የኡጋንዳ ወታደራዊ ሄሊኮፕተር በሶማሊያ አውሮፕላን ማረፊያ ተከሰከሰ

የፎቶው ባለመብት, Munasar Mohamed
ስምንትን ሰዎችን አሳፍሮ የነበረ የኡጋንዳ ወታደራዊ ሄሊኮፕተር በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ ዋና አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ረቡዕ፣ ሰኔ 25/ 2017 ዓ.ም መከስከሱን የሶማሊያ አቪዬሽን ባለስልጣን ለቢቢሲ ተናገሩ።
ሄሊኮፕተሩ መከስከሱን ተከትሎ በአደን አዴ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ የእሳት ቃጠሎ ተነስቶ የነበረ ቢሆንም በአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በፍጥነት በቁጥጥር ስር መዋሉን የመንግሥት የዜና ወኪል ዘግቧል።
ከአውሮፕላን ማረፊያው ከፍተኛ ጭስ ሲወጣ የሚያሳይ ቪዲዮ ተጋርቷል።
"ፍንዳታ ሰምተን ከሄሊኮፕተሯ ላይ የእሳት ነበልባል እና ጭስ ሲወጣ አየን። ጭሱ ሄሊኮፕተሯን ሙሉ በሙሉ ሸፍኗታል" ሲሉ የአየር መንገድ ሰራተኛ የሆኑት ፋራህ አብዱሌ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ረቡዕ ጥዋት 1፡30 ላይ በኡጋንዳ መከላከያ ኃይል የሚተዳደረው የአፍሪካ ህብረት ሄሊኮፕተር አደን አዴ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከማረፉ በፊት መከስከሱን በአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በሄሊኮፕተሩ ውስጥ ከነበሩት ስምንት ተሳፋሪዎች መካከል ሶስቱን መታደግ የታቻለ ሲሆን ለህክምና ወደ ሞቃዲሾ የአውሶም ሆስፒታል መወሰዳቸውን ተልዕኮው ገልጿል።
የተቀሩትን ሰራተኞች እና ተሳፋሪዎችን የማፈላለግ እና የማዳን ስራዎች መቀጠላቸውን አክሏል።
የአደጋው መንስዔም ሆነ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ የተገለጸ ነገር የለም።
የሶማሊያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ኃላፊ አህመድ ማሊም ሄሊኮፕተሩ ከሞቃዲሾ 90 ኪሎሜትር ርቀት ላይ፣ የታችኛው ሸበሌ ክልል ከሚገኘው ባሊዶግሌ የጦር ሰፈር ተነስቶ ከበረረ በኋላ በአውሮፕላን ማረፊያው ወታደራዊ ማረፊያ ላይ ወድቋል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአደጋውን መንስዔ ለማጣራት ምርመራ እየተካሄደ መሆኑንም ተናግረዋል።
"ሄሊኮፕተራችን በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ ሊያርፍ ሲል ተከስክሶ በእሳት ተያይዟል። ሶስቱ እሳቱ ቢደርስባቸውም አምልጠዋል የተቀሩት አምስቱ እስካሁን ያሉበት ሁኔታ አይታወቅም። የአደጋውን መንስዔ ለማጣራት ኮሚቴ እናቋቁማለን" ሲሉ የኡጋንዳ ጦር ቃል አቀባይ ፌሊክስ ኩላይግዬ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኡጋንዳ ወታደሮች በአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) ካቀፋቸው 11 ሺህ ወታደሮች መካከል የሚገኙበት ሲሆን የአገሪቱ ማዕከላዊ መንግሥት ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ካለው የአልሻባብ ቡድን ጋር በሚደረገው ትግል እየተሳተፉ ይገኛሉ።
አደጋው የቱርክ አየር መንገድ ንብረት የሆነ የመንገደኞች አውሮፕላን ከመነሳት ቢያዘገየውም የሃገር ውስጥ በረራዎች ግን መደበኛ ስራቸውን ቀጥለዋል።















