ሊዝ ትረስ ከንግሥቲቱ ጋር ከተገናኙ በኋላ በይፋ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ

ንግስት ኤልዛቤጥ ሁለተኛ እና ጠቅላይ ሚንስትር ሊዝ ትረስ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, ንግስት ኤልዛቤጥ ሁለተኛ እና ጠቅላይ ሚንስትር ሊዝ ትረስ

ትናንት ሰኞ የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪ ሆነው የተመረጡት ሊዝ ትረስ ዛሬ ማክሰኞ ከንግሥት ኤልዛቤጥ ሁለተኛ ጋር ከተገኙ በኋላ በይፋ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ።

ሊዝ ትረስ ወደ ባልሞራል ቤተ-መንግሥት ተጉዘው ንግሥት ኤልዛቤጥን ያገኙት በይፋ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን የተለመደ አካሄድን መከተል ስላለባቸው ነው።

የዩኬ እና የኮመን ዌልዝ አገራት ንግሥት ኤልዛቤጥ ዳግማዊት በ70 ዓመት የንግሥና ዘመናቸው ሊዝ ትረስ 15ኛ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው።

አዲሷ ጠቅላይ ሚኒስትር ንግሥቲቱን ያገኙት ቀደም ሲል ተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ለንግሥቲቱ የመልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ካስገቡ በኋላ ነው።

ሊዝ ትረስ ከባኪንግሃም ይልቅ ስኮትላንድ ወደ ሚገኘው ባልሞራል ቤተ-መንግሥት መሄድ ያስፈለጋቸው ንግሥቲቱ ለመንቀሳቀስ የጤና እክል ስለገጠማቸው ነው ተብሏል።

ዛሬ ምን ይጠበቃል?

አዲሷ ጠቅላይ ሚኒስትር በመጀመሪያው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትርነት ቀናቸው ቀሪ የሥልጣን ዘመናቸውን የሚጀመሩት በሚከተሉት ተግባራት ይሆናል።

በቅድሚያ ንግሥት ኤልዛቤት፣ ሊዝ ትረስ ካቢኔያቸውን አዋቅረው መንግሥት እንዲመሰርቱ እና ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ግብዣ ያቀርባሉ።

ሊዝ ትረስም ‘እጅ መሳም’ ተብሎ በሚጠራው ሥርዓት ግብዣውን ይቀበላሉ።

ከዚያም በይፋ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ሊዝ ትረስ ወደ መኖሪያ እና የሥራ ቦታቸው ወደሚሆነው 10 ዶውኒንግ ስትሪት በማቅናት ከጥቁሩ በር ፊትለፊት የመጀመሪያ ንግግራቸውን ያደርጋሉ።

ሊዝ ትረስ በዚህ ንግግራቸው የአስተዳደራቸው ዋና ዓላማዎች ምን እንደሆኑ ያብራራሉ።

ቀጥሎ ባሉት ቀናት ሊዝ ትረስ ከሚተገብሯቸው ተግባራት መካከል አንዱ ለዩኬ ጦር ኃላፊዎች ደብዳቤ መጻፍ ነው።

በዚህ ጽሑፋቸው ዩናይትድ ኪንግደም የኒውክለር ጥቃት ቢፈጸምባት ምላሿ ምን ይሆናል የሚል ነው። ይህ ደብዳቤ ታዲያ የሚከፈተው ጦሩ ከዩኬ መንግሥት ጋር ግንኙነቱ ከተቋረጠ ነው።

ሊዝ ትረስ ዛሬ በይፋ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት የዩኬ ወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪ ሆነው ከተመረጡ በኋላ ነው።

ባለፉት ዓመታት የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት ሊዝ ትረስ፤ የወግ አጥባቂ መሪ ለመሆን ከቀድሞ የገንዘብ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ብርቱ ፉክክር ገጥሟቸው ነበር።

ይሁን እንጂ የኋላ ኋላ ሊዝ ትረስ በሰፊ የድምጽ ብልጫ ሪሺ ሱናክን በመብለጥ የወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪ እንዲሆኑ በፓርቲው አባላት ተመርጠዋል።