ሰሜን ኮሪያ የጦር መሳሪያ ለሩሲያ እያቀረበች መሆኗን ሪፖርቶች ጠቁሙ

የፎቶው ባለመብት, RUSSIAN DEFENCE MINISTRY
በዩክሬን ላይ በፈጸመችው ወረራ ምክንያት ምዕራባውያን ጠንካራ ማዕቀብ የጣሉባት ሩሲያ የጦር መሳሪያ ፍላጎቷን ለማሟላት ፊቷን ወደ ሰሜን ኮሪያ ስለማዞሯ ሪፖርቶች ጠቆሙ።
ኒው ዮርክ ታይምስ የአሜሪካ የደኅንነት መረጃዎችን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ፣ ሞስኮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከባድ ተተኳሾችን እና ሮኬቶችን ከፒዮንግያንግ ገዝታለች።
የኒው ዮርክ ታይምስ ዘገባ ሩሲያ ከሰሜን ኮሪያ ገዝታለች የተባለው ዝርዝር የጦር መሳሪያ አይነት እና ብዛት አልተጠቀሰም።
አንድ በስም ያልተጠቀሱ የአሜሪካ ባለሥልጣን ጦርነቱ በተራዘመ መጠን ሩሲያ ተጨማሪ የጦር መሳሪያዎችን ከሰሜን ኮሪያ ለመግዛት ትገደዳለች ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት ደግሞ ሞስኮ የመጀመሪያ ዙር ሰው አልባ አውሮፕላን ከኢራን ስለመቀበሏ የሚጠቁሙ መረጃዎች ወጥተው ነበር።
በተመሳሳይ በምዕራባውያኑ ከፍተኛ ማዕቀብ ስር የሚገኙት ሰሜን ኮሪያ እና ኢራን ከዩክሬን ጦርነት መጀመር ወዲህ ከሞስኮ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ማጠንከርን መርጠዋል።
ሰሜን ኮሪያ፣ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ እርምጃ እንድትወስድ ያስገደዱት ምዕራባውያን ናቸው የሚል የጸና አቋም ያለት ሲሆን፣ ከአንድ ወር በፊት ሞስኮ በኃይል የያዘቻቸው የዩክሬን ዶኔስክ እና ሉሃንስክ ግዛቶች የሞስኮ አካል ናቸው ስትል እውቅና ሰጥታለች።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሁለቱ አገራት “አጠቃላይ እና ገንቢ የሁለትዮች ግንኙነታቸውን” ያጠናክራሉ ስለማለታቸው የሰሜን ኮሪያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ለአሶሺየትድ ፕሬስ ሲናገሩ ሩሲያ የጦር መሳሪያ ፍለጋ ፊቷን ወደ ሰሜን ኮሪያ ማዞሯ፤ በተጣለባት ማዕቀብ ምክንያት ዩክሬን ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የአቅርቦት እጥረት እንደገጠማት ያሳያል ብለዋል።
ይህ ባለሥልጣን ይህን ይበሉ እንጂ በሌላ በኩል ምዕራባውያን የጣሉት ማዕቀብ ሩሲያ ከኃይል ሽያጭ በምትጋገኘው ገቢ ላይ ይህን ነው የሚባል ጉዳት አላመጣም የሚሉ ቡድኖች አሉ።
አንድ የፊንላንድ ተቋም ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች ከስድስት ወራት ወዲህ የኃይል ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ ሞስኮ 158 ሚሊዮን ዩሮ ገቢ ሳታገኝ አትቀርም ይላል።
አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት ግን ሞስኮ የጦሯ ግብዓት እክል ገጥሞታል ይላሉ።
ባለፈው ሳምንት የባይደን አስተዳደር ባለሥልጣናት ኢራን ሰራሽ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወደ ሞስኮ መላካቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የአሜሪካ የደኅንነት ኃላፊዎች እንደሚሉት ከሆነ የሩሲያ ባለሙያዎች ሞሃጀር-6 እና ሻሂድ የተባሉ ኢራን ሰራሽ ሰው አልባ አውሮፕላኖች አጠቃቀም ዙሪያ ሥልጠና ለመውሰድ ወደ ኢራን ተጉዘዋል።
በቅርብ ቀናት ደግሞ የአሜሪካ ደኅንነት ኃላፊዎች ወደ ሩሲያ የተላኩት ድሮኖች 'ቴክኒካል' እና 'መካኒካል' ችግሮች አጋጥሟቸዋል ብለዋል።
ዛሬ ማክሰኞ ጳጉሜ 01/2014 ዓ.ም. ደግሞ የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ በዕለታዊ መግለጫው ላይ፤ ሞስኮ በጦር ሜዳ እየደረሰባት ባለው ከፍተኛ ጉዳት ከፍተኛ የሆነ የሰው አልባ አውሮፕላን እጥረት አጋጥሟታል ብሏል።
ኢራን በበኩሏ ለሞስኮም ሆነ ለዩክሬን ጦር መሳሪያዎችን አልሰጠሁም ትላለች።












