በአውስትራሊያ የህጻናት እንክብካቤ ሰራተኛ በመድፈር መከሰሱን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ህጻናት ምርመራ ሊደረግላቸው ነው

ፖሊስ ያጠረው ስፍራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአውስትራሊያዋ ከተማ ሜልቦርን የህጻናት እንክብካቤ ማዕከል ሰራተኛ ህጻናትን በመድፈር መከሰሱን ተከትሎ 1 ሺህ 200 የሚሆኑ ህጻናት የተላላፊ በሽታዎች ምርመራ ሊደረግላቸው ነው።

ጆሹዋ ዳሌ ብራውን የተባለው ግለሰብ የአምስት ወር ህጻንን ጨምሮ ስምንት ህጻናት ላይ ጥቃት በመፈጸም 70 ክሶች ተመስርተውበታል።

ግለሰቡ ህጻናቱን ከ2022 እስከ 2023 ባለው ወቅት ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ተገልጿል።

የ26 ዓመቱ ግለሰብ ከአውሮፓውያኑ 2017 ጀምሮ ባሉት ዓመታት በ20 የህጻናት እንክብካቤ ማዕከላት ሰርቷል።

በዚህ ሰራተኛ እንክብካቤ ስር የነበሩ ማንኛውም ህጻናት "ለጥንቃቄ" ምርመራ እንዲደረግላቸው የጤና ባለስልጣናቱ ወላጆቻቸውን እያሳወቁ ነው።

ብራውን በእስር ላይ የሚገኝ ሲሆን በመጪው ዓመት መስከረም ላይ ሜልቦርን በሚገኘው ፍርድ ቤት ይቀርባል።

ግለሰቡ ጥቃት አድርሶባቸዋል የተባሉት ከአምስት ዓመት በታች ያሉት ስምንቱ ህጻናት 'ክሬቲቭ ጋርደንስ' የተሰኘ ማዕከል ነው።

ብራውን በመድፈር፣ ወሲባዊ ጥቃቶች እንዲሁም ህጻናት ጥቃት ሲደርስባቸው የሚያሳዩ ይዘቶችን በማዘጋጀት እና በማሰራጨት ነው የተከሰሰው።

የጤና ባለስልጣናት ከሰሞኑ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በህጻናት ዙሪያ ለሚሰሩ ግለሰቦች አጣርቶ ፍቃድ የሚሰጠው ችልድረን ቼክ በተሰኘው ተቋም ግለሰቡ ፍቃድ የተሰጠው መሆኑ ተገልጿል።

ብራውን እነዚህን ጥቃቶች በፈጸመበት ወቅት ብቻውን እንደነበር የገለጹት ባለስልጣናቱ የተፈጸሙትም በቪክቶሪያ ብቻ መሆኑም ተነግሯል።

የጥቃት ፈጻሚዎችን ማንነትን ይፋ ማድረግ በአውስትራሊያ ህግ "ያልተለመደ ውሳኔ" ቢሆንም የቪክቶሪያ ፖሊስ ጃኔት ስቲቨንሰን ይህ ግን "ልዩ ጉዳይ" ነው ሲሉ ገልጸዋል።

"በህጻናት የእንክብካቤ ማዕከላት ውስጥ ልጆች ያሏቸው ወላጆች በሙሉ ግለሰቡ ማን እንደሆነ እና የት እንደሚሰራ እንዲያውቁ ማድረግ መሰረታዊ ጉዳይ ነው" ብለዋል።

ብራውን በወሲብ በሚተለላፉ ህመሞች ተጠቅቶ እንደሆነ ዋና የጤና መኮንን ክርስቲያን ማክግራዝ ከመናገር የተቆጠቡ ቢሆንም ለህጻናቱ ተላላፊ በሽታዎች ምርመራ ማድረግ ግለሰቡ ከተወነጀለባቸው ጥቃቶች አንጻር የአሰራሩ አካል ነው ብለዋል።

እስካሁን ድረስ ወደ 2,600 የሚጠጉ ቤተሰቦችን ባለስልጣናቱ ያናገሩ ሲሆን 1, 200 ህጻናት ምርመራ እንዲደረግላቸው እንዲሁም በተላላፊ በሽታዎች ተጠቅተው የሚገኙ ህጻናት ህክምና እንደሚደረግላቸው አመልክተዋል።

የቪክቶሪያ አስተዳዳሪ ጃሲንታ አለን ተፈጸሙ የተባሉ ጥቃቶች "ህመም ፈጥሮብኛል" ብለዋል።

"ለእያንዳንዱ ወላጅ አስከፊ በሆነው በዚህ እያለፉ ላሉ ወላጆች ልቤ ተሰብሯል" ብለዋል።

በቪክቶሪያ የሚገኙ ቤተሰቦች በሙሉ ሁኔታው "እንደሚያስፈራቸው እና እንደሚያበሳጫቸው" የገለጹት ጃሲንታ በዚህ የተጎዱ ሰዎችን የሚያግዝ ድረገጽ ተዘጋጅቷል ብለዋል።