንዲውል እንዳልተከፈተ አልታወቀም።
ከአገራቱ መሪዎች ጀምሮ የተለያዩ ባለሥልጣናት የወደብ አግልግሎቱን በፍጥነት ለማስጀመር ፍላጎት እንዳለ እና አስፈላጊው ሥራ በፍጥነት እንደሚከናወን በተደጋጋሚ ሲገልጹም ቆይተው ነበር።
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭ ለቢቢሲ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የጅቡቲ ወደብን አንዳንድ አገልግሎቶች በብድር ልታገኝ ብትችልም፣ በየጊዜው እየተሻሻለ እና እየተስፋፋ የመጣውን ወደብ ለመጠቀም በየዓመቱ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ትከፍላለች።
ምንጩ እንደሚሉት “በጅቡቲ ከምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ባነሰ መጠን የአሰብ ወደብ አገልግሎት የሚያስገኝ ስለሆነ ለኢትዮጵያ ትልቅ ጥቅም ነበረው” ይላሉ።
የኢትዮጵያ የወደብ ፍላጎት
ለሁለት ዓመታት በተካሄደው የትግራይ ጦርነት ላይ በጋራ ቆመው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና በፕሬዝዳንት ኢሳያስ መካከል የነበረው ግንኙነት ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ መቀዛቀዙ ይነገራል።
ሁለቱ አገራት የጀመሩት ግንኙነታቸውን የማጠናከር እርምጃ የት እንደደረሰ ምንም ሳይሰማ ከመቆየቱ በተጨማሪ የአገራቱ ባለሥልጣናትም ምን እየሠሩ እንደሆነ አይታወቅም። ከመጪው መስከረም አጋማሽ በኋላ ደግሞ የቀረው የአገራቱ የግንኙነት መስመር የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ እንዲቆም በኤርትራ ተወስኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቅርቡ ስለባሕር በር እና ስለወደብ ያደረጉት ንግግር እና ያሳዩት ፍላጎት የኤርትራ ባለሥልጣናትን የሚያስደስት አይመስልም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን የወደብ ፍላጎትን በተመለከተ “የቀይ ባሕርን ጉዳይ ሳናነሳ በሰላም ቆይተናልና አሁን ለምን ዝም አንልም? ከኤርትራ ጋር እንዳንጋጭ ቢቀርብንስ? ከጅቡቲ ጋር ብንጋጭስ የሚል ስጋት ያለባቸው ሰዎች አሉ” ብለው ነበር።
ለዚህ ጥያቄ መነሳት እንደ ምክንያት የጠቀሱት እየጨመረ የመጣው የኢትዮጵያ የሕዝብ ብዛት የባሕር መተላለፊያ ስለሌለው “የመልክዓ ምድር እስረኛ” ሆኖ መቀጠሉን አመልክተው ነበር።
ኤርትራ ነጻ አገር መሆኗን ተከትሎ ወደብ አልባ የሆነችው ኢትዮጵያ ባለፉት 35 ዓመታት ውስጥ የሕዝብ ብዛቷ እና የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴዋ በከፍተኛ መጠን አድጓል። ይህም የወደብ አጠቃቀሟን እና ፍላጎቷን ከፍ አድርጎታል።
በኢህአዴግ የአስተዳደር ዘመን የወደብ አስፈላጊነት ዝቅ ከመደረጉ ባሻገር ኢትዮጵያ የወደብ ባለቤት የመሆኗ ዕድል የተዘጋ ጉዳይ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል።
ነገር ግን አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የወደብ ጉዳይን ከዋነኛ አጀንዳቸው መካከል አድርገው መያዛቸውን መረዳት አዳጋች አይደለም።
ለዚህም ምላሽ ከሶማሊያ ነጻ አገር መሆኗን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር ብዙ የተባለለት የወደብ አገልግሎትን የተመለከተ የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙ ይታወቃል።
ከዓመታት በፊት የአሰበ ወደብን ለመጠቀም የተጀመረው እንቅስቃሴ ስለመቋረጡ ወይም እየተከናወነ ስላለ ሥራ ከሁለቱም ወገን በኢትዮጵያ የሚገኙ የባህር ትራንስፖርት ባለስልጣናት እና ሌሎች የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ኤርትራ ምን ልትጠቀም ትችላለች?
ኢትዮጵያ ከአሰብ ያጣችውን አገልግሎት ከጅቡቲ ወደብ እና ካሻሻለችው የአየር ትራንስፖርት ማግኘት ብትችልም፣ ኤርትራ ሩብ ክፍለ ዘመን ለሚጠጋ ጊዜ ገቢዋን ሙሉ በሙሉ አጥታለች።
ለዘርፉ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ኤርትራ ከሁለቱም ወደቦች ብቸኛ ተጠቃሚ ልትሆን ከምትችለው ኢትዮጵያ በዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር ገደማ ልታገኝ ትችላለች ይላሉ።
“ኤርትራ ከሁለቱም ወደቦች በዓመት እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት ትችላለች። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንደታሰበው ቢያድግ የኤርትራ ገቢም በዚያው መጠን ይጨምራል” ሲሉ አገራቱን በቅርበት የሚከታተሉ ስማቸውነ እነዲጠቀስ ያለፈለጉ ባለሙያ ይናገራሉ።
ከአስር ዓመታት በፊት የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው እያደገ ያለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 12 ወደቦች እንደሚያስፈልገው ያመለክታል። የኤርትራ ወደቦች ደግሞ ለኢትዮጵያ ቅርብ በመሆናቸው ለሁለቱም አገራት ትልቅ ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው።
በተለይ የአሰብ ወደብ ከታደሰ እና ማስፋፋት ከተቻለ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም አቀፍ አገልግሎትም ሊውል ይችላል።
እነዚህ አገልግሎቶች በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር እና በማጓጓዣ እና በመጋዘን አገልግሎታቸው ገቢ በማስገኘት ቀጣይነት ያለው ቀጥተኛ የኢኮኖሚ ጥቅሞችን እንደሚሰጡ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
እንደ የባሕር፣ የብስ እና የአየር ትራንስፖርት ከወደብ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች ለንግድ እና ለሠራተኞች ተጨማሪ ዕድሎችን ይፈጥራሉ።
የአሰብ ወደብ ሁኔታ
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በመስከረም 2013 (እአአ) ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ወደቦች አሉን ብለን መናገር የሚቻል አይደለም” በማለት የምጽዋ እና የአሰብ ወደቦች መስፋፋት እንዳለባቸው ተናግረው ነበር።
“አሰብ መልማት እና ማደግ ያለበት ወደብ ነው. . . አሰብ ካደገ ኢትዮጵያን ማገልግል ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው እና ለዓለም አቀፍ አገልግሎት ሊውል ይችላል . . . ስትራተጂካዊ ፕሮጀክት ነው . . . ለነገ የሚቆይ አይደለም።”
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሆነው ዲፒ ወርልድ ለኤርትራ ወደቦች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ለመቀየር እና የወደቦቹን ብቃት ለማሻሻል ጥገና እያካሄደ እንደሆነ ከዓመታት በፊት ገልጾ ነበር።
የአሰብ ወደብ 10.97 ሜትር ጥልቀት እና 210 ሜትር ርዝመት ያላቸው ሰባት ትላልቅ የመርከብ ማረፊያዎች አሉት።
ወደ 385,930 ሜትሪክ ቶን የሚጠጋ ቁሳቁሶችን የማስተናገድ አቅም ያለው ይህ ወደብ ከ275,320 ካሬ ሜትር በላይ የሆነ የማከማቻ ቦታንም ያጠቃለለ ነው።
አገልግሎቱን ለማሳለጥም ዓለም አቀፍ የስልክ፣ የቴሌክስ እና የፋክስ ግንኙነት እንደነበረው በ2013 (እአአ) የወጣ የኤርትራ መንግሥት ሪፖርት ያሳያል።
በአለም ባንክ ድጋፍ ወደቡን ለማደስ እና ለመጠገን ጥረት ቢደረግም ከኢትዮጵያ ጋር የተፈጠረው አለመግባባት ወደቡ ባዶውን እንዲቀር እንዳደረገው ባንኩ ገልጿል።












