እስራኤል እና ሐማስ ስምምነት ላይ ከመድረሳቸው በፊት የነበሩ ቁልፍ ክስተቶች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እስራኤል እና ሐማስ በአሜሪካ እና ኳታር አደራዳሪነት የተኩስ አቁም፣ የታጋቾች እና የእስረኞች ልውውጥ ለማድረግ ተስማምተዋል።
የስምምነቱ የመጀመሪያው ምዕራፍ ዛሬ እሁድ ጥር 11/2017 ዓ.ም. ተግባራዊ ይደረጋል።
እስራኤል እና የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን እና ፖለቲካዊ ንቅናቄ የሆነው ሐማስ ላለፉት 15 ወራት ጦርነት ላይ ነበሩ።
ይህ ጦርነት የተጀመረው በመቶዎች የሚቆጠሩ የሐማስ ታጣቂዎች ወደ ደቡባዊ እስራኤል ዘልቀው ገብተው ጥቃት በማድረስ 1200 ሰዎች ገድለው ከ250 በላይ የሚሆኑ ሰዎችን አግተው ከወሰዱ በኋላ ነው።
እስራኤል ይህን ጥቃት ተከትሎ ወዲያውኑ የአየር ጥቃት ከፈፀመች ከቀናት በኋላ እግረኛ ጦሯን ይዛ ወደ ጋዛ ዘልቃለች።
ከዚህ በኋላ እስራኤል ጋዛ ላይ በመሬት፣ በባሕር እና በአየር ጥቃት ስትፈጽም ሐማስ ደግሞ በሮኬት እስራኤል ላይ ጥቃት ሲሰነዝር ቆይቷል።
በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር እንደሚለው በእስራኤል ጥቃት ምክንያት ከ46 ሺህ በላይ ሰዎች ሲገደሉ አብዛኞቹ ሰላማዊ ሰዎች ናቸው።
ለመሆኑ እስራኤል እና ሐማስ አሁን እንዴት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ሊደርሱ ቻሉ?
በአውሮፓውያኑ 2023
ጥቅምት 7፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሐማስ ታጣቂዎች በደቡባዊ እስራኤል በኩል ዘልቀው ገብተው በአካባቢው ያሉ ሰዎች፣ የፖሊስ ጣቢያዎች እና የጦር ካምፖች ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት ፈፀሙ።
በጥቃቱ 1200 የሚሆኑ ሰዎች ሲገደሉ 251 ሰዎች ደግሞ ታግተው ወደ ጋዛ ተወሰዱ። ሐማስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን እስራኤል ላይ ተኩሷል።
የእስራኤል ጦር ኃይል በምላሹ ፈጣን የአየር ድብደባ ፈፀመ።
ጥቀምት 27፡ እስራኤል ጋዛን ወረረች። በዚህ ወረራ አብዛኛው የጋዛ ክፍል ሲወድም ከ2.3 ሚሊዮን በላይ ፍልስጤማውያን ተሰደዱ። በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር እንደሚለው በእስራኤል ጥቃት ከ46 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
ኅዳር 21፡ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በኳታር እና በግብፅ አደራዳሪነት ሐማስ ከታጋቾቹ መካከል 105 ሰዎች ሲለቅ እስራኤል ደግሞ 240 ፍልስጤማውያንን ከእስር ፈታች። እስራኤል እና ሐማስ በወቅቱ የደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነት ለአንድ ሳምንት የዘለቀ ነበር። ለተኩስ አቁሙ መፍረስ አንዱ አንደኛውን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
ታኅሣሥ 28፡ አዲስ የተኩስ አቁም እና የታጋቾች ለመለቀቅ ድርድር መደረግ ተጀመረ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአውሮፓውያኑ 2024
ግንቦት 21፡ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በሦስት ምዕራፎች የሚከናወን እስራኤልን የሚወክል የተኩስ አቁም ሐሳብ አቅርበው ታጋቾች እንዲለቀቁ ጠየቁ። ይህ ሐሳብ አሁን ለተደረሰው ስምምነት መሠረት እንደሆነ ይታመናል።
ሰኔ 10፡ የተባበሩት መንግሥት የፀጥታው ምክር ቤት የጋዛው ጦርነት እንዲቆም የተቀረበውን የተኩስ አቁም ሐሳብ የሚደግፍ ውሳኔ አሳለፈ።
ሐምሌ 31፡ እስራኤል የሐማስ የፖለቲካ ክንፍ መሪ እና ዋና ተደራዳሪ የነበሩት ኢስማኢል ሃኒያን በኢራን መዲና ቴህራን መግደሏን ተከትሎ ድርድሩ ተቋረጠ። ድርድሩ ሐማስ ባልተገኘበት ከሁለት ሳምንታት በኋላ ድጋሚ ተጀመረ።
ጥቅምት 17፡ የእስራኤል ጦር የሐማሱ መሪ ያህያ ሲንዋር በደቡባዊ ጋዛ መገደሉን አስታወቀ። ኔታኒያሁ ግድያውን የጦርነቱ "የመጨረሻው መጀመሪያ" ሲሉ ገለፁት።
ኅዳር 9፡ ከወራት ሙከራ በኋላ ኳታር ከተኩስ አቁሙ ድርድሩ ራሷን ማግለሏን አስታወቀች። ኳታር በወቅቱ እስራኤል እና ሐማስ አቋማቸውን ለመቀየር ዝግጁ መሆን አለባቸው ብላ ነበር። ሐማስ እና እስራኤል እርስ በርስ ተወነጃጀሉ።
ኅዳር 27፡ እስራኤል ከሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሔዝቦላህ ጋር የነበራውን የ13 ወራት ግጭት በመግታት የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ተስማማች። ሔዝቦላህ ሐማስ ላይ በተሰነዘረው ጥቃት ምክንያት ነው ወደ ግጭቱ የገባው። ይህን ተከትሎ ባይደን ድጋሚ ሐማስ እና እስራኤል እንዲስማሙ ለማድረግ እንደሚሠሩ አስታወቁ።
ታኅሣሥ 2፡ ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን ከመጨበጣቸው በፊት ጋዛ የሚገኙ ታጋቾች ካልተመለሱ "ገሀነም ይወርዳል" ሲለ አስጠነቀቁ።
ታኅሣሥ 17፡ የፍልስጤም ከፍተኛ ባለሥልጣን ድርድሩ "የመጨረሻውን ምዕራፍ" ላይ ደርሷል ሲሉ የእስራኤሉ መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ በበኩላቸው ወደ ስምምነት መቃረባቸውን አስታወቁ።
በአውሮፓውያኑ2025
ጥር 13፡ ባይደን በመጨረሻው ሳምንት የሥልጣን ዘመናቸው ከኔታንያሁ ጋር በስልክ ሲመክሩ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊከን ስምምነቱ ሊደረስ "ተቃርቧል" ሲሉ ተናገሩ።
ጥር 15፡ የኳታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር እስራኤል እና ሐማስ የተኩስ አቁም ለማድረግ መስማማታቸውን አስታወቁ። አክለው ታጋቾች እንደሚለቀቁ እና ስምምነቱ ከጥር 19 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ተናገሩ።












