አዲሷ የዩናይድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ወዳጆቻቸውን በቁልፍ የካቢኔ ቦታዎች ላይ ሾሙ

ሊዝ ትረስ

የፎቶው ባለመብት, NO 10

ቦሪስ ጆንሰንን ተክተው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትርነት መንበሩን የተረከቡት ሊዝ ትረስ ባደረጉት ከፍተኛ የካቢኔ ሹመት ለቅርብ አጋሮቻቸው ቁልፍ ቦታዎችን ሰጡ።

ክዋሲ ክዋርቴንግ ቻንስለር ሆነው ሲሾሙ፣ ጀምስ ክሌቨርሊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነዋል። ሱዌላ ብሬቨርማን ደግሞ ፕሪቲ ፓቴልን ተክተው የአገር ውስጥ ሚኒስትርነቱን ቦታ ተረክበዋል።

ከትረስ የቅርብ ጓደኞች አንዷ ሆኑት ቴሬዝ ኮፊ የጤና ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሰይመዋል።

አዲሱ ካቢኔያቸው ትረስ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣኑን ከተረከቡ በኋላ የመጀመሪያቸው ከሚሆነው የጥያቄና መልስ ጊዜያቸው በፊት ይሰበሰባል ተብሏል።

ካቢኔው በውድድሩ የተሸነፉትን ተቀናቃኛዋን ሪሺ ሱናክን ከደገፉት መካከል አንዳቸውም እንዲቀጥሉ አልተደረገም። ዶሚኒክ ራብ፣ ግራንት ሻፕስ፣ ጆርጅ ኤስቲስ እና ስቲቭ ባርክሌይ ወደ ቀድሞ ቦታቸው ተመልሰዋል።

የትረስ ቃል አቀባይ ለውጦቹ የወግ አጥባቂውን ፓርቲ “አንድ እንደሚያደርገው” ተናግረዋል። ለአምስት የተቀናቃኛቸው አመራሮችም ሹመት ሰጥተዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ከአራቱ ከፍተኛ “የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የኃላፊነት ቦታዎች” ከሚባሉት የጠቅላይ ሚኒስትር፣ የቻንስለር፣ የአገር ውስጥ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ቦታዎች አንዳቸውም በነጮች ወንዶች አልተያዙም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አዲሷ ጠቅላይ ሚኒስትር ከአገር መሪ ጋር የመጀመሪያ ስልክ ልውውጣቸውን ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ጋር አድርገዋል። በዚህም አገራቸው ለዩክሬን ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደምትሰጥ ቃል ገብተዋል።

ትረስ ዩክሬንን እንዲጎበኙ የቀረበላቸውን ግብዣም በመቀበል ደስተኛች መሆናቸው ተገልጿል።

በኋላም የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን አነጋግረዋል። ዩናይትድ ኪንግደም ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በሰሜን አየርላንድ የድኅረ-ብሬግዚት የንግድ ሕጎች ላይ ከስምምነትመድረሳቸው ስላለው አስፈላጊነት ተወያይተዋል።