አል-ሸባብ የእርዳታ እህልን ዒላማ አድርጎ በርካቶች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በሶማሊያ ሂራን ግዛት ጽንፈኛው የአል-ሻባብ ታጣቂ ቡድን የእርዳታ እህል የጫኑ በርካታ ተሽካርካሪዎች ላይ ባደረሰው ጥቃት ከ20 ያላሱ ሰዎች ሲገደሉ የእርዳታ እህል ደግሞ ወድሟል።
የግዛቷ አስተዳዳሪ ለቢቢሲ ሶማልኛ፤ “ሰዎች የነበሩበት መኪና ውስጥ ቦምብ አፈንድተዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
ለጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደው አል-ሻባብ እርምጃ የወሰድኩባቸው ተሸከርካሪዎች ከመንግሥት ጋር ወግነው ለሚወጉን ታጣቂዎች ምግብ ጭነው የነበሩ ናቸው ብሏል።
እስላማዊው ታጣቂ ቡድን አል-ሻባብ ዒላማ ያደረኩት ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ያለቸውን ታጣቂ ቡድኖችን ነው ይበል እንጂ ከሟቾቹ መካከል ሴቶች እና ሕጻናት ይገኙበታል ተብሏል።
በአሁኑ ወቅት በምስራቅ አፍሪካ በተለይ ደግሞ በሶማሊያ በአስርት ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ አስከፊ ድርቅ መከሰቱን ሰብዓዊ ተቋማት ሲገልጹ ቆይተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተው ድርቅ በሶማሊያ ብቻ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አፈናቅሏል ብሏል።
ከአል-ቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው አል-ሻባብ የማዕከላዊ መንግሥቱን ለመቆጣጠር የፌደራል መንግሥቱን ይወጋል። በአሁኑ ወቅት አል-ሻባብ አብዛኛውን ደቡባዊ እና መካከለኛውን ሶማሊያ ተቆጣጥሮ ይገኛል።
ከሁለት ሳምንት በፊት የአል-ሻባብ ታጣቂዎች የመንግሥት ባለስልጣናት ያዘወትሩበታል ወደ ተባለ ሆቴል በኃይል ገብተው ከ20 በላይ ሰዎችን ገድለው ነበር።
አርብ ነሐሴ 27/2014 ዓ.ም. የእርዳታ እህል ጭነው በነበሩ ተሽከርካሪዎች ላይ በተፈጸመው ጥቃት የሟቾች ቁጥር ከፍ ሊል እንደሚችል የሂራን ግዛት አስተዳዳሪ አሊ ጄይሬ ኦስማን ተናግረዋል።
“የተጎዱ ሰዎች አሉ። የተኩስ ድምጽ ሲሰሙም የሸሹ አሉ። የሕጻናት እና የሴቶችን ጨምሮ አስክሬኖች እስካሁንም እየተሰበሰቡ ነው” በማለት ተናግረዋል።
የግዛት አስተዳዳሪው ታጣቂ ቡድኑ የውሃ ጉድጓዶችን ጨምሮ መሠረተ ልማቶችን እያፈረሰ መሆኑን በመጥቀስ አል-ሻባብ ጦርነት የገጠመው ከሰፊው ማሕብረሰብ ጋር ነው ብለዋል።
የአካባቢው ጎሳ መሪ ሞሐመድ አብዲራህማን ደግሞ ጥቃቱን “አስከፊ” ሲሉ የገለጹት ሲሆን ሟቾቹ ሰላማዊ ዜጎች መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ አገራቸው በሽብር ላይ በምታደርገው ጦርነት አስተዳደራቸው “የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም” ብለዋል።












