ጦርነት እንዲቆም የሰላም ጥሪ ለማቅረብ የተጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ታገደ

የፎቶው ባለመብት, CARD
በአገሪቱ ባሉ በርካታ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲቆም የሰላም ጥሪ ለማስተላለፍ የተጠራ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳይካሄድ በፀጥታ ኃይሎች መታገዱ ተገለጸ።
ጋዜጣዊ መግለጫውን ከጠሩት 35 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የመብቶች እና የዴሞክራሲ እድገት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ በፍቃዱ ኃይሉ፤ መግለጫ ሊሰጥበት በነበረው ሆቴል ሲቪል የለበሱ የመንግሥት የፀጥታ ኃይል አባላት ነን ያሉ ግለሰቦች መግለጫውን መስጠት አይቻልም በማለት ከልክለዋል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“የትኛው የመንግሥት አካል ክልከላውን እንደፈጸመ አልተነገረንም። እንዲሁ በጥቅሉ ይህን መግለጫ መሰጠት የለባችሁም የሚል መልዕክት ብቻ ነው የተላለፈልን” ብለዋል አቶ በፈቃዱ።
ቢቢሲ ስለጉዳዩ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ምላሽ ጠይቆ ኮሚሽኑ ስለክልከላው የሚያውቀው ነገር እንደሌለ የገለጸ ሲሆን፣ የፌደራል ፖሊስ ምላሽን ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ግን አልተሳካም።
የመንግሥት የፀጥታ ሰዎች ነን ያሉት ግለሰቦች ጋዜጣዊ መግለጫውን ለመዘገብ በሆቴሉ ተገኝተው የነበሩ ጋዜጠኞችም መግለጫው እንደማይካሄድ በመግለጽ እንዲያሰናብቱ ለሆቴሉ ሠራተኞች ተናግረዋል ሲሉ አቶ በፍቃዱ ተናግረዋል።
“ለማካሄድ አቅደን የነበረው የአደባባይ ስብሰባ ስላልነበረ ቀድመን ማሳወቅ አይጠበቅብንም ነበር” ያሉት አቶ በፍቃዱ፤ ወደፊት ማን ለምን እንደከለከለን ለማጣራት እንሞከራለን ብለዋል።
35ቱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሊሰጡት የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ መከልከሉን ተከትሎ “ይህ ዓይነቱ አሠራር የሕግ የበላይነትን የሚፃረር ከመሆኑ ባሻገር የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለሰላም ሊጫወቱ የሚገባቸውን ድርሻ ይነፍጋል” በማለት ደርጊት እንዲታረም ጠይቀዋል።
አስቸኳዩ የሰላም ጥሪ!
35ቱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በአንድ ስፍራ ተገኝተው ሊያስተላልፉት የነበረውን መልዕክት በጋዜጣዊ መግለጫ አሰራጭተዋል።
በዚህም በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልል የተዛመተው ጦርነት አገሪቷን እና ሕዝቧን ለሰብዓዊ እና ቁሳዊ ከፍተኛ ኪሳራ ዳርጓል ብለዋል ሲቪል ማኅብራቱ።
አክለውም ተፋላሚ ወገኖች ለሰብዓዊነት ሲባል የተኩስ አቁም ማድረጋቸው እና ለሰላም ድርድር ፍላጎት ማሳየታቸው ትልቅ ተስፋ እንዲሰንቁ አድርጓቸው እንደነበር አመልክተው፣ ይሁንና ጦርነቱ ዳግም ማገርሸቱ በእጅግ እንዳሳዘናቸው ግልጸዋል።
ከሰሜኑ ጦርነት ባሻገር በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በአንዳንድ የደቡብ ክልል አካባቢዎች ግጭቶች እየተካሄዱ ነው ያሉት ማኅበራቱ፤ ግጭቶቹ በሕይወት የመኖር መብትን ጨምሮ መሠረታዊ የዜጎችን መብቶችን ከመንፈጋቸው ባሻገር የአገርን ኅልውናን የሚፈታተኑበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል ብለዋል።
ስለሆነም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያለው ጦርነት እና በሌሎችም አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች በአስቸኳይ ቆመው፤ “ሐቀኛ፣ ሰላማዊና የግጭቶቹ ተሳታፊ አካላትን በሙሉ ያካተቱ የእርቅ ንግግሮች እንዲጀመሩ” ጠይቀዋል።
በትግራይ እና ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች የተቋረጡ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች በአፋጣኝ እንዲጀመሩ እና ሰብዓዊ ዕርዳታ ያለ እንቅፋት እንዲደርስ የጠየቁ ሲሆን፤ በጦርነት ወቅት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ያደረሱ አካላት ላይ ምርመራ ተደርጎ የተጠያቂነት እርምጃ ይወሰድ ሲሉ ጠይቀዋል።
ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለአምስት ወራት ያህል ጋብ ብሎ ከቆየ በኋላ ከሁለት ሳምንት በፊት ዳግም ተቀስቅሷል።
ቀደም ባለው ጦርነት ከፍተኛ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመትን ያስከተለው ግጭት፣ ዳግም ወደ ደም መፋሰስ እንዳያመራ መንግሥትና የትግራይ ኃይሎች በአስቸኳይ ድርድር እንዲጀምሩ ጥሪ እያደረጉ ነው።












