ውቅያኖስ ላይ ጠፍቶ የነበረው አውስትራሊያዊ ሁለት ወር ሙሉ ጥሬ ዓሣ እየበላ ከውሻው ጋር ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, 9 NEWS
ከሁለት ወራት በፊት ከውሻው ጋር ባሕር ላይ ጠፍቶ የነበረው አውስትራሊያዊ ሁለት ወር ሙሉ ጥሬ ዓሣ እየበላ እና የዝናብ ውሃ እየጠጣ ቆይቶ በሕይወት ተገኘ።
ነዋሪነቱ ሲድኒ የሆነው የ51 ዓመቱ ቲም ሻዶክ እና ውሻው ቤላ ከሜክሲኮ ተነስተው ወደ ፍሬንች ፖሊኔዚያ ደሴት እያመሩ ሳለ ነው ጀልባቸው የተበላሸችው።
ቲምና ውሻው ቤላ ባሕር ላይ ለበርካታ ሳምንታት ቆይተዋል።
ከሳምንታት በኋላ አንድ ሄሊኮፕተር ተመልክቷቸው ባደረገው ጥቆማ ምክንያት ሰው ደርሶላቸዋል።
ቲም እና ውሻውን ለመታደግ የሄደው መርከብ ላይ የሚገኘው ዶክተር ለአውስትራሊያ መገናኛ ብዙሃን “ግለሰቡ ጤናው መልካም ነው” ብሏል።
ቲም ሻዶክ 6 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚርቀውን የባሕር ላይ ጉዞ ለማድረግ ከሜክሲኮ ላ ፓዝ ወደብ ነበር የተነሳው።
ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ በከባድ የአየር ሁኔታ ምክንያት የጀልባዋ ኤሌክትሮኒክስ ገመዶች ከጥቅም ውጭ ሆኑ።
በዚህ ምክንያት ግለሰቡና ውሻው አስፈሪው የሰሜን ፓሲፊክ ውቅያኖስ ላይ ተንሳፈው ቀሩ።
ከሁለት ወራት በኋላ ከሜክሲኮ ብዙም ሳይርቅ ሲገኝ ሰውነቱ ተጎሳቁሎ፤ ፂሙ አድጎ ነበር።
የአውስትራሊያው 9ኒውስ የዜና ጣቢያ ባስተላለፈው አንድ ቪድዮ ላይ ቲም “በጣም ብዙ ነገር አይቻለሁ። ውቅያኖስ ላይ የገጠመኝን መናገር ቀላል አይደለም” ብሏል።
“እሁን የሚያስፈልገኝ እረፍትና ጥሩ ምግብ ነው። ምክንያቱም ውቅያኖስ ላይ ለረዥም ጊዜ ቆይቻለሁ። ከዚያ ውጭ ጤንነቴ መልካም ነው።”
ሰውዬው እንደሚለው የያዘው የዓሣ ማጥመጃ በሕይወት እንዲቆይ እጅግ ረድቶታል።
አልፎም በፀሐይ እንዳይቃጠል የጀልባዋን ዳስ እየተጠለለ ከርሟል።
ግለሰቡ ከሁለት ወራት በኋላ ሰዎች ሲያገኙት ፈገግ ብሎ የደም መለኪያ መሣሪያ እጁ ላይ ተገጥሞ ታይቷል።
ዶክተሩ እንደሚሉት ለጊዜው አነስ ያሉ ምግቦችን እየበላ ነው።
ቲም እና ውሻውን ያገኘችው መርከብ አሁን ወደ ሜክሲኮ እያቀናች ሲሆን አውስትራሊያዊው ወደ ሆስፒታል ሄዶ ተጨማሪ ምርምራ ይደረግለታል።












