ተደፍራ የተገደለችውን ህንዳዊት ዶክተር ተከትሎ የአገሪቱ ዶክተሮች የስራ ማቆም አድማ መቱ

የህንድ ዶክተሮች

የፎቶው ባለመብት, EPA

በህንድ ኮልካታ ከተማ በምትሰለጥንበት ሆስፒታል ተደፍራ የተገደለችውን ህንዳዊት ዶክተር ተከትሎ የአገሪቱ ዶክተሮች ብሔራዊ የስራ ማቆም አድማ መቱ።

የሃገሪቱን ዶክተሮች ያሰባሰበው የህንድ ህክምና ማህበር ሁሉም ድንገተኛ ያልሆኑ የሆስፒታል አገልግሎቶች በመላው አገሪቱ ዛሬ አገልግሎት መስጠት እንደሚያቆሙ ገልጿል።

ማህበሩ ባለፈው ሳምንት በባልደረባቸው ላይ የተፈጸመውን ግድያ “አረመኔያዊ ወንጀል” ሲል የጠራው ሲሆን ለሴቶች ደህንነቱ የተጠበቀ ባለመኖሩ እንደተፈጸመም ገልጿል።

ተቋሙ አክሎም ፍትህ ለማግኘት በሚድረገው ትግል ህዝቡ ድጋፍ ድጋፉን እንዲሰጥ ጠይቋል።

የዶክተሯን ግድያ በመቃወም እና ሴቶች የተሻለ ጥበቃ እንዲደረግላቸው የሚጠይቁ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ከቅርብ ቀናት ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ ተቀጣጥለው ይገኛሉ።

ከነዚህ ተቃውሞዎች ጋር በተገናኘ አንድ ሆስፒታል ውድመት እንደደረሰበት ተገልጿል።

የአደጋ እና የድንገተኛ አገልግሎቶች እንደሚቀጥሉ የገለጸው የህክምና ማህበሩ የስራ ማቆም አድማው ለ24 ሰዓታት ይቆያል ብሏል።

በአንዳንድ የመንግሥት ሆስፒታሎች ውስጥ ያሉ ዶክተሮች የስራ ማቆም አድማው ላልተወሰነ ጊዜ እንደሚቀጥል ነው ያስታወቁት።

ማህበሩ የሕክምና ባለሙያዎች ከጥቃት በተሻለ ሁኔታ ለመጠበቅ ሕጉን ማጠናከር፣ በሆስፒታሎች ውስጥ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ጥብቅ ማድረግ እንዲሁም ደህንነቱ የተጠበቀ ቦታዎችን መፍጠርን ጨምሮ ሌሎች ጥያቄዎችን አቅርቧል።

በዶክተሯ ግድያ ላይ “ጥልቅ እና በሞያ የታገዘ ምርመራ” እንዲከፈት እንዲሁም ለሟቿ ቤተሰቦች ካሳ እንዲከፈላቸው ማህበሩ ጠይቋል።

የ31 ዓመቷ ሰልጣኝ ዶክተር መንግሥታዊ በሆነው አርጄ ካር ሜዲካል ኮሌጅ ሆስፒታል ባለፈው ዓርብ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሏን ተከትሎ በአገሪቱ ቁጣ ተቀስቅሷል።

ዶክተሯ እረፍት የለሽ የ36 ሰዓታት የፈረቃ ስራዋን ካጠናቀቀች በኋላ ለመኝታ የተዘጋጀ ስፍራ ባለመኖሩ ስልጠና በሚሰጥበት ክፍል መተኛቷ ተነግሯል።

በማግሥቱ ጥዋት ባልደረቦቿ በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት የደረሰበት እና ግማሽ እርቃን የሆነውን ህይወት አልባ ገላዋን አግኝተውታል።

ፖሊስ ወጣቷን ደፍሮ ገድሏል ያለው በጎ ፈቃደኛ በቁጥጥር ስር ቢያውልም ነገር ግን ወንጀሉን ለመሸፋፈን እንዲሁም ቸልተኝነት ታይቶበታል የሚሉ ክሶች ቀርበውበታል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ጉዳዩ ከአካባቢው ፖሊስ ወደ ፌደራል የምርመራ ቢሮ እንዲተላለፍ ተደርጓል።

የዶክተሯን ግድያ ተከትሎ በህንድ ተጨማሪ መደፈሮች ርዕሰ ዜናዎች ሆነዋል ይህንንም ተከትሎ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ “በሴቶች ላይ አረመኔያዊ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ በአስቸኳይ እና በከፋ ሊቀጡ ይገባል” ብለዋል።