በካናዳ 10 ሰዎችን በስለት ወግተው የገደሉት ግለሰቦች እየተፈለጉ ነው

የካናዳ ፖሊስ የሚፈልጋቸው ተጠርጣሪዎች ምስል

የፎቶው ባለመብት, RCMP Saskatchewan

በካናዳዋ ሳስካቹዋን ግዛት ቢያንስ 25 ሰዎችን በስለት ወግተው በሽሽት ላይ ያሉ ሁለት ግለሰቦች እየታሰሱ ነው።

የአገሪቱ ፖሊስ ዳሚዬን ሳንድርሰን እና ማየልስ ሳንደርሰን የተባሉ ሁለቱ ግለሰቦች በመንገዳቸው ያገኟቸውን በስለት ከወጉ በኋላ 10 ሰዎች ሞተው 15 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል ብሏል።

ይህ ጥቃት ካናዳ በታሪኳ ካጋጠሟት የከፉ ጥቃቶች መካከል አንዱ ነው ተብሏል።

ጥቃቱ የተፈጸመው በጄምስ ስሚዝ ክሪ እና ዌልደን ተብሎ በሚጠራ መንደር በሚገኙ 13 ቦታዎች ነው።

ፖሊስ በወንጀል ድርጊቱ የሚፈለጉት ግለሰቦች የታጠቁ እና አደገኛ ስለሆኑ ዜጎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል። ከዚህ በተጨማሪም ፖሊስ አሰሳው በቀጠለበት ወቅት ሰዎች በቤት እንዲቆዩ ጠይቋል።

“ደኅንነቱ በተጠበቀ ስፍራ ቆዩ። ወደ መኖሪያ ቤትዎ ስለሚያስገቡት ሰው ጥንቃቄ ያደርጉ” ሲል የግዛቷ ሮያል ካናዳ ሞወንትድ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል።

ጥቃቶች በተፈጸሙበት አካባቢ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ሲሆን፤ ፖሊስ መንገዶች በመዝጋት መታወቂያ እየጠየቀ የተጓዦችን ማንነት እየለየ ነው።

ፖሊስ ጥቃት አድራሾቹን በተመለከተ ሰዎች መረጃ እንዲኖራቸው እና ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በሳስካቹዋን እና በአጎራባች አልበርታ እና ማኒቶባ ግዛቶች ለተመዘገቡ ሞባይል ቁጥሮች የማሳሰቢያ መልዕክት ልኳል።

ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ በትዊተር ገጻቸው ላይ ጥቃቱን “አስከፊ እና ልብ የሚሰብር” ሲሉ የገለጹት ሲሆን ጥቃቱን ያደረሱት ለሕግ መቅረብ አለባቸው ብለዋል።

በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር እሁድ ምሽት ላይ የአገሪቱ ፖሊስ በሰጠው መግለጫ በጥቃቱ እንደተጎዱ ከታወቁት 15 ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ ብሏል።

አንዳንዶች ጥቃት አድራሾቹ ጥቃት ያደረሱት ሰዎችን እየለዩ ነው ቢሉም ሌሎች ደግሞ በመንገዳቸው ያገኙትን ሁሉ ነው በስለት የወጉት ይላሉ።

በወንጀል ድርጊቱ የተጠረጠሩት የ31 ዓመቱ ዳሚዬን ሳንድርሰን እና የ30 ዓመቱ ማየልስ ሳንደርሰን ግንኙነት ምን እንደሆነ ፖሊስ እስካሁን ያለው ነገር የለም።