አምስት ስዊድናዊ ታዳጊዎች የታክሲ አሽከርካሪ በመግደል ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, SHUTTERSTOCK
አራት ስዊድናዊያን ታዳጊዎችና አንድ የ15 ዓመት እህታቸው የታክሲ አሽከርካሪ ገድለዋል ሲል ፍርድ ቤት ወስኗል።
ታዳጊዋ አሽከርካሪውን የመድፈር ወንጀል ፈፅሞብኛል ስትል ከሳ ነበር።
የታክሲ አሽከርካሪው ባለፈው መጋቢት ስዊድን በሚገኝ አንድ የተፈጥሮ ጥበቃ ሥፍራ ተሰቅሎ ነው የተገኘው።
የአፕሳላ ፍርድ ቤት ይህን የደረሰበት ታዳጊዋ አሽከርካሪው ወደዚያ ሥፍራ የተገኘው ወሲባዊ ድርጊት ሊፈፅም ቃል ተገብቶለት ነው ማለቷን ተከትሎ ነው።
የታክሲ አሽከርካሪው አስከሬን ለአንድ ሳምንት ያክል አልተገኘም ነበር።
በጊዜው የ18 ዓመት ታዳጊ የነበረው ታላቅ ወንድም የዕድሜ ልክ ፅኑ እሥራት ተፈርዶበታል።
ሌሎቹ አራት ታዳጊዎች ደግሞ ከሶስት እስከ አራት ዓመት ፍርድ የተወሰነባቸው ሲሆን በታዳጊዎች ማረሚያ የሚቆዩ ይሆናል።
ሶስቱ ወንድማማቾች በግድያ ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ሲገኙ ጊዜው የ15 ዓመት ታዳጊ የነበሩት እህታቸውና የፍቅር ጓደኛዋ ግድያው ሲፈፀም በሥፍራው ባይኖሩም የወንጀል ተባባሪ በመሆናቸው ነው የተፈረደባቸው።
የታክሲ አሽከርካሪው ዛፍ ላይ ተሰቅሎ የተገኘ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ይህ የሆነው ታዳጊዎች ግድያው ራስ ማጥፋት እንዲመስል በማድረጋቸው ነው ብሏል።
ምንም እንኳ አምስቱም ታዳጊዎች ግድያውን አልፈፀምንም ቢሉም ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው ከአቃቤ ሕግ በተገኘ ማስረጃ ነው።
አቃቤ ሕግ ታዳጊዎቹ የተላላኩትን የፅሑፍ መልዕክት ለፍርድ ቤቱ አቅርቦ የግድያ ወንጀል ለመፈፀም ሲያሴሩ ነበር ብሏል።
አንደኛው ወንድም “አርብ ዕለት እናድርገው [የግድያው ቀን]” ብሎ ሲፀፍ፤ ሌላኛው ወንድም “እሺ” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
በአውሮፓውያኑ መጋቢት 20 ሰለባው ከመጥፋቱ ከአራት ቀናት በፊት ታዳጊዋ ለጓደኛዋ “ወንድሞቼ ደፋሪየን ሊያገኙት ነው” ስትል የፅሑፍ መልዕክት ልካ ነበር።
ከግድያው በኋላ አንደኛው ወንድም ከግድያ ሰለባው የባንክ ሒሳብ ወደራሱ ገንዘብ ማስተላለፉም ተረጋግጧል።
ታዳጊዋ ወንድሞቿ ግለሰቡን ሊገድሉት ሳይሆን ሊደበድቡት እንደሆነ እንደምታውቅ ለፍርድ ቤቱ ተናግራ ወንጀሉን አልፈፀምንም ስትል አስተባብላለች።
ነገር ግን የአፕሳላ ቀጣና ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ላርስ ሆምጋርድ፤ ወንድማማቾቹ ሰውየውን ለመግደል ማሴር የጀመሩት ገመድ ከገዙ ጀምሮ ነው ሲሉ ፈርደዋል።
“ዕቅዳቸው የነበረው ሰውየውን በገመድ መስቀል ነው” ብለዋል።












