አገራት በኦሊምፒክ ሜዳሊያ ላስገኙ አትሌቶች ምን ያክል ገንዘብ ይሸልማሉ?

ማን ዋይ ቪቪያን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት ከሚያገኙ መካከል ለሆንግ ኮንግ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘችው አትሌቶች ማን ዋይ ቪቪያን

በኦሊምፒክ መድረክ የአገራቸውን ሰንደቅ ከፍ አድርገው የአገር ኩራት የሚሆኑ አትሌቶች ዳጎስ ያለ ሽልማት ያገኛሉ።

በኦሊምፒክ መድረክ ከሚያገኙት በርካታ የሜዳሊያ ቁጥር አንጻር በሽልማት መልክ ብዙ ወጪ ከሚያወጡ አገራት መካከል አሜሪካ፣ ጣልያን እና ፈረንሳይ ተጠቃሽ ናቸው።

ፎርብስ መጽሔት በፓሪስ ኦሊምፒክ ተሳተፊ ለሆኑ ለሁሉም አገራት እና ግዛቶች ሜዳሊያ ለሚያስገኙ አትሌቶች በሽልማት መልክ የሚያገኙትን የገንዘብ መጠን ጠይቋል።

ለመሆኑ በነብስ ወከፍ ሜዳሊያ ለሚያስገኙ አትሌቶች ከፍተኛ ገንዘብ በጉርሻ መልክ የሚሰጡ አምስት አገራት የትኞቹ ናቸው?

ኢትዮጵያ

ምንም እንኳ በፎርብስ ዘገባ ላይ ኢትዮጵያ ሜዳሊያ ለሚያስገኙ አትሌቶቿ ምን ያህል የገንዘብ ሽልማት እንደምታበረክት የተባለ ነገር ባይኖርም በፓሪስ ኦሊምፒክ ሜዳሊያ ላስገኙ አትሌቶች እና አሠልጣኞች የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ ሰጥታለች።

በዚህ ውድድር ለኢትዮጵያ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ በማራቶን ያስገኘው ታምራት ቶላ ሰባት ሚሊዮን ብር (70 ሺህ የአሜሪካ ዶላር አካባቢ) እና የወርቅ ኒሻን ከአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ተበርክቶለታል።

ቀሪዎቹን የብር ሜዳሊያዎች ላመጡት በሴቶች ማራቶን ሁለተኛ የወጣቸው ትግስት አሰፋ፣ በ10 ሺህ ሜትር ሁለተኛው በሪሁን አረጋዊ እና ኢትዮጵያ እምብዛም በማትታወቅበት በ800 ሜትር በኢሊምፒክ የመጀመሪያውን የብር ሜዳሊያ ያስገኘችው ፅጌ ዱጉማ ለእያንዳንዳቸው 4 ሚሊዮን ብር (40 ሺህ ዶላር) ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ሆንግ ኮንግ

እንደ ፎርብስ መረጃ ወርቅ የሚያስገኙ የሆንግ ኮንግ አትሌቶች እያንዳንዱ 768 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ይሸለማሉ። ብር የሚያስገኙ ስፖርተኛ ደግሞ 394 ሺህ ዶላር ሲያገኙ፤ የነሐሰ ሜዳሊያ ደግሞ 192 ሺህ ዶላር ያስገኛል።

ሆንግ ኮንግ በፓሪስ ኦሊምፒክ ሁለት ወርቅ እና ሁለት ነሐስ ያገኘች ሲሆን፣ የግዛቷ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ለአትሌቶቹ በአጠቃላይ 1.9 ሚሊዮን ዶላር በሽልማት መልክ ይሰጣል።

ሃንጋሪ

ሃንጋሪ ለዋናተኞቿ፣ ለጀልባ ቀዘፋ እና ለሻምብላ ተወዳዳሪዎቿ በፓሪሱ ኦሊምፒክ የተለያዩ በአጠቃላይ 19 ሜዳሊያዎችን ሰብስባለች።

ሃንጋሪ ለወርቅ 165 ሺህ ዶላር፣ ለብር 118 ሺህ ዶላር እና ለነሐሰ ደግሞ 94 ሺህ ዶላር ትሸልማለች።

እስራኤል

በፓሪሱ ኦሊምፒክ አንድ ወርቅን ጨምሮ በአጠቃላይ 7 ሜዳሊያዎችን የሰበሰበችው እስራኤል፤ ለአሸናፊ አትሌቶች ከፍተኛ ገንዘብ ከሚሸልሙ አገራት መካከል አንዷ ነች።

ወርቅ ያስገኘ አትሌት 268 ሺህ ዶላር፣ ብር 188 ሺህ ዶላር እንዲሁም ነሐሰ ያስገኘ 134 ሺህ ዶላር ይሸለማሉ።

እንደ ፎርብስ ከሆነ ሽልማቶቹ ግብር አይከፈልባቸዋል።

ታምራት ቶላ

የፎቶው ባለመብት, world athletics

የምስሉ መግለጫ, ለኢትዮጵያ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ በማራቶን ያስገኘው ታምራት ቶላ

ጣልያን

በዘንድሮ ኦሊምፒክ 40 ሜዳሊያ የሰብሰበችው ጣልያ፤ አሸናፊ አትሌቶቿን ለመሸለም 10.7 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ታደርጋለች።

ወርቅ ያሸነፉ 196 ሺህ ዶላር፣ ብር ያመጡ 98 ሺህ ዶላር እንዲሁም ነሐስ ያገኙ 65 ሺህ ዶላር ይሸለማሉ።

በጣልያን አትሌቶች ባሸነፉት የሜዳሊያ ልክ ሽልማታቸውን ይቀበላሉ። እንደ ምሳሌም በፓሪሱ ኦሊምፒክ የጂምናስቲክ ስፖርተኛዋ አሊስ ደአምቶ ወርቅ እና ብር ማግኘቷን ተከትሎ ወደ 300 ሺህ የሚጠጋ ዶላር በጉርሻ መልክ ትቀበላለች።

ዩክሬን

ጦርነት ውስጥ የምትገኘው ዩክሬን በኦሊምፒክ የተሳትፎ ታሪኳ አነስተኛ የሆኑ 140 አትሌቶችን ወደ ፓሪስ ልካለች።

በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከ500 ያላነሱ አትሌቶች እንደተገደሉባት የምትገለጸው ዩክሬን በፓሪስ ኦሊምፒክ ተሳትፎዋ 12 ሜዳሊያዎቸን መሰብሰብ ችላለች።

በኢሊምፒክ መድረክ ወርቅ የሚያመጣ የዩክሬን አትሌት 125 ሺህ ዶላር በጉርሻ መልክ ይሸለማል። ብር የሚያመጣ 80 ሺህ ዶላር ሲከፈለው፤ ነሐሰ ሜዳሊያ ደግሞ 55 ሺህ ዶላር ያስሸልማል።

አሜሪካ

ምንም እንኳ እንደ ፈረንሳይ፣ ፖላንድ እና ኒው ዚላንድ ያሉ አገራት ከአሜሪካ በላይ ሜዳሊያ ለሚያስገኙ አትሌቶች በነብስ ወከፍ የሚያበረክቱት ገንዘብ ከፍ ያለ ቢሆንም፤ የአሜሪካ መንግሥት በርካታ ሜዳሊያ ያስገኙ አትሌቶች ስላሉት ለሽልማት ከፍተኛውን ገንዘብ ወጪ ያደርጋል።

አሜሪካ በዚህ የፓሪስ ኦሊምፒክም ከፍተኛውን ሜዳሊያ በመውሰድ በውድድሩ የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ላይ ቀዳሚ ሆና መጨረሷ ይታወቃል።

አሜሪካ በዘንድሮ ኦሊምፒክ 40 ወርቅ፣ 44 ብር እና 42 ነሐስ አግኝታለች። በዚህም የአሜሪካ የኦሊምፒክ እና ፓራኦሊምፒክ ኮሚቴ 8.3 ሚሊዮን ዶላር አጠቃላይ ለሽልማት የሚሰጠው ገንዘብ ነው።

እያንዳንዱ አትሌት ወርቅ ካስገኘ 37 ሺህ 500 ዶላር በጉርሽ መልክ ይሰጠዋል። ለብር 22 ሺህ 500 ዶላር እንዲሁም ነሐሰ ያመጣ አትሌት 15 ሺህ ዶላር ይሸለማል።