በካቴና የታሰረ ታራሚን ደብድበው ለሞት ዳርገዋል የተባሉ አስር የአሜሪካ የእስር ቤት ጠባቂዎች ተከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, New York State Attorney General's Office
ከጥቂት ወራት በፊት በካቴና የታሰረ ታራሚን ክፉኛ ደብድበው ለሞት ዳርገዋል የተባሉ አስር የኒው ዮርክ እስር ቤት ጠባቂዎች ተከሰሱ።
የ43 ዓመቱ ታራሚ ሮበርት ብሩክስ፣ ማርሲ በተሰኘው እስር ቤት በሚገኝ የጤና ማዕከል በመመርመሪያ አልጋ ላይ እጁ በካቴና ታስሮ ተቀምጦ በነበረበት ወቅት የእስር ቤቱ ጠባቂዎች ክፉኛ ሲደበድቡት የተቀረጸ ቪዲዮ አሳይቷል።
ሮበርት ድብደባው በተፈጸመበት ማግስት በማረሚያ ቤቱ ሕይወቱ አልፏል።
ሐሙስ ዕለት ከፍተኛው ፍርድ ቤት የእስር ቤት ጠባቂዎቹን በሁለተኛ ደረጃ የግድያ ወንጀል፣ ለሞት በመዳረግ እንዲሁም ማስረጃዎችን በማጥፋት ከሷቸዋል።
ሐሙስ ዕለት ችሎት ቀርበው የነበሩት ዘጠኙ ፖሊሶች ጥፋተኛ አይደለንም በማለት ቃላቸውን ሰጥተዋል። ሌላኛው ግለሰብ በሚቀጥለው ሳምንት ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።
በፖሊሶች አካል ላይ የሚገጠም የቪዲዮ ካሜራ፣ አንደኛው የእስር ቤቱ መኮንን ሮበርትን ከመደብደቡ በፊት አፉ ውስጥ የሆነ ነገር ሲከትበት ያሳያል። ሌላኛው መኮንን ደግሞ በካቴና የታሰረውን ሮበርት ሆዱ ላይ በጫማ ሲመታው ያሳያል።
ቪዲዮው በተጨማሪም አንደኛው መኮንን አንገቱን አንቆ ካነሳው በኋላ በኃይል የምርመራው አልጋ ላይ ሲጥለው ያሳያል። ሮበርት ለህልፈቱ ምክንያት አንገቱ መታነቁ ወይም 'አስፊክሲያ' መሆኑን የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራዎች አረጋግጠዋል።
አንድ የሕክምና መርማሪ የታራሚውን ሞት ግድያ ነው ሲል አረጋግጠዋል።

የፎቶው ባለመብት, New York State Attorney General's Office
ጉዳዩን እንዲያዩ የተመደቡት ልዩ ዐቃቤ ሕግ ዊልያም ፊትዝፓትሪክ ሮበርት የደረሰበትን አካላዊ ጉዳቶች በዝርዝር ገልጸዋል።
ዐቃቤ ሕጉ ከዘረዘሯቸው ጉዳቶች መካከል የአጥንት እና መገጣጠሚያ ስብራት፣ የውስጥ አካላት ማበጥ እንዲሁም በደረሰበት ተደጋጋሚ መታፈን ከፍተኛ የአእምሮ ጉዳት አስከትለውበታል የሚሉ ናቸው።
ይህ ጥቃት እንዲፈጸም "ሮበርት ምንም አላደረገም። በመጨረሻም በራሱ ደም ተለውሶ ሕይወቱ አለፈ" ሲሉ ልዩ ዐቃቤ ሕጉ ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ተናግረዋል።
የታራሚውን ህልፈት ተከትሎ ብዙም ሳይቆይ የኒው ዮርክ ገዢ ካቲ ሆቹል በጥቃቱ ተሳትፈዋል የተባሉ 13 የፖሊስ መኮንኖች እና የእስር ቤቱ ነርስ እንዲባረሩ አዘዋል።
መኮንንኖቹን የወከለው የኒው ዮርክ ግዛት የማረሚያ ቤት መኮንኖች እና ፖሊሶች ማኅበር ድርጊታቸው "ተቀባይነት የሌለው እና የአብዛኛው አባሎቻችንን የማይገልጽ ነው" ብሏል።
ተከሳሾቹን የወከሉት የሕግ ባለሙያዎች በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሲሆን፤ በታራሚው ህልፈት ላይ የተጀመረው ምርመራ እንደቀጠለ ነው።
የልጁን እናት በስለት በመውጋት አስራ ሁለት ዓመት ተፈርዶበት የነበረው ሮበርት ሕይወቱ ባለፈበት ወቅት የዘጠኝ ዓመት እስሩን ጨርሶ ነበር።
ሟቹ ታራሚ በእስር ላይ ከነበረበት ሞሃውክ ማረሚያ ቤት አቅራቢያው ወደ ሚገኘው ማርሲ ማረሚያ ቤት የተዘዋወረው ጥቃቱ ከተፈጸመበት ሰዓታት በፊት ነበር።












