በኖርዌይ ኢትዮጵያዊቷን 'በዘረኝነት ተነሳስቶ' በስለት የገደላት ግለሰብ በሽብር እንደሚጠየቅ ተዘገበ

የፎቶው ባለመብት, sM
በኖርዌይ የ34 ዓመቷን ኢትዮጵያዊ የማኅበራዊ ሠራተኛ (ሶሻል ወርከር) 'በዘረኝነት ተነሳስቶ' በተደጋጋሚ በስለት ወግቶ የገደላት የ18 ዓመት ግለሰብ ከግድያ በተጨማሪ በሽብርተኝነት እንደሚከሰስ ተዘገበ።
ታሚማ ኒብራስ ጁሃር የተባለችው ይህች ኢትዮጵያዊት ትሠራበት በነበረው የታዳጊዎች ማዕከል ውስጥ ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ በተደጋጋሚ በስለት ተወግታ መገደሏን ባለሥልጣናት ሰኞ ዕለት ማስታወቃቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
ታሚማ ተጋላጭ ወጣቶችን ከማኅበረሰቡ ጋር ለማዋሃድ በሚሠራ አንድ ማዕከል ውስጥ ትሠራ የነበረ ሲሆን፣ እሷን በመግደል የተጠረጠረው በማዕከሉ ውስጥ ይኖር የነበረ የኖርዌይ ዜጋ ነው።
ታሚማ በኦስሎ ካምፔን በተሰኘ ሰፈር በአንድ የመኖሪያ ተቋም ውስጥ ብቻዋን በሥራ ላይ እያለች ግድያው እንደተፈጸመባት ተዘግቧል።
በዚህ ማዕከል ነዋሪ የሆነው ተጠርጣሪ ከጥቃቱ በኋላ በመዲናዋ ኦስሎ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን፣ በግለሰቧ ግድያም እጁ እንዳለ ማመኑን ፖሊስ ገልጿል።
ጀርመን የተወለደው ይህ ወጣት በርካታ የሕይወት ዘመኑን ያሳለፈው በኖርዌይ ሲሆን፣ ታሚማን በአሰቃቂ ሁኔታ ከገደላት በኋላ ብዙም ሳይቆይ በቁጥጥር ስር መዋሉን የኖርዌይ መገናና ብዙኃን ዘግበዋል።
ግለሰቧ በስለት በሰውነቷ በተለያዩ ክፍሎች ስለመወጋቷም ተነግሯል።
ተጠርጣሪው ከኖርዌይ ካለው የሚዲያ አሠራር ጋር ተያይዞ ስሙ ይፋ አልተደረገም።
በተጠርጣሪው ላይ የቀረበው ክስ ሽብርተኝነትን እንዲያካትት በማድረግ መስፋቱንም ፖሊስ አክሎ ገልጿል።
ግለሰቡ "በምርመራው ወቅት ሌሎች ሰዎችን ለመጉዳት ማቀዱን ተናግሯል" ሲሉ ምክትል ዐቃቤ ሕግ ፊሊፕ ግሪን መግለጻቸው ተዘግቧል።
"በደረስንበት ደረጃ በተወሰነው ማኅበረሰብ መካከል ሽብርን ለመንዛት አቅዷል ብለን እናምናለን፤ ለዚያም ነው የሽብርተኝነት ምርመራ የምንከፍትበት" ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ ዐቃቤ ሕግ ከሆነ ተጠርጣሪው "በሙስሊም ማኅበረሰብ ላይ የጥላቻ አስተያየት ሲሰጥ ተደምጧል።"
ተጠርጣሪው በመስጊድ ላይ ጥቃት ለመንሰዘር ማቀዱን የኖርዌይ መገናኛ ብዙኃን ቢዘግቡም ዐቃቤ ሕግ ይህንን አለማረጋገጡ ተነግሯል።
"በዚህ ሳምንት መጨረሻ አንድ የሚያሳምም እውነት አስታውሰናል። ጥላቻ እና ጽንፈኝነት ሕይወትን ይነጥቃል። ሌሎችን እየረዳች ባለችበት ወቅት ሕይወቷን ያጣችው የታሚማ ግድያ እጅግ አሳዛኝ ነው" ሲል አምነስቲ ኖርዌይ ባወጣው መግለጫ ኃዘኑን አስተላልፏል።
አምነስቲ ሊገለጽ በማይችል ሐዘን ውስጥ ካሉት ለቤተሰቦቿ፣ ለጓደኞቿ እና ለሥራ ባልደረቦቿ መጽናናትን ተመኝቶ "ለደኅንነት፣ ለመከባበር እና ለእኩልነት መቆም የጋራ ኃላፊነታችን ነው" ብሏል።
የሟች ቤተሰብን የወከሉ ጠበቃ በበኩላቸው "ልጃችን፣ እህታችን እና አክስታችንን በማጣችን በጥልቅ ሐዘን፣ ድንጋጤ እና አለማመን ውስጥ ነን" ሲሉ መናገራቸውን በርካታ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ግለሰቡ በኦስሎ ፍርድ ቤት ቀርቦ በነበረበት ወቅት ችሎቱ ለሕዝብም ሆነ ለሚዲያ ዝግ የተደረገ ሲሆን "ግለሰቡ ሚዲያ ባለበት ወቅት ሊገልጽ የሚችለውን ጉዳይ ስለፈራነው ነው" ብለዋል ዐቃቤ ሕግ።
ግለሰቡ ጽንፈኛ የሆኑ መልዕክቶችን እንዳያስተላልፍ የኖርዌይ ባለሥልጣናት ሊገድቡት እንደሚፈልጉ ተነግሯል።
ፖሊስ እና ፒኤስቲ የተሰኘው የኖርዌይ የስለላ ድርጅት የ18 ዓመቱ ወጣት "የቀኝ ክንፍ ጽንፈኛ" እየሆነ ስለመምጣቱ መረጃ እንደደረሳቸው ሚዲያዎች አስነብበዋል።
ታሚማ ኒብራስ ኢትዮጵያ ውስጥ በ1983 እንደተወለደች እና ወደ ኖርዌይም የመጣችው በታዳጊነቷ እንደሆነ በኦስሎ የሚገኘው ኤልደን የተሰኘ የሕግ ተቋም ባልደረባ የሆኑት አኔት ስክጀርቨን ኦርንክቬርን በቤተሰቧ ስም በወጣው መግለጫ አስታውቀዋል።
በኦስሎ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ እያጠናች ከልጆች እና ከታዳጊዎች ጋር ትሠራ እንደነበር መግለጫው አትቶ፤ ሥራዋም ያተኮረው በእኩልነት፣ በዘረኝነት እና በዓለም አቀፍ ግጭቶች ላይ ነበር።
"ቤተሰቧ እንዴት ግድያዋ ሊፈጸም ይችላል" የሚለውን ጭምር መልስ እንደሚፈልጉም መግለጫው አትቷል። በርካቶች ግድያዋን አውግዘው ምላሽ ሰጥተዋል።
ከእነዚህም መካከል የኦስሎ ከተማ አስተዳዳሪ ኢሮክ ላ ሶልበርክ "በካምፔን የተከሰተው ነገር በጣም አሳዛኝ ነው። በኦስሎ ወደ ሥራ መሄድ ችግር ሊሆን አይገባም ነበር" ሲሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
በኖርዌይ እንዲህ ዘርን መነሻ ያደረጉ ጥቃቶች ሲፈጸሙ የመጀመሪያው አይደደለም፤ ከዚህ ቀደምም በርካታ የቀኝ አክራሪ ጥቃቶች ተፈጽመውባታል።
በአውሮፓውያኑ 2011 የቀኝ ክንፍ አክራሪው አንደር ቤህሪንግ ብሬይቪክ በኦስሎ በሚገኝ የመንግሥት መስሪያ ቤት ደጃፍ በአንድ መኪና ላይ ቦምብ በማፈንዳት 77 ሰዎችን መግደሉ ይታወሳል።
ይኸው ግለሰብ በሌበር ፓርቲ የወጣቶች ካምፕ ላይ እሳት ለኩሶ ነበር።
ከአምስት ዓመት በፊት ፊሊፕ ማንሻውስ የተባለ ግለሰብ ከኦስሎ ወጣ ባለ ስፍራ በሚገኝ መስጊድ ላይ ተኩስ ከፍቷል።
በርካቶች ተረባርበው ይህንን ጥቃት በማክሸፋቸው ጉዳት አልደረሰም።
ሆኖም ይህ ግለሰብ በመስጊዱ ላይ ጥቃት ከመክፈቱ በፊት ግማሽ እስያዊ የሆነችውን የማደጎ እህቱን በዘረኝነት ተነሳስቶ ገድሏታል።
ሁለቱም ግለሰቦች 21 ዓመት እስር ተፈርዶባቸዋል።















