ሴት ባልደረቦቹ ጾታዊ ጥቃት ያደርስብናል እያሉ የሚከሱት ዝነኛው የቀድሞ የአል-ጀዚራ ጋዜጠኛ

አንዳንዶቹ የቀረቡብኝ ክሶች የተጋነኑ ናቸው ይላል

የፎቶው ባለመብት, BARRY IVERSON / ALAMY STOCK PHOTO

የምስሉ መግለጫ, ሴቶቸም ወንዶችም ላይ ጸታዊ ትንኮሳን በማድረስ ክስ የሚቀርብበት ጋዜጠኛ

ከማል ሳንታማሪያ ዕውቅ የቴሌቪዥን ዜና አቅራቢ ነው። ሥመ ጥር የቲቪ መርሐግብሮችንም ያሰናዳል።

ለአልጀዚራ ለ16 ዓመታት ካገለገለ ከኋላ ከሰሞኑ መልቀቁን ይፋ አድርጓል።

በድንገት የመልቀቁ ነገር ጋዜጠኛው ለብዙ ዓመታት በባልደረቦቹ ሲያደርስ የነበረውን ጾታዊ ጥቃት እየተጋለጠ በመምጣቱ የሆነ ነው የሚል ጥርጣሬ አለ።

ቢቢሲ ከባልደረቦቹ በደረሱት ጠንካራ መረጃዎች በመነሳት ግለሰቡ በእርግጥ የሚባለውን ጥቃት ሲያደርስ እንደኖረና ሆኖም ግን ጣቢያው በሱ ላይ ይመሠረቱ የነበሩ ክሶችን በቸልታ ሲመለከት እንደቆየ ተብራርቷል።

ካማል ሳንታማሪያ ማን ነው?

ካማል ሳንታማሪያ ቲቪኤንቪ (TVNZ) በሚባል የኒውዚላንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ ነበር ሥራ የጀመረው።

ከ32 ቀናት በኋላ ግን ሥራ ለቀቀ።

በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ሥራ የለቀቀው ከባህሪው በመነሳት ነበር።

ቢቢሲ ከቀድሞው እና ከአሁን ባልደቦቹ ስለ ጋዜጠኛው ባሰባሰበው መረጃ ግለሰቡ ጾታዊ ጥቃት የማድረስ አባዜ ያለበት እንደነበር ለመረዳት ችሏል።

በተለይም በዶሃ ቢሮ በርካታ ቅሬታዎች የሚቀርቡበት ሰው ነው።

አንዳንዶች እንዲያውም ይህ ጾታዊ ትንኮሳ የርሱ ብቻ ችግር አይደለም ይላሉ።

እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት በአልጃዚራ ውስጥ ጾታዊ ትንኮሳና ዘረኝነት እንደዋዛ ይታለፋሉ።

ቢቢሲ ለጋዜጠኛ ሳንታማሪያ ስለቀረበበት ክስ ምላሽ እንዲሰጥ ቢጠይቀውም በቀጥታ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በግሉ ጠቅለል ያለ መግለጫን ማተም መርጧል።

በዚህ መግለጫ፣ ‘የሚባሉት ክሶች አንዳንዶቹ እውነት ናቸው፤ አንዳንዶቹ ከአውድ ውጭ የተወሰዱ ናቸው፤ አንዳንዶቹ ቅጥፈት ናቸው’ የሚል መስመር ይገኝበታል።

ከቢቢሲ ለቀረበበት ክስ ሲመልስም፣ ‘ባሕሪዎቼ የሰዎችን ምቾት የሚነሱ ከነበሩ ይቅርታ እጠይቃለሁ’ ብሏል።

ቢቢሲ ጥልቅ ምርመራ ካደረገው በኋላ ለአልጀዚራ ቴሌቪዥን 22 ክሶችን ያቀረበ ሲሆን እነዚህን ክሶች ጣቢያው አንድ በአንድ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ አድበስብሶ ጠቅለል ያለ ምላሽ ሰጥቷል።

ጸታዊ ትንኮሳ ዕለታዊ ተግባር እንደሆነ የሚናገሩት የአል ጀዚራ ባልደቦች በኳታር ይህን እንደ ችግር ማንሳት ግን የማይታሰብ እንደሆነ ይናገራሉ። 

‘ምራቁን ከፊቴ ላይ መጥረግ ነበረብኝ’

ጋዜጠኛ ሳንታማሪያ በኒውዚላንድ ቴሌቪዥን ከ32 ቀናት በኋላ ሥራ ከለቀቀ በኋላ በፈረንጆቹ 2005 ነበር አልጀዚራን የተቀላቀለው።

ወዲያውኑ ዜናና የቀጥታ ሥርጭቶችን ማስተናገድ ጀመረ።

እሱን የሚያውቁት ባልደቦቹ፣ ቀለል ያለ፣ተጫዋች፣ ወዲያው መግባባት የሚችል እና 'ጎበዝ የቴሌቪዥን ባለሙያ' እንደሆነ ይመሰክሩለታል።

ሳንታማሪያ አልጀዚራ በተቀጠረበት ሰዓት ቶሪ ገና ወጣት የቴቪ ፕሮዲዩሰር ነበረች።

‘አንዳንድ ነገር እናድርግ እንጂ...ለበዓል ምነው ቤትሽ ሳትጋብዥኝ ’ እያለ አጭር የጽሑፍ መልዕክት በትዊተርና በዋትስአፕ ይልክልኝ ነበር ትላለች።

ቢቢሲ ለዚህች ባልደባው የላከላትን መልእክት በመመልከት ክሷ እውነተኛ እንደሆነ ማረጋገጥ ችሏል።

ቶሪ እንደምትለው የሳንታማሪያ ጾታዊ ትንኮሳ በአጭር የጽሑፍ መልዕክት አልቆመም።

‘ቢሮ ውስጥ ይነካካኛል፣ እጁን ሆን ብሎ ጀርባዬ ላይ ያሳርፋል’ ትላለች።

ከዚህ ሁሉ የከፋው ያለፈቃዷ በሳማት ጊዜ ነበር።

‘...ከአንድም ሁለት ሦስት ጊዜ ምራቁን ከፊቴ ለመጥረግ መታጠቢያ ቤት መሄድ ነበረብኝ’ ብላለች የሳንታማሪያን ገደብ የለሽ ጾታዊ ትንኮሳ ለቢቢሲ ስታብራራ።

ሌላ የአልጀዚራ ባልደረባ ሳንታማሪያ አብረውት በቲቪ ስለሚያቀርቡ ሴት ባልደቦቹ የጡት መጠን በተደጋጋሚ አስተያየት ሲሰጥ እንደሰማችው ትናገራለች።

የዶሃው የአልጀዚራ ቢሮ በርካታ ጾታዊ ትንኮሳዎች የሚፈጸሙበት ነው ይላሉ ባልደረቦች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዶሃው የአልጀዚራ ቢሮ በርካታ ጾታዊ ትንኮሳዎች የሚፈጸሙበት ነው ይላሉ ሠራተኞች

‘ከንፈሬን በድንገት ሳመው’

ሌላ ወንድ የአልጀዚራ ባልደረባ በበኩሉ ሳንታማሪያ በአንድ ወቅት በዜና ክፍል አብረው እየሠሩ ሳለ በድንገት ከንፈሩን እንደሳመው ይናገራል።

ይህ ግለሰብ አሁንም በአልጀዚራ የዜና አርታኢ ሠራተኛ ነው።

ሌላ ሴት ባልደረባው ደግሞ ሕዝብ በተሰበሰበበት ሳንታማሪያ መጥቶ አንገቴ ሥር ስሞኛል ብላለች።

“በወቅቱ ከፍተኛ ድንጋጤና ሐፍረት ነበር የተሰማኝ፤ ሰዎች ከርሱ ጋር ግንኙነት ያለን ሊመስላቸው ይችል ይሆን ብዬ አሰብኩ። እሱን ለአለቃ የምከስበት ዕድል አልነበረም’ ትላለች።

ብዙዎቹ ትንኮሳ ያደረሰባቸው ባልደቦቹ ለምን ለበላይ እንዳልከሰሰቱ ከቢቢሲ ሲጠየቁ፤ 'እሱ ኃያልና ዝነኛ ስለሆነ...' ለአስተዳደር በርሱ ላይ ክስ መመስረት ከባድ እንደሆነ ነው የሚያብራሩት።

ፊዮና የተባለች ሌላ ወጣት በአልጀዚራ በልምምድ ላይ ሳለች እያቀፈ ያስቸግራት እንደነበረ፣ ጸያፍ ወሲባዊ መልእክቶችን ይልክላት እንደነበረ ታስታውሳለች።

ያደረሰብኝን ነገር መካከለኛ ደረጃ ላለ አለቃ ተናግሬ ነበር፤ ‘አሁንም ቀጥሏል ትንኮሳው፤ እስከአሁን እንኳ ቆሟል መቼስ...’ ብሎኝ አፊዞብኝ አለፈ ትላለች ፊዮና።

ከዚያ በኋላ ነገሩን ለሰው ሃብት አስተዳደር ለማመልከት ፈልጌ 'አንቺ የአጭር ጊዜ ኮንትራት ስላለሽ ያን ማድረግ አትችይም' ተባልኩ ብላለች።

‘ሥራዬን አጣለሁ ብዬ ፈራሁ’

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ብዙዎቹ ትንኮሳ የደረሰባቸው የአልጀዚራ ባልደረቦቹ የደረሰባቸውን ጾታዊ ጥቃት ለበላይ አለቃ መናገር ያልቻሉት ሥራችንን እናጣለን በሚል ነው።

በአልጀዚራ ውስጥ ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር አለመኖሩም ፍርሃት ፈጥሮባቸዋል።

በአልጀዚራ ይህ ትንኮሳን ቸል ብሎ የማየቱ ጉዳይ ይኑር እንጂ በኒዊዚላንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ ግን አልሆነም።

ጋዜጠኛ ሳንታማሪያ ለወር ያህል ብቻ በሠራበት ኒውዚላንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ ክስ ቀርቦበት፣ ጉዳዩ ወዲያውኑ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ከተደረገ በኋላ እርሱን የቀጠረው ሰው ራሱ በፍጥነት ከሥራ እንዲባረር ተደርጓል።

በአልጀዚራ ያለው የጸታ ትንኮሳ ምን ያህል እንደተነሰራፋ የሚናገሩ ብዙ ጋዜጠኞች አሉ።

ይህ ጸታዊ ትንኮሳን የጋዜጠኛ ሳንታማሪያ ጉዳይ ብቻ አለመሆኑን የምትናገር አንዲት ሴት ሌላ አለቃዋ ሚስቱ በሌለች ጊዜ ሁሉ ቤቱ እንድትመጣ እንደሚጋብዛት ተናግራለች።

ሌላኛው የአልጀዚራ ሴት ጋዜጠኛ በበኩሏ ስለ አለቃዋ ስትናገር ‘በረመዳን ወሲብ ካልፈጸምን ይለኛል...’ ነገሩን ባመለክት ግን ሥራዬን አጣለሁ ብዬ ፈራሁ' ትላለች።

ቢቢሲ ይህ በአልጀዚራ ቢሮ የሚፈጸመው ጾታዊ ትንኮሳ በዶሃ ብቻ ሳይሆን በለንደን ቢሮም እንደሚታይ መረጃ አግኝቷል።

ሆኖም በዶሃ ቢሮ ከሌሎች ቅርንጫፍ ቢሮዎች የበዛ ጸታዊ ትንኮሳዎችና ዘረኝነቶች እንደሚንጸባረቁ ሠራተኞች ይናገራሉ።

ቅሬታ ማቅረብ ለምን እንደሚፈሩ ሲናገሩ፣በዶሃ ብዙ ነገሮች ከቅጥር ጋር የተሳሰሩ እንደሆኑ ያሰምሩበታል።

 ከሥራ መባረር ማለት የመኖርያ ፍቃድን ያስነጥቃል፣የልጆች ትምህርት ቤት እና መኖርያ ቤት፣ የጤና መድኅንን ሁሉ ያሳጣል።

ስለዚህ ሠራተኞች ጾታዊ ትንኮሳን ሪፖርት ማድረግ እጅግ ይፈራሉ።

ምንም እንኳ አልጀዚራ ጣቢያ ነጻና ገለልተኛ ሚዲያ ነኝ ቢልም የገንዘብ ምንጩ ከኳታር ኢሚር ስለሆነ በኳታር ጉዳይ ላይ ጋዜጠኞቹ ደፍረው የፈቀዱትን መዘገብ አይችሉም።

የአገሪቱም ሕግም ቢሆን የመናገር ነጻነትን አይፈቅድም።

አልጀዚራ ከቢቢሲ ለቀረቡ ክሶች በሰጠው ምላሽ ‘ጾታዊ ትንኮሳዎችን በተመለከተ በሠራተኞች የሚቀርቡ ክሶችን እንደዋዛ እንደማይመለከት ጠቅሶ ጉዳዩን እንደሚመረምረው ገልጧል።

የአልጀዚራ ባልደረቦች እንደሚናገሩት ከሆነ ይህ ምላሽ ለወጉ ያህል የተባለ ነው። ምክንያቱም ለዘመናት ቅሬታ ቀርቦ የተለወጠ ነገር የለም።

በአልጀዚራ ቢሮ ‘አንዳንድ ሠራተኞች ከሕግ በላይ ናቸው።'