ጠፍታ የነበረችው የአሜሪካዊው ቢሊዮነር የልጅ ልጅና ወራሽ አስከሬኗ ተገኘ

የአሜሪካዊ ቢሊዮነር የልጅ ልጅና ወራሽ ኤሊዛ ፍሌቸር

የፎቶው ባለመብት, Memphis Police department

ጠፍታ የነበረችው የአሜሪካዊ ቢሊዮነር የልጅ ልጅና ወራሽ ኤሊዛ ፍሌቸር አስከሬኗ ሰኞ እለት እንደተገኘ የቴኔሲ ፖሊስ አስታወቀ።

የሁለት ልጆች እናት የሆነቸው የ34 አመቷ ኤሊዛ የቢሊዮነር የልጅ ልጅና ወራሽም ነበረች ተብሏል።

በአካባቢው በመምህርነት ታገለግል የነበረችው ኤሊዛ በሜምፊስ ዩኒቨርስቲ አካባቢ አካላዊ እንቅስቃሴ በምታደርግበት ወቅትም ነው ታፍና የተጠለፈችው።

ክሌዎታ አብስተን የተባለ ግለሰብ ኤሊዛን በመጥለፍ እና በመግደል ወንጀል ተከሷል።

ቤተሰቦቿ አስከሬኗ ከተገኘ በኋላም “ልባችን ተሰብሯል፤ ሃዘን ውስጥ ነን” ሲሉ መግለጫ አውጥተዋል።

“ሊዛ ለቤተሰቦቿ፣ ለጓደኞቿ፣ ለስራ ባልደረቦቿ፣ ለተማሪዎቿ፣ ለወላጆች፣ በቤተ ክርስቲያኗ ለሚያገለግሉ፣ ለሚያውቋት ሁሉ ደስታን የምታመጣ ነበረች” ብለዋል።

አክለውም “ምን ያህል ልዩ እንደነበረች የምናስታውስበትና የምንዘክርበት እንዲሁም ለተጨነቁላት ሁሉ የምንደግፍበት ጊዜው አሁን ነው” በማለት መግለጫው አስፍሯል።

በአካባቢው ማሀረሰብ ዘንድ ስመ ጥር የነበረችው ኤሊዛ የሟቹና የቢሊየነሩ ጆሴፍ ኤርጊል የልጅ ልጅ ነበረች ። ከቢሊየነርታቸውም በተጨማሪ በበጎ አድራጎታቸው ይታወቁ የነበሩት ጆሴፍ የኮምፒውተር ግብዓቶች ኩባንያቸው ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመትና ከ5 ሺህ በላይ ሰዎችን ቀጥሯል።

ኤሊዛ ከቤተሰቦቿ ንግድ ይልቅ ማስተማርን በመምረጥ በሴንት ሜሪ ኤፒስኮፓል በተሰኘው የመዋዕለ ህጻናት በመህርነት ታገለግል ነበር።

ባለፈው ሳምንት አርብ አስር ሰዓት አካባቢ የጠፋቸውን ኤሊዛ በአካባቢው የተቀረጸ ቪዲዮ እንደሚያሳየው አንድ ግለሰብ ታግሎ አፍኖ ወደ አንድ ጥቁር መኪና አስገድዶ ሲያስገባት መታየቱን የፖሊስ ሰነዶች ጠቁመዋል።

ከማለዳ የአካል እንቅስቃሴዋ አለመመለሷን ተከትሎ ቤተሰቦቿ እንደጠፋች ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን ቤተሰቦቿም ያለችበትን ለጠቆመ የ50 ሺህ ዶላር ሽልማትም አዘጋጅተው ነበር።

የሜምፊስ ፖሊስ ዲፓርትመንት ሰኞ እለት 11 ሰዓት አካባቢ አስከሬኗን ማግኘታቸውን ገልጸዋል።