ኤርዶዋን በማዕድን ስፍራ የደረሰው አደጋ “ዕጣ ፈንታ ነው” ማለታቸው ተቃውሞ አስነሳባቸው

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን

የቱርኩ ፕሬዝዳንት 41 ማዕድን አውጪዎች የሞቱበትን ፍንዳታ “ከዕጣ ፈንታ" ጋር ማያያዘቸው እና እንዲህ አይነት አደጋዎች "ሁልጊዜም ይኖራሉ" ማለታቸው ትችት አስከትሎባቸዋል። 

የረሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን አስተያየት በኢስታንቡል ተቃውሞ ቀስቅሷል። አንዳንዶችም በሰሜናዊ ቱርክ የደረሰውን አደጋ “እልቂት” ሲሉ ገልጸውታል።

የሟች ዘመዶች እንዳሉት ከሆነ ማዕድን አውጪዎቹ ከአንድ ሳምንት በላይ ስፍራው የጋዝ ሽታ ነበረው።

አርብ ዕለት በጥቁር ባህር ላይ በሚገኘው ማዕድን ማውጫ በደረሰው ፍንዳታ 28 ሰዎች ቆስለዋል።

ኤርዶዋን ተቃውሞ ያስከተለባቸውን አስተያየት የሰጡት ቅዳሜ ዕለት በባርቲን ግዛት የሚገኘውን የማዕድን ማውጫ ስፈራን በጎበኙበት ወቅት ነው።

በነፍስ አድን ሠራተኞች ተከበው ለጋዜጠኞች "እኛ በዕጣ ፈንታ የምናምን ሰዎች ነን። እንዲህ ያሉ አደጋዎች ሁልጊዜም ይኖራሉ፣ እኛም ይህን ማወቅ አለብን” ብለዋል።

ሆኖም ግን "ጉድለቶችን ወይም አላስፈላጊ አደጋዎችን" ማየት እንደማይፈልጉ መናገራቸውንም ዩሮ ኒውስ ዘግቧል። 

አስተያየቱ ግን ብዙዎችን አስቆጥቷል። የተቃዋሚ መሪው ከማል ኪሊዳሮግሉ "በየትኛው ክፍለ ዘመን ነው የምንኖረው?" የሚለውን ማወቅ እፍልጋለሁ ሲሉ ጠይቀዋል።

"ለምንድነው የማዕድን አደጋዎች በቱርክ ብቻ የሚከሰቱት?" ሲሉም ጠይቀዋልብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የቱርክ መሐንዲሶች እና አርክቴክቶች ህብረትን የሚመሩት ኢሚን ኮራማዝ በትዊተር ገጻቸው ላይ “መቶ ሜትሮችን ወደሚርቁ ጉድጓዶች አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሳያደርጉ፣ ሳይፈተሹና ሳይመረመሩ ተልከዋል” በማለት ፍንዳታው እንደ አደጋ ሊገለጽ ይችላል የሚለውን ሃሳብ ውድቅ አድርገውታል።

መንግሥት የፍንዳታው ምክንያት እስካሁን አላስታወቀም። የቱርክ አቃቤ ህጎች የፍንዳታው መንስኤ ላይ ምርመራ መጀመራቸውን የሃገሪቱ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

ቁጣቸው ያልበረደላቸው የተጎጂ ቤተሰቦች ግን ጋዝ ይሆናል ሲሉ ይጠራጠራሉ። በፍንዳታው ከሞቱት አንዱ የሆነው እና በ20ዎቹ መጀመሪያ የሚገኝ ግለሰብ አባት ለፓኪስታኑ አሶሺየትድ ፕሬስ እንደገለጹት ልጁ ለ10 ቀናት ያህል ጋዝ ሲሸተው መቆየቱን ተናግረዋል።

ወንድሟን በአደጋው ያጣች አንዲት ሴት ለፕሬዝዳንት ኤርዶዋን "ከ10 እና 15 ቀናት በፊት የጋዝ መፍሰስ እንዳለ ተናግሯል። ‘እዚሁ ያፈነዱናል’ ብሎ ነበር” ስትል ተናግራለች። 

ከአፍታ ዝምታ በኋላ ኤርዶሃን “በህይወት ስላጣችሁት ይቅርታ አላህ ምህረቱን ይስጣችሁ” ሲሉ መመለሳቸው የዜና ወኪል አጃንስ ዘግቧል።

ፍንዳታው በደረሰበት ወቅት 110 የሚጠጉ ሰዎች በማዕድኑ ስፍራ ነበሩ። ግማሽ የሚያህሉት ከ300 ሜትር በላይ ጥልቀት ያለው ስፍራ ውስጥ ነበሩ። ፍንዳታው ሲያጋጥም በማዕድን ማውጫው ይሠሩ የነበሩ 58 ሰዎች በነፍስ አድን ሠራተኞች ድነዋል ወይም ራሳቸውን አወጥተዋል።

ማዕድን ማውጫው በመንግሥት ባለቤትነት የሚተዳደረው የቱርክ ሃርድ ኮል ኢንተርፕራይዞች ነው።

ቱርክ እአአ በ2014 በከሰል ማዕድን ማውጫ ስፍራ በታሪኳ እጅግ አስከፊ የተባለውን አደጋ አስተናግዳለች። በምዕራብ ሶማ ከተማ በደረሰ ፍንዳታ 301 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።