የኢኳቶሪያል ጊኒው ባለሥልጣን የወሲብ ቪድዮ ሾልኮ መውጣት እና የሥልጣን ሽኩቻ

ባልታዛር ኢባንግ ኢንጎንጋ

የፎቶው ባለመብት, Baltasar Ebang Engonga / Facebook

ከሰሞኑ የአንድ የኢኮቶሪያ ጊኒ ባለሥልጣን የወሲብ ቪድዮዎች ሾልከው መውጣታቸው ከፍተኛ ትኩረት አግኝቷል።

ነገር ግን የሰውዬው የወሲብ ቅሌት አፈትልኮ መውጣቱ ቀጣዩ የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ማን እንደሚሆን ሊጠቁመን ይችላል።

በበይነ መረብ የተሰራጩት ቪድዮዎች ከ150 እስከ 400 እንደሚሆኑ ይገመታል። ይህ ነባር የመንግሥት ባለሥልጣን ከተለያዩ ሴቶች ጋር ቢሮው ውስጥ እና የተለያዩ ቦታዎች ወሲብ ሲፈፅም ይታያል።

በተለይ በማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ዘንድ መነጋገሪያ የሆነው የግለሰቡ ድርጊት የትንሿን የመካከለኛው አፍሪካ ሀገር ዜጎች አስደንግጧል።

ቪድዮው ላይ የሚታዩት አብዛኛዎቹ ሴቶች የባለሥልጣን ሚስቶች እና ለባለሥልጣናት ቅርበት ያላቸው ናቸው።

በመልከ መልካምነቱ ምክንያት “ቤሎ” ተብሎ ከሚጠራው ባልታዛር ኢባንግ ኢንጎንጋ ጋር ወሲብ ሲፈፅሙ የሚታዩት አብዛኛዎቹ ሴቶች ድርጊቱን የፈፀሙት በፈቃደኝታቸው እንደሆነ ተነግሯል።

የፕረስ ነፃነት ብዙ ባልተጠበቀባት ኢኳቶሪያል ጊኒ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን ማጣራት ከባድ ነው።

ነገር ግን እየተንሰራፋ ያለው ፅንሰ ሐሳብ የወሲብ ቪድዮዎች መውጣት ቀጣዩ ፕሬዝደንት ይሆናሉ ተብሎ የሚጠበቁ ሰውን ለማጣጣል ነው ይላል።

ባልታዛር የፕሬዝደንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ንጉዌማ ዘመድ ነው። ዕድሜ ጠገቡን ፕሬዝደንት ወደፊት ይተካሉ ተብለው ከሚጠበቁ ሰዎች መካከልም አንዱ ነው።

ከአውሮፓውያኑ 1979 ጀምሮ ሥልጣን ላይ የቆዩት ኢቢያንግ በዓለማችን ብዙ ዓመት መንበረ ሥልጣን ላይ የከረሙ ሰው ናቸው።

የ82 ዓመቱ ፕሬዝደንት በሥልጣን ዘመናቸው የሀገሪቱን ኢኮኖሚ መለወጥ ቢችሉም እየተሟጠጠ በመጣው የሀገሪቱ ነዳጅ ምክንያት ምጣኔ ሀብቷ ተቃውሷል።

እጅግ የናጠጡ ሀብታሞች የሀገሪቱን ሥልጣን ይቆጣጠራሉ። ከ1.7 ሚሊዮን ሕዝቧ አብዛኛው ግን ድኅነት ውስጥ ነው።

የኦቢያንግ አስተዳደር በሰብዓዊ መብት ጥሰት ከፍተኛ ትችት ይደርስበታል። የአሜሪካ መንግሥት የኦቢያንግን አስተዳደር ዜጎችን በመግደል እና በማሰቃየት ወንጀል ይከሳል።

ከፕሬዝደንቱ ልጆቹ አንዱ ምክትል ፕሬዝደንት ናቸው። እጅግ የናጠጡ ሀብታም መሆናቸው የአደባባይ ሚስጢር ነው። በአንድ ወቅት የሚያብረቀርቀው የማይክል ጃክሰንን ጓንትን በ275 ሺህ ዶላር መግዛታቸው ይታወሳል።

ምንም እንኳ ሀገሪቱ ምርጫ ብታካሂድም ምንም አይነት ተቃዋሚ ፓርቲ የላትም። አብዛኛዎቹ አክቲቪስቶች እስር ቤት አሊያም ከሀገር ውጭ ናቸው።

የማይክል ጃክሰን ጓንት

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የማይክል ጃክሰን ጓንት
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በኢኳቶሪያል ጊኒ ፖለቲካ ማለት ወደ ቤተ-መንግሥት ለመግባት የሚደረግ ሽኩቻ ሲሆን የባልታዛር የወሲብ ቅሌትም ከዚህ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል።

ሰውዬው የብሔራዊው የፋይንናስ ምርመራ ኤጀንሲ ኃላፊ ነበር። ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ጨምሮ ሌሎች ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን ይመረምራል።

ነገር ግን ነገሮች ተገልብጠው ባልታዛር ራሱ ምርመር ተከፍቶበት ኖሯል።

ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር የዋለው ጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ሲሆን የቀረበበት ክስ ደግሞ ዳጎስ ያለ ገንዘብ በመመዝበር ኬማን ደሴቶች ላይ ወዳለ አካውንት አዛውሯል የሚል ነው።

ባልታዛር ብላክ ቢች ወተባለው በዋና ከተማዋ ማላቦ ወደሚገኝ ስሙ የጠለሸ እስር ቤት የተላከ ሲሆን ተቃዋሚዎች ከፍተኛ ስቃይ የሚደርስባቸው እዚህ እስር ቤት እንደሆነ ይነገራል።

የግለሰቡ ስልኮችና ኮምፒውተሮች በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው የወሲብ ቪድዮዎቹ በይነ መረብ ላይ ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩት።

ቪድዮዎቹ አንድ በአንድ መለቀቅ የጀመሩት ቴሌግራምፕ ላይ ወሲባዊ ምስሎችን በሚለጥፍ ገፅ አማካይነት ነበር። ኢኳቶሪያል ጊኒ ውስጥ ደግሞ በስፋት የተሰራጩት በዋትስአፕ ገፆች አማካይነት ነው።

ባልታዛር ቪድዮዎቹ ላይ በግልፅ የሚታይ ሲሆን አብዛኛዎቹ ሴቶች ደግሞ የፕሬዝደንቱ ዘመዶች እና የሚኒስትሮች እና የወታደራዊ ባለሥልጣናት ሚስቶች መሆናቸው ይፋ ሆነ።

ምክትል ፕሬዝደንቱ ቴዎዶሮ አቢያንግ ማንጉዌ የሀገሪቱ የቴሌኮም ኩባንያዎች በ24 ሰዓታት ውስጥ የወሲብ ቪድዮዎቹ እንዳይሰራጩ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ አስተላለፉ።

ምክትል ፕሬዝደንቱ እና የፕሬዝደንቱ ልጅ በኤክስ (በቀድሞው ትዊተር) ገፃቸው ቪድዮዎቹን ማን እንደለጠፋቸው እንደሚጣራና ቅጣት እንደሚተላለፍባቸው አስታውቀዋል።

ምክትል ፕሬዝደንቱ እና የፕሬዝደንቱ ልጅ ቴዎዶሮ አቢያንግ ማንጉዌ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ምክትል ፕሬዝደንቱ እና የፕሬዝደንቱ ልጅ ቴዎዶሮ አቢያንግ ማንጉዌ

የባልታዛር ኮምፒውተሮች እና ስልኮች በፖሊስ እጅ በመሆናቸው ቪድዮዎቹ የተለቀቁት የግለሰቡን ስም ለማጥፋት ነው የሚል ጥርጣሬ አለ።

አሁን ግልፅ ያልሆነው ነገር ባልታዛር ለምንድነው ቪድዮዎቹን ቀድቶ ያስቀመጣቸው የሚለው ነው።

ባልታዛር የፕሬዝደንቱ ዘመድ ብቻ አይደለም የኢንጎንጋ ኤጆ ልጅ ነው። ሰውየው የማዕከል አፍሪካ የገንዘብ ትብብር ኃላፊ እና በኢኳቶሪያል ጊኒ ስም ያላቸው ሰው ናቸው።

መኖሪያውን ለንደን ያደረገው አክቲቪስቱ ንሳንግ ክሪስቲያ “አሁን እያየነው ያለው የሥልጣን ሽኩቻ ነው። ፕሬዝደንቱ የሥልጣን ዘመናቸው እያበቃ በመሆኑ ቀጣዩ ፕሬዝደንት ለመሆን የሚደረግ ግርግር ነው” ይላሉ።

አክቲስቪስቱ አክለው ምክትል ፕሬዝደንቱ ኦቢያንግ ቀጣዩ ፕሬዝደንት መሆን ስለሚሹ “ተፎካካሪ የሚሏቸውን እያስወገዱ ነው” ይላሉ።

ምክትል ፕሬዝደንቱ እና እናታቸው የትኛውንም ተቀናቃኝ እያስወገዱ እንደሆነ ይሰማል። ከእነዚህ መካከል ጋብርኤል አቢያንግ ሊማ አንዱ ናቸው። ለ10 ዓመታት ያክል የነዳጅ ሚኒስትር ሆነው የሠሩት ሊማ ፕሬዝደንቱ ከሌላ ሚስት ያፈሯቸው ናቸው።

አክቲቪስቱ እንደሚሉት የወሲብ ቪድዮዎቹ የሥልጣን ሽኩቻ ማሳያ ከመሆናቸው ባለፈ ማኅበራዊ ሚድያውን ለመቆጣጠር እንደምክንያት ሊወሰዱ ይችላሉ።

ባለፈው ሐምሌ በኢኳቶሪያል ጊኒዋ አኖቢን ደሴት ተቃውሞ መነሳቱን ተከትሎ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ኢንተርኔት ማቋረጣቸው ይታወሳል።

አክቲቪስቱ ንሳንግ እንደሚለው ባለሥልጣናት ከትዳራቸው ውጭ መማገጣቸው አዲስ ነገር አይደለም፤ የሀገሪቱ ሥልጣን በጥቂት ሰዎች እጅ መሆኑን ማሳያም ነው።

ፈረንሳይ ውስጥ በሙስና ወንጀል የተፈረደባቸው ምክትል ፕሬዝደንቱ ከወሲባዊ ቅሌት በኋላ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የደኅንነት ካሜራዎች እንዲተከሉ አዘዋል። አክሎም መሰል ድርጊት የሚፈፅሙ ባለሥልጣናት ቅጣት ይተላለፍባቸዋልም ብለዋል።

የጉግል መረጃ እንደሚያሳየው የኢኳቶሪያል ጊኒ ስም በጣም ተፈላጊ ነበር። ኤክስ ላይ ደግሞ በኬንያ፣ ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ደግሞ “ኢኳቶሪያል ጊኒ” የሚለው ስም ከአሜሪካ ምርጫ በላይ ትኩረት አግኝቶ (ትሬንድ ሲያደርግ) ውሏል።