አዲሷ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስ ማን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን የወግ አጥባቂው ፓርቲ መሪ ሆነው የተመረጡት ሊዝ ትረስ ከንግሥት ኤልዛቤጥ ጋር ከተገናኙ በኋላ በይፋ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል። ሊዝ ከየት ተነስተው አሁን ካሉበት ደረሱ?
* *
ሊዝ ትረስ ገና በ7 ዓመታቸው የቀድሞዋን ዝነኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርጋሬት ታቸርን በመወከል ተማሪ ሳሉ ተውነው ነበር።
ሊዝ ትረስ ከ39 ዓመታት በኋላ በእውኑ ዓለም የወግ አጥባቂው ፓርቲ መሪ መሆን ችለዋል።
እስካሁን ድረስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን እያገለገሉ ያሉት ሊዝ ትረስ፣ በተቀናቃኛቸው ሪሲ ሱናክ ለአምስት ዙሮች ሲመሩ ቢቆዩም በወግ አጥባቂ ፓርቲ አባላት ምርጫ በመጨረሻ አሸናፊ መሆናቸው ታውቋል።
ሜሪ ኤልዛቤት ትረስ በሚለው ሙሉ የመዝገብ ስማቸው የሚታወቁት ፖለቲከኛዋ፣ ከሂሳብ ሊቁ አባታቸው እና ከነርስ እናታቸው እአአ 1975 በኦክስፎርድ፤ ኢንግላንድ ነበር የተወለዱት።
የሊዝ ትረስ መሠረታዊ መረጃዎች
- ዕድሜ፡ 47
- የትውልድ ስፍራ፡ ኦክስፎርድ
- መኖሪያ ቦታ፡ ለንደን እና ኖርፎርክ
- ትምህርት፡ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ምሩቅ
- የትዳር ሁኔታ፡ ባለትዳር እና የሁለት ሴት ልጆች እናት

ሊዝ ገና በልጅነት እድሜያቸው የዩናይትድ ኪንግደም አካል በሆነችው ስኮትላንድ መዲና ግላስጎ ውስጥ ኖረዋል። ከዚያም የቤተሰብ አባላቱ ወደ ሊድስ ተዘዋውሯል።
ሊዝ ትረስ በወጣትነት እድሜያቸው ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ገብተው፤ ፍልስፍና፣ ፖለቲካ እና ምጣሄ ሃብት አጥንተዋል። በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በተማሪዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ንቁ ተሳትፎን ያደርጉ ነበር።
አሁን ላይ የወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪ ሆነው የተመረጡት ሊዝ ትረስ፤ በተማሪነት ዘመናቸው ግን ሊብራል ዴሞክራት ነበሩ። ሊዝ በፀረ ንጉሣዊ አስተዳደር ላይ በሚያንጸባርቁት ጠንካራ አቋም ይታወቁ ነበር።
እአአ 1994 ላይ በሊብራል ፓርቲ ኮንፈረንስ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ “እኛ ሊብራል ዴሞክራቶች ለሁሉም መሰጠት ስላለበት ዕድል እናምናለን። ሰዎች ለመምረት ይወለዳሉ ብለን አናምንም” ሲሉ ተናግረው ነበር።

የሥልጣን ጉዞ
ሊዝ ገና በኦክስፎርድ ሳሉ ነበር የፖለቲካ አቋም ለውጥ በማድረግ ፊታቸውን ወደ ወግ አጥባቂ ፓርቲ ያዞሩት።
ከዩኒቨርሲቲ ከወጡ በኋላ ለሼል እንዲሁም ኬብል ኤንድ ዋየርለስ ለሚባል ኩባንያ የሂሳብ ባለሙያ ሆነው እያገለገሉ ሳለ ከሙያ አጋራቸው ጋር እአአ 2000 ላይ ትዳር መስርተዋል።
ጥንዶቹ በእስራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ የሁለት ሴት ልጆች ወላጆች ናቸው።
ትረስ እአአ 2001 ላይ በምዕራብ ዮርክሻየር የወግ አጥባቂ ፓርቲን ወክለው ተወዳድረው የነበረ ቢሆንም፣ ድል ሳይቀናቸው ቀርቷል። በተመሳሳይ 2005 ላይ በነበረ ምርጫም ተሸናፊ ነበሩ።
ሊዝ ትረስ ከአንድም ሁለቴ ሽንፈት ቢገጥማቸውም ለፖለቲካ እጅ አልሰጡም። እአአ 2006 ላይ በደቡብ ምሥራቅ ለንደን ካውንስለር ሆነው ተመርጠው ነበር።
እአአ 2010 ለነበረው ምርጫ የወግ አጥባቂው ፓርቲ መሪ ዴቪድ ካሜሩን ሊዝ ትረስን ለፓርቲው አጋርነት የመጀመሪያ ተመራጭ ዕጩ ዝርዝሮች ውስጥ ቢያካትቷቸውም፤ ወጣቷ ፖለቲከኛ ማርክ ፊልድ ከተባሉ የፓርላማ አባል ጋር የፍቅር ግንኙነት እንደነበራቸው ይፋ መሆኑን ተከትሎ ከፓርቲ አባላቶች ጫና በዝቶባቸው ነበር።
ይሁን እንጂ የቀረበባቸውን ፈተና በማለፍ ተመራጭ ሆነው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ሊዝ ትረስ እአአ 2010 ላይ ከሌሎች አራት የወግ አጥባቂ ፓርቲ አባላት ጋር በመሆን ‘ብሪታኒያ አንቼንድ’ የተሰኘ ብዙ ያነጋገረ መጽሃፍ አሳትመው ነበር።
በዛ መጽሐፍ ላይ ብሪታኒያውያን ሠራተኞችን፤ “በዓለማችን ካሉ ሰነፍ ሠራተኞች” ብለው መግለጻቸው ብዙ ያስተቻቸው ሲሆን፤ በቅርብ በነበሩ የክርክር መድረኮች ላይ ሊዝ ትረስ ይህን አስተያየት እንዳልጻፉ ተናግረዋል።
ሊዝ የፓርላማ አባል በሆኑ በሁለት ዓመታት ውስጥ የትምህርት ሚንስትር ሆነው ተሾሙ። ከሁለት ዓመታት በኋላ ደግሞ በእድገት የአካባቢ ጥበቃ ሚንስትር በመሆን ሌላ ሹመት አግኝተዋል።
ፖለቲካዊ አቋምና ሥልጣን
ምናልባትም እአአ 2015 ከአውሮፓ ኅብረት የመውጣት ሕዝበ ውሳኔ በዚህ የዩኬ ትውልድ ትልቁ የፖለቲካ ክስተት ሊሆን ይችላል።
ሊዝ ትረስ በብሬክዚት ላይ የነበራቸው አቋም ዩናይትድ ኪንግደም በአውሮፓ ኅብረት ውስጥ መቆየት አለባት የሚለው ነበር።
ዘ ሰን ጋዜጣ ላይ አስፈረውት በነበረው መከራከሪያቸው፤ ዩኬ ከአውሮፓ ኅብረት ብትለይ ምርቶችን ለአውሮፓ ኅብረት ማቅረብ ፈታኝ ይሆናል ብለው ነበር።
በሕዝበ ውሳኔው ዩኬ ከአውሮፓ ኅብረት ከተለየች በኋላ ሊዝ ትረስም አቋማቸውን በመቀየር፤ ዩኬ ከኅብረቱ መውጣቷ በበጎ መልኩ የአሰራር ሂደቶችን ቀይሯል ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ አስተዳደር ውስጥ የፍትሕ ሚኒስትር፣ ከዚያም ደግሞ የግምጃ ቤት ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል።
እአአ 2019 ላይ ቦሪስ ጆንሰን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ወደ ሥልጣን ሲመጡ ደግሞ ሊዝ ትረስ የዓለም አቀፍ ንግድ ሚኒስትር ሆነው ማገልገል ጀምረዋል።
ሊዝ የ46 ዓመት ጎልማሳ ሳሉ ነበር ትልቁን የመንግሥት ኃላፊነት የተረከቡት። እአአ 2021 ከዶሚኒክ ራብ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሥልጣንን ተረክበዋል።
የሊዝ ትረስ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ያደረጉት ጉዞ አልጋ ባልጋ አልነበረም። ከተቀናቃኛቸው ሪሺ ሱናክ ጋር በነበሯቸው ክርክሮች ላይ ባቀረቧቸው መከራከሪያዎች ሲተቹ ነበር።
ይሁን እንጂ የምርጫ ውጤቱ ሊዝ ትረስ ከሪሺ ሱናክ ይልቅ በፓርቲ አባላት ዘንድ የተሻለ ተቀባይነት እንዳላቸው አሳይቷል።












