በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ በታጣቂዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች በእጅጉ እንዳሳሰቡት ኢሰመኮ ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, social media
ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ውስጥ ኡሙሩ ወረዳ ለበርካታ ነዋሪዎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት የሆኑት በታጣቂዎች የተፈጸሙ ጥቃቶች በእጅጉ አሳሳቢ እንደሆኑ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ከነሐሴ 23 እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ በታጣቂ ኃይሎች የተፈጸሙ ጥቃቶችን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ ከ60 በላይ ሰዎች መገደላቸውን፤ ከ70 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን እና ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን ገልጿል።
የመብት ድርጅቱ ከነዋሪዎችን እና ከመንግሥት አካላት ያሰባሰበውን መረጃ መሠረት አድርጎ እንዳለው ጥቃቱ “በአካባቢው ተሰማርቶ የነበረ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ወደ ሌላ አካባቢ መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ” ተፈጽሟል።
ጥቃቱን ኣሳሰቢ ነው ያሉት የመብት ተቋሙ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በማንኛውም ጊዜ የፀጥታ ስጋት ካለባቸው አካባቢዎች የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ወደ ሌላ ቦታ በሚዘዋወሩበት ወቅት የነዋሪዎች አጠቃላይ ደኅንነት ለአደጋ እንዳይጋለጥ ጥንቃቄ መደረግ አለበት” ሲሉ አሳስበዋል።
ጥቃቱ በነሐሴ 23/2014 ዓ.ም. ሲጀመር መንግሥት በሽብርተኝነት የፈረጀውና ሸኔ ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ አገምሳ ቀበሌ በፈጸሙት ጥቃት ሦስት የአማራ ብሔር ተወላጆች መግደላቸውን ተከትሎ ጥቃቱ መባባሱን ኮሚሽኑ ገልጿል።
በዚህም በተከታይ ቀናት ከኡሙሩ ወረዳ፣ ሀሮ አዲስ ዓለም ከተባለ ቀበሌ እና አጎራባች ከሚገኘው የአማራ ክልል፣ ቡሬ ወረዳ የተውጣጡ ታጣቂዎች ኡሙሩ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ በርካታ ቀበሌዎች ውስጥ በሚገኙ ቀበሌዎች ባሉ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል ብሏል ኢሰመኮ።
በጥቃቶቹ ከ60 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፣ ከ70 በላይ ሰዎች ቆስለው የነዋሪዎች የቤት ንብረቶች እና የቀንድ ከብቶች መዘረፋቸውን እንዲሁም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችንና የመንግሥት ኃላፊዎችን ጠቅሶ ገልጿል። ጨምሮም ጥቃቱን ተከትሎ የተፈናቀሉት ነዋሪዎች ኦቦራ በተባለ ከተማ ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙም አመልክቷል።
ከዚህ ባሻገርም ኮሚሽኑ በተፈጸሙት ጥቃቶች ሳቢያ የተከሰተው ስጋት አሁንም አሳሳቢ መሆኑን እና በዞኑ ውስጥ ባሉ ሌሎች ወረዳዎች ውስጥም ተመሳሳይ ጥቃቶች ሊፈጸሙ እንደሚችሉ ስጋቶች መኖራቸውን ኮሚሽኑ ከነዋሪዎች መረዳቱን ገልጿል።
ኮሚሽኑ ጥቃት በተፈጸመባቸው አካባቢዎች በአስቸኳይ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እንዲሰማሩ እና ሰላምና ደኅንነትን በማረጋገጥ ነዋሪዎችን ወደ ተረጋጋ ሕይወት የመመለስና ተገቢውን ምርመራ አድርጎ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሥራ እንዲሠራ አሳስቧል።
በምዕራብ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በነዋሪዎች ላይ በታጣቂዎች አማካይነት በሚፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ሲዘገብ ቆይቷል። እነዚህ ጥቃቶች ማንነትን መሠረት ያደረጉ መሆናቸው በእጅጉ አሳሳቢ መሆኑን ዓለም አቀፍ የመብት ድርጅቶችን ጨምሮ ሌሎችም ሲገልጹ ቆይተዋል።
ቀደም ባሉት በምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ ለተፈጸሙት ጥቃቶች ነዋሪዎችና መንግሥት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ተጠያቂ ሲያርጉ፣ ቡድኑ ግን ድርጊቱን አለመፈጸሙን በተደጋጋሚ ሲያስተባብል ቆይቷል።
ባለፈው ሳምንት የተፈጸመውን ጥቃት ጨምሮ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከኦሮሞ ነጻነት በተጨማሪ የአካባቢ ባለሥልጣናት እና ነዋሪዎች የአማራ ታጣቂዎች እጅ እንዳለበት ይከሳሉ።
ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ውስጥ ኡሙሩ ወረዳ የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ አስካሁን የክልሉ መንግሥት ያለው ነገር የለም፣ ቢቢሲም ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ምላሽ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም ሳይሳካለት ቀርቷል።












