የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ማን ሊያነሳ ይችላል? የትኞቹ ቡድኖችስ ከሊጉ ይወርዳሉ?

የአርሰናሉ አማካይ ኦዴጋርድ እና የሲቲው አጥቂ ሃላንድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የ2024/25 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ አርብ ምሽት ማንቸስተር ዩናይትድ ከፉልሃም በሚያደርጉት ግጥሚያ ይጀመራል።

የቢቢሲው የእግር ኳስ ፀሐፊ ፊል ማክነልቲ ተሳታፊ ቡድኖች የሚኖራቸውን ደረጃ እንደሚከተለው ገምቷል።

1. ማንቸስተር ሲቲ

ያለፈው ዓመት ደረጃ፡ ሻምፒዮን

ማንቸስተር ሲቲ ለዋንጫ ያለው ፍላጎት ቡድኑ ለተከታታይ አራተኛ ዓመት ሻምፒዮን እንዲሆን አድርጎታል።

ከጁሊያን አልቫሬዝ ውጪ ሌሎቹን ኮከቦች ማቆየት የቻለው ቡድኑ ሌሎች ተጫዋቾችንም የማስፈረም አቅም አለው።

እንደኦስካር ቦብ እና ጀምስ ማክአቲ ያሉ ተስፈኛ ወጣት ተጫዋቾችን ይዟል።

ሲቲ ዋንጫ የማያገኝበት ውድድር ዓመት ቢኖርም ዘንድሮ ግን ሻምፒዮን ከመሆን የሚያግደው ነገር የለም።

2. አርሰናል

ያለፈው ዓመት ደረጃ፡ ሁለተኛ

የማይክል አርቴታ ቡድን ባለፈው ዓመት ጠንካራ ፉክክር ቢያደርግም ሲቲን ከመንበሩ የሚያስነሳ ሊሆን አልቻለም።

ቡድኑ ካለው አቅም አንጻር ዘንድሮም ሲቲን እንደሚፎካከር አምናለሁ።

ጠንካራው ተከላካይ ክፍሉ በሪካርዶ ካላፊዮሪ ይበልጥ ቢጠናከርም ችግር ያለበትን የአጥቂውን ክፍል ለማጠናከር በዝውውር መስኮቱ መሥራት ግድ ይለዋል።

ለሊጉ ባይሆንም ለዋንጫ መፎካከር ይችላል። ያለፈው የውድድር ዓመት ሻምፒዮንስ ሊግ ጉዟቸውም ጥሩ ተሞክሮ ይሰጣቸዋል።

3. ሊቨርፑል

ያለፈው ዓመት ደረጃ፡ 3ኛ

አርን ስሎት የቀድሞውን አሠልጣኝ የርገን ክሎፕን የመተካት ከባድ ኃላፊነት ቢጣልባቸውም የተረከቡት ድንቅ ቡድን ነገሮችን ያቀልላቸዋል።

ቡድኑ እንደ ሞሐመድ ሳላህ፣ አሊሰን. . . ካሉት ኮከቦች በተጨማሪ ተስፈኛ ወጣቶችን ይዟል።

ማርቲን ዙቢሜንዲ በክለቡ በመቆየት የሊቨርፑልን የእናስፈርምህ ጥያቄ ውድቅ ማድረጉ፤ ስድስት ቁጥር ላይ ሌላ ተጫዋች እንዲፈልጉ ያስገድዳቸዋል።

ቡድኑ ተጫዋቾችን ባያስፈርምም ያሉት ኮከቦች ጠንካራ ስለሚያደርጉት ቡድኑ እስከ አራተኛ ያያለውን ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ ያግዙታል።

አዲሱ የሊቨርፑል አሰልጣኝ አርን ስሎት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አዲሱ የሊቨርፑል አሠልጣኝ አርን ስሎት

4. አስቶን ቪላ

ያለፈው ዓመት ደረጃ፡ አራተኛ

ባለፈው ዓመት ቡድኑ ባጠናቀቀበት አራተኛ ደረጃ ለመቆየት የሚያስችል ቡድን እና አሠልጣኝ አለው።

ዳግላስ ሉዊዝ ክለቡን ቢለቅም ኦሊ ዋትኪንሰን የመሰለ ድንቅ ፊት መስመር ተጫዋች አላቸው።

አማዱ ኦናና፣ ሮዝ ባርክሌይ እና ኢያን ማስቲንን ማስፈረምም ችለዋል።

የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ቡድኑ ላይ ጫና ቢፈጥርም ቡድኑ እስከ አራት ያለውን ደረጃ ይዞ እንደሚያጠናቅቅ እገምታለሁ።

5. ማንቸስተር ዩናይትድ

ያለፈው ዓመት ደረጃ፡ 8ኛ

አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ አዲስ ኮንትራት ቢፈርሙም ስለቆይታቸው የሚነሳው ጥያቄ ለማስቀረት ድንቅ አጀማመር ማድረጋቸው ተጠባቂ ነው።

ጨዋታ ቀያሪ የሚባሉ ተጫዋቾችን ያላስፈረመው ዩናይትድ አዲስ ፈራሚውን ሌኒ ዮሮን በጉዳት አጥቶታል።

ቴንሃግ ተከላካዩ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ ከጉዳት ነጻ እንዲሆን ተስፋ ያደርጋሉ። በጁቬንቱስ እና ባየር ሙኒክ የሚጠበቀውን ያህል ያልሆነውን ማቲያስ ደሊትን በአያክስ በነበራቸው ቆይታ ያውቁታል።

ማርከስ ራሽፎርድ ወደ ብቃቱ ይመለሳል ወይ? የጄደን ሳንቾ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? ጆሹዋ ዘርከሲስ ምን ዓይነት ሚና ይኖረዋል? የሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ ይፈልጋሉ።

ቡድኑ እንደኮቢ ማይኑ እና አሊሃንድሮ ጋርናቾ ያሉ ወጣት ኮከቦችን በመያዙ ካለፈው ዓመት የተሻለ ውጤት ያስመዘግባል።

6. ቶተንሃም ሆትስፐር

ያለፈው ዓመት ደረጃ፡ 5ኛ

ቶትንሃም ባለፈው ዓመት ከነበረው መሻሻል አንጻር እስከ አራተኛ ደረጃ ያለውን አለመያዙ የሚያስቆጭ ነው።

አንጅ ፖስትኮግሉ ማጥቃት ላይ መሠረት ያደረገው አጨዋወታቸው በሁለተኛው የውድድር ዓመቱ አጋማሽ ተጋለጭ ሆኗል።

ዶምኒክ ሶላንኬ እና እርቺ ግሬይን መሳሰሉ ተጫዋቾችንም ወደ ቡድኑ ቀላቅለዋል።

ሶን ሁንግ-ሚንን እና ሌሎች አስደናቂ ተጫዋቾችን የያዘው ቡድን እስከ ስድስት ያለውን ደረጃ ይዞ የማጠናቀቅ አቅም አለው።

ብዙ እየተባለለት ያለው የ17 ዓመቱ ሚኪ ሙርን የምንመለከትበት ዓመት ይሆናል።

7. ቼልሲ

ያለፈው ዓመት ደረጃ፡ 6ኛ

አይደለም የቼልሲን የአንድ ዓመት ጉዞ የ20 ደቂቃ ውጤቱን መገመት ከባድ ነው።

አዲስ ዓመት አዲስ አሠልጣኝ። ኤንዞ ማሬስካ ድንቅ ብቃት ባላቸው በርካታ ተጫዋቾች የተሞላ ስብስብ አላቸው።

ኮል ፓልመርን ጨምሮ የሌሎችን ድንቅ ብቃት መጠቀም ከቻሉ አሠልጣኙ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ይችላሉ።

ማሬስካ ብዙ ማስመስከር የሚገባቸው ጉዳዮች ይጠብቋቸዋል።

የቼልሲው ኮል ፓለመር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቼልሲው ኮል ፓለመር

8. ዌስት ሃም

ያለፈው ዓመት ደረጃ፡ 9ኛ

ዩሊየን ሌፕቴጉ አሠልጣኝ ዴቪድ ሞዬስን ተክተው ዌስት ሃም ደርሰዋል። ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች አሏቸው።

ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾችንም ለማስፈረም ችለዋል።

አሠልጣኙ ያላቸውን ቡድን በደንብ መጠቀም የሚችሉ ከሆነ ለዌስት ሃም ጥሩ የውድድር ዓመት ይሆናል።

9. ኒውካስል

ያለፈው ዓመት ደረጃ፡ 7ኛ

ኒውካስል ቤት ከመጋረጃ ጀርባ ብዙ ለውጦች ተከናውነዋል። የቦርድ አባላት እና የስፖርት ዳይሬክተሮች ተቀይረዋል።

ቡድኑ በፋይናንስ ሕግ ምክንያት እንደፈለገው ተጫዋቾችን ማስፈረም አልቻለም።

አሠልጣኝ ኤዲ ሃው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንን ይረከባሉ መባሉም ቡድኑ እንዳይረጋጋ ያደርጋል።

ተከላካዩን ማርክ ጉሄይን ከፓላስ ማስፈረም ከቻሉ ቡድኑ አለመረጋጋት ውስጥ ቢሆንም እስከ አስር ያለውን ደረጃ ይዞ የማጠናቀቅ ዕድል አለው።

10. ክሪስታል ፓላስ

ያለፈው ዓመት ደረጃ፡ 10ኛ

ፓላስ ያለፈው የውድድር ዓመት እንዲጠናቀቅ የሚፈልግ ቡድን አይመስልም። ኤበረቺ ኤዜ፣ ዢን ፊሊፔ ማቴታ እና ማይክል ኦሊሴ ከወጣቱ አዳም ዋርትን ጋር በመሆን አስደናቂ እና በርካታ ጎሎችን የሚያስቆጥር ቡድን ሆኖ ነበር።

ኦሊሴ ባየር ሙኒክን ተቀላቅሏል። ጉሄይ ኒውካስልን ሊቀላቀል ይችላል። አሠልጣኝ ኦሊቨር ጋልስነር ቀሪውን ቡድን ይዘው የመቆየት ግዴታ ይኖርባቸዋል።

ቡድኑ አንድ ላይ ከዘለቀ የአሠልጣኝ ጋልስነር በማጥቃት ላይ የተመሠረተ አጨዋወት ሌላ ምርጥ የውድድር ዓመትን ለቡድኑ ሊፈጥር ይችላል።

11. ኤቨርተን

ያለፈው ዓመት ደረጃ፡ 15ኛ

በፋይናንስ ሕግ ጥሰት ምክንያት 8 ነጥብ የተቀነሰበትን ቡድን ለማቆየት አሠልጣኝ ሾን ዳይሽ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም።

ጃራድ ብራንትዌት፣ ጀምስ ታርኮውስኪ እና ጆርዳን ፒክፎርድን የመሳሰሉ ተጫዋቾችን ለማቆየት ችለዋል። ጃክ ኦብሪያንን ደግሞ አስፈርመዋል።

አማዱ ኦናና ደግሞ በ50 ሚሊዮን ፓውንድ አስቶን ቪላን ተቀላቅሏል።

ቡድኑ ጎል የማስቆጠር ችግሩን ቀርፎ የተወሰኑ ተጫዋቾችን ካስፈረመ ኤቨርተን እንዳለፈው ዓመት የሚቸገር አይመስለም።

አሠልጣኝ ሾን ዳይሽ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አሠልጣኝ ሾን ዳይሽ

12. ብራይተን

ያለፈው ዓመት ደረጃ፡ 11ኛ

አሠልጣን ሮቤርቶ ዲ ዘርቢ ተሰናብተው በ31 ዓመቱ ፋብያን ሃርዝለር እንዲተኩ ተደርጓል።

አዲሱ አሠልጣኝ ተስፋ የሚጣልበትን ስብስብ የሚረከቡ ይሆናል።

በ25 ሚሊዮን ፓውንድ ማትስ ዋይፈርን ከፌይኖርድ አስፈርመዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት እንደነበረው እስከ ስድስት ያለውን ደረጃ ይዘው ባያጠናቅቁም ብራይተን ለማየት የሚስብ ቡድን ሆኖ ይቀጥላል።

13. ፉልሃም

ያለፈው ዓመት ደረጃ፡ 13ኛ

ባለፈው ዓመት አጥቂያቸው አሌክሳንደር ሚትሮቪችን ቢያጡም ጥሩ የሚባል ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። ዘንድሮም ጆአኦ ፓሊንሃ፣ ቶሲን አዳራቢዮ እና ቲም ሪምን ቢያጡም አሠልጣኝ ማርኮ ሲልቫ ውጤታቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል።

ተመሳሳይ ፈተናዎችን በማለፍ የሚታወቁት ሲልቫ ከአርሰናል ኤሚል ስሚዝ ሮውን አስፈርመዋል።

ሪያን ሴሴኞንም ከቶተንሃም ቡድኑን በድጋሚ ተቀላቅሏል።

ብዙ ነገር በአሠልጣኙ ላይ የሚወሰን ቢሆንም ቡድኑ የተረጋጋ ውድድር ዘመን ያሳልፋል።

14. በርንመዝ

ያለፈው ዓመት ደረጃ፡ 12ኛ

ባለፈው ዓመት 19 ጎሎችን ያስቆጠረው አጥቂው ዶምኒክ ሶላንኬ ክቡን መልቀቁ ኪሳራ ቢሆንም አሠልጣኝ አንዶኒ ኢይራኦላ አሁንም ተስፈኛ ናቸው።

አሠልጣኙ ባለፈው ዓመት መጥፎ አጀማመር ባይኖራቸውም ባመኑበት መንገድ በመጓዝ አጨራረሳቸውን አሳምረዋል።

የሶላንኬ መልቀቅ አንቶኒ ስሜንዮ እና ሉዊስ ሲንሲቴራ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ከፍ አድርጎታል።

መጪው ጊዜ ከባድ ቢሆንም በኢይራኦላ ስር ቡድኑ ችግሩን ያልፋል።

15. ዎልቨርሃምፐተን ዎንደረርሰ

ያለፈው ዓመት ደረጃ፡ 14ኛ

ጋሪ ኦኔል ቡድኑን ከተረከቡ በኋላ ጥሩ የሚባል ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል።

ማክስ ኪልማን እና ፔድሮ ኔቶን ቢያጡም ቡድኑ ኦኔል ላይ ጥገኛ ይሆናል።

ቶሚ ዶይልን ከማስፈረም በተጨማሪ ሌሎች ዝውውሮችን በማከናወን የውድድር ዓመቱን ውጤታማ ለማድረግ መሥራት አለባቸው።

የዘንድሮው ውጤት በሚያስፈርሟቸው ተጫዋቾች እና በአሠልጣኙ ብቃት ላይ የተንጠለጠለ ይሆናል።

16. ኖቲንግሃም ፎረስት

ያለፈው ዓመት ደረጃ፡ 17ኛ

ኑኖ እስፕሪቶ ሳንቶ 4 ነጥብ የተቀነሰበትን ቡድን በሊጉ ለማቆየት ችለዋል።

ቡድኑ በሜዳው ያለው ድጋፍ ለውጤታማነቱ መሠረት ሆኖ ይቀጥላል። ላለፉት ሁለት ዓመታት የቡድኑ የጀርባ አጥንት የሆነውን ሞርጋን ጊብስ ዋይትን ማቆየታቸውም ተጠቃሽ ነው።

የሙሪሎ በቡድኑ ለመቆየት መፈለግም ሌላው ጠንካራ ጎን ነው።

ቡድኑ ተጫዋቾቹን ማቆየት ከቻለ በሊጉ የመቆየት ዕድል አለው።

17. ብሬንትፎርድ

ያለፈው ዓመት ደረጃ፡ 16ኛ

አጥቂው አይቫን ቶኒ ይለቃል፣ አይለቅም የሚለው ጉዳይ እስከዝውውር መስኮቱ መጨረሻ በእንጥልጥል የሚቆይ ይመስላል።

ቡድኑ ብራዚላዊውን አጥቂ ኢጎር ቲያጎን አስፈርሟል።

አሠልጣን ቶማስ ፍራንክ ጥሩ እየሠሩ ቢቆዩም ዘንድሮ የሚፈተኑበት የውድድር ዓመት ይሆናል።

የፋቢዮ ካርቫልሆ መፈረም እና የብሪያን ምቡሞ እና ቤን ሚ መቆየት ለቡድኑ ጥንካሬ ጠቃሚ ነው።

18. ሳውዝሃምፐተን

ሦስቱ ታላላቅ ቡድኖች ወደ ሊጉ ተመልሰዋል።

በአሠልጣኝ ረስል ማርቲን አስደናቂ አጨዋወት ወደ ሊጉ የተመለሰው ሳውዝሃምፐተን በዚሁ አጨዋወቱ በፕሪሚር ሊጉ ለመቆየት ሊቸግረው ይችላል።

የተለያዩ ተጫዋቾችን ማስፈረም ችለዋል።

በቂ ነው? በቂ ባይመስልም በሴንት ሜሪ ስታዲየም የሚኖረው ድባብ ለተቃራኒ ቡድን ከባድ እንደሚሆን እጠብቃለሁ።

ስቲቭ ኩፐር ሌስተር ሲቲን ይመራሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ስቲቭ ኩፐር ሌስተር ሲቲን ይመራሉ

19. ሌስተር ሲቲ

ሌስተር ወደ ሊጉ ቢመለስም የነጥብ ቅነሳ ሊኖርበት መቻሉ ግን የውድድር ዓመቱን ከባድ ሊያደርግበት ይችላል።

ተመሳሳይ ጊዜ ያሳለፈውን ኖቲንግሃምን በሊጉ ያቆዩትን ስቲቭ ኩፐርን አሠልጣኝ አድርገው ሾመዋል።

ኩፐር የኮኖር ኮዲ፣ ሃሪ ዊንክስ እና ጂሚ ቫርዲን ልምድ እንደሚጠቁ ይጠበቃል። የውሰት ውሉን ወደ ቋሚነት የቀየረው አብዱል ፋታዉም በደጋፊዎች ይጠበቃል።

ቀበሮዎቹ ዊልፍሬድ ዛሃን እና ፎቲስን ለማስፈረም እየተንቀሳቀሱ ነው።

ኩፐር እና ሌስተር ውጤታማ ሊሆኑ ቢችሉም ከፊታቸው ትልቅ ተራራ አለ።

20. ኢፕስዊች ታውን

የኢፕስዊቹ አሠልጣኝ ኬሪያን ማክኬና በተከታታይ ሁለት ዓመታት ቡድናቸው ከሊግ ዋን ወደ ፕሪሚየር ሊግ በማብቃት ሙገሳ እየተቸራቸው ይገኛል።

ማኬና ትልቅ ግምት ከተሰጣቸው ወጣት አሠልጣኖች መካከል ናቸው።

ቡድኑ ትልቅ ግምት ባይሰጠውም በሊጉ መቆየት ማቻል ትልቅ ስኬት ሆኖ ይቆጠራል።

ሊያም ዴላፕ፣ ጃኮብ ግሪቭስ እና ቤን ጆንሰንን አስፈርመዋል።

ደጋፊዎችም ሆኑ አሠልጣኙ ቡድኑ እንደሚወርድ ባይጠብቁም ኢፕስዊች በሊጉ ከቆየ ትልቅ ፈንጠዝያ ይሆናል።