በአዲሱ የውድድር ዘመን ጎልተው ይወጣሉ የተባሉ አፍሪካውያን ተጫዋቾች የትኛቹ ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዘንድሮው የክረምት ዘመን እንደ ወትሮው የእረፍት አልነበረም።
የአውሮፓ ዋንጫ፣ ኮፓ አሜሪካ እንዲሁም ኦሊምፒክ ውድድሮች የተካሄዱት ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ነው።
እነሆ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ተመልሷል። አፍሪካ የሚገኙ የሊጉ ደጋፊዎችም ‘ሪሞት ኮንትሮል’ አቀባብለው ጨዋታውን ለማጣጣም እየተሰናዱ ነው።
የ2024/25 ውድድር ዘመን የሚብተው በኦልድ ትራፈርድ ማንቸስተር ዩናይት ከፉልሀም ባደረጉት ጨዋታ ነው።
ሴኔጋላዊው አጥቂ ኢሊማን ንዳዬ፣ ጋናዊው የመስመር ተጫዋች ኢብራሒም ኦስማን እና ሞሮኳዊው ተከላካይ ቻድ ሪያድ የዓለማችን እጅግ ተዋዳጁን ሊግ ከተቀላቀሉ አፍሪካዊያን ተጫዋቾች መካከል ናቸው።
ቢቢሲ አፍሪካ በሚቀጥሉት ዘጠኝ ወራት ሊነሱ ይችላሉ የተባሉ ጥያቄዎችን ምላሽ እንዲህ አሰናድቷል።
ሳላህ በአዲሱ ሊቨርፑል
ሞሐመድ ሳላህ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ከተጫወቱ አፍሪካዊያን መካከል የምንጊዜም ምርጥ ነኝ ቢል የሚገርም አይሆንም።
ነገር ግን የግብፅ ብሔራዊ ቡድን አምበሉ ባለፈው የውድድር ዘመን ያሳየው ብቃት ከወትሮው ዝቅ ያለ መሆኑ የሚያከራክር አይደለም። በተለይ በውድድር ዘመኑ መገባደጃ ለዋንጫ ተስፋ የነበረው ሊቨርፑል የውጤት ቀውስ ውስጥ ሲገባ ሳላህ ምንም ሊያደርግ አልቻለም።
18 ግቦችን አስቆጥሯል። አምስቱ ከፍፁም ቅጣት ምት የተገኙ ናቸው። ቢሆንም ሳላህ በአውሮፓውያኑ 2017 ሊቨርፑልን ከተቀላቀለ በኋላ ይህ ቁጥር አነስተኛው ነው።
በጉዳት ምክንያት በ2023 በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ ያልቻለው ግብፃዊ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግም በተመሳሳይ ምክንያት በአንዳንድ ጨዋታዎች እንዳናየው ሆኗል።
በተለይ ደግሞ ባለፈው ሚያዝያ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በነበረው ጨዋታ ተቀይሮ ሲወጣ ከአሠልጣኝ ዩርገን ክሎፕ ጋር የገባው እሰጥ አገባ ተጫዋቹ ምናልባት ደስተኛ አይደለም የሚል ሐሜት እንዲነዛ ምክንያት ሆኗል።
አሁን ክሎፕ ከሊቨርፑል ጋር ተለያይተዋል። ሳላህ ከሊቨርፑል ጋር የገባው ውል ከአንድ ዓመት በኋላ ይጠናቀቃል። የሚሰሙት ወሬዎች የሚታመኑ ከሆነ ሳላህ በሚቀጥለው ዓመት “ሊቨርፑልን ተሰናብቶ ወደ ሳዑዲ አረቢያ” ሊያቀና ይችላል።
ነገር ግን ሳላህ ባለፈው ዓመት ያለምንም ዋንጫ ላጠናቀቀው ክለቡ “እስከ መጨረሻው እንደሚሟሟት” ተናግሯል።
አሁን ጥያቄው ሳላህ በአዲሱ አሠልጣኝ አርን ስሎት አስተዳደር እንዴት ይሆናል የሚለው ነው?
የክሎፕ ለቨርፑል የሚታወቀው ተጭኖ ወደፊት እየገፋ በመጫወት ነበር። ኔዘርላንዳዊው አሠልጣኝ ግን ኳስን ይዞ በመጫወት ነው የሚታወቁት።
ስሎት፤ ኳስ ከኋላ መስርተው ፊት ለፊት ላለው ዋና አጥቂ በማቀበል ነው የሚጫወቱት። ይህ ደግሞ መስመሩን ይዞ ወደፊት በፍጥነት በመሮጥ ለሚታወቀው ሳላህ ላይመች ይችላል።
ቀያዮቹ በክረምቱ የዝውውር መስኮት አዲስ ተጫዋች አላስፈረሙም። ይህ ማለት ሳላህ አስፈላጊነቱ አሁንም የጎላ ነው ማለት ነው። በሚቀጥለው ግንቦት ውሉ ሲያበቃ የሊቨርፑል ቆይታውን ያራዝም ይሆናል ወይ የሚለውን አብረን እናየዋለን።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሚንቴህ 30 ሚሊዮን ይገባዋል?
ባለፈው የውድድር ዘመን በአርን ስሎት አሠልጣኝነት ለፌይኑርድ ይጫወት የነበረው ጋምቢያዊው ያኩቡ ሚንቴህ በክረምቱ የዝውውር መስኮት በብዙዎች ተፈላጊነት ካገኙ ተጫዋቾች መካከል ሆኗል።
የ20 ዓመቱ ሚንቴህ ባለፈው ሰኔ ከዴንማርኩ ክለብ ኦዴንሴ በ5 ሚሊዮን ፓውንድ ኒውካስልን ተቀላቅሎ ነገር ግን ምንም ሳይጫወት በውሰት ወደ ሌላ ሊግ ተልኮ ነበር።
በኤሬዲቪዜ [የዴንማርክ ሊግ] ቆይታው በ27 ጨዋታዎች 10 ጎሎችን ያስቆጠረው ሚንቴህ በኤቨርተን፣ ሊዮን እና ቦሩሲያ ደርትሙንድ ሲፈለግ ቆይቷል። በስተመጨረሻም ብራይተን 30 ሚሊዮን ፓውንድ በማውጣት “እንደ መብረቅ ፈጣን” የተባለውን የመስመር ተጫዋች አስፈርሞታል።
በ18 ዓመቱ አገሩን ወክሎ እንዲጫወት ዕድሉን የሰጡት ቶም ሴይንትፊት ወጣቱ ሚንቴህ “አስገራሚ ብቃት ያለው ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ይናገራሉ።
የብራይተን ደጋፊዎች ጋምቢያዊው ተጫዋች በአዲሱ የውድድር ዘመን ብቃቱን ያሳያል ብለውም ይጠብቃሉ።
ፓርቲ ለአርሰናል አስፈላጊ ነው?
በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2020 በ45 ሚሊዮን ፓውንድ አርሰናልን የተቀላቀለው ቶማስ ፓርቴ በኤሜሬትስ ብቃት እና ልምዱን ያሳያል ተብሎ ብዙ ተስፋ ተጥሎበት ነበር።
ነገር ግን በጉዳት ምክንያት ሙሉ ብቃቱን ማሳየት ያልቻለው ፓርቴ ለአርሰናል 95 ጨዋታዎችን ቢያደርግም ይህ ነው የሚባል ሚና አልነበረውም።
የአርሰናል ደጋፊዎች ምናልባት ቶማስ ፓርቴ የሚለው ስም በመጀመሪያዎቹ 11 ተጫዋቾች ስም ዝርዝር ላይ ይታያል የሚለው ተስፋቸው የመነመነ ይመስላል።
ዋናው ጥያቄ ግን አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ አሁንም በፓርቴ ተስፋ አለው ወይ የሚለው ነው።
ባለፈው የውድድር ዘመን አርቴታ የ31 ዓመቱን አማካይ በመጨረሻዎቹ አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች አሰልፎታል። አርሰናል በአምስቱም ጨዋታዎች ድል ቢቀናውም ዋንጫውን በሲቲ ተነጥቋል።
ኮንትራቱ ሊቀደድ አንድ ዓመት የቀረው ፓርቴ አርሰናልን የሚሰናበት ከሆነ ምናልባትም መድፈኞቹን በዋንጫ ቢሰናበታቸው የተሻለ ነው የሚሆነው።
ሳር የሚደምቅበት ዘመን ይሆን?
የቶተንሀሙ አሠልጣኝ አንጅ ፖስቴኮግሉ ባለፈው የውድድር ዘመን ባሳዩን አሰላለፍ መሠረት ሴኔጋላዊው አማካይ ፓፔ ሳር ለክለቡ ወሳኝ እንደሚሆን እሙን ነው።
በሊጉ ውድድር አጋማሽ ለአፍሪካ ዋንጫ በመጓዙ ቀጥሎ ደግሞ በጉዳት ምክንያት የተወሰኑ ጨዋታዎች ያመለጡት የ21 ዓመቱ አማካይ ብዙ አድናቆት አግኝቷል።
ፓፔ ሳር ለቶተንሀም ስኬት አስፈላጊው ተጫዋች በመሆን የሚደምቅበት ዘመን ይሆን?
ለሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን በቋሚነት እየተሰለፈ ያለው ሳር ለሰሜን ለንደኑ ክለብ ምን ያክል ወሳኝ መሆኑን የሚያሳይበት ጊዜ ተቃርቧል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አዳዲስ መጪዎች
ያለፈው የውድድር ዘመን ከአውሮፓውያኑ 1992 ለመጀመሪያ ጊዜ ከታችኛው ሊግ አድገው የመጡ ሦስቱም ክለቦች የወረዱበት ሆኗል።
በርንሊ፣ ሉተን እና ሼፊልድ ዩናይትድ ማድረግ ያቃታቸውን ኢፕስዊች ታውን፣ ሌስተር ሲቲ እና ሳውዝአምፕተን ለማሳካት ሙከራ ያደርጋሉ።
ለሌስተር ሲቲ የሚጫወተው ናይጄሪያዊው ዊልፍሬድ ንዲዲ በቀበሮዎቹ ቤት ያለውን ውል አራዝሟል።
ከ22 ዓመት በኋላ ወደ ፕሪሚዬር ሊግ ለተመለሰው ኢፕስዊች፤ ግብፃዊው አማካይ ሳም ሞርሲ እና የዲሞክራቲክ ኮንጎው አክስል ቱዋንዜቤ አስፈላጊ ናቸው።
ሳውዝአምፕተንም እንዲሁ በናይጄሪያዊው የአጥቂ አማካይ ጆ አሪቦ መሪነት በሊጉ ለመቆየት ይታገላል።












