ከብሪታኒያ ወታደሮች የተወለዱ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ክስ የመሠረቱ ኬንያውያን አሸነፉ

ከኬንያውያኑ መካከል አንዱ የሆነው ፒተር ዋምቡጉ
የምስሉ መግለጫ, ከኬንያውያኑ መካከል አንዱ የሆነው ፒተር ዋምቡጉ አባቱን ሳያውቅ ማደጉን ይናገራል

ሰባት ኬንያውያን ለሕዝብ ይፋ የሆነ የዘረመል (ዲኤንኤ) መረጃ ቋትን በመጠቀም በአገራቸው በሚገኝ የጦር ሰፈር ውስጥ ከሚሰሩ የብሪታኒያ ወታደሮች የተወለዱ መሆናቸውን በፍርድ ቤት አረጋገጡ።

በለንደን በሚገኘው የቤተሰብ ፍርድ ቤት ሲካሄድ የነበረውን ክርክር ያሸነፉት ኬንያውያን፤ ማንነታቸው የማይታወቅ የነበሩ አባቶቻቸውን ለመለየት በክፍያ የሚገኙ የዲኤንኤ የመረጃ ቋቶችን ተጠቅመዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም ፍርድ ቤት ውስጥ በዚህ ዓይነት መንገድ አባትነት ሲረጋገጥ ይህ የመጀመሪያው ነው።

በፍርድ ቤቱ የተሰጠው ውሳኔ ከወታደሮች የተወለዱት ኬንያውያን የብሪታኒያ ዜግነትን እንዲያገኙ በር ይከፍትላቸዋል።

ኬንያውያኑን በፍርድ ቤት ወክሎ የተከራከረው በእንግሊዛዊው ጠበቃ ጄምስ ኔቶ፤ ከፎረንሲክ ጄኔቲክስ ፕሮፌሰር ከሆኑት ዴኒስ ሲንደርኮምብ ኮርት ጋር በትብብር ሠርቷል።

ጠበቃው በኬንያ ናንዩኪ ግዛት ከሚገኙ ሰዎች የዲኤንኤ ቅንጣት የሰበሰበ ሲሆን የነዋሪዎችን ምስክርነትንም ተቀብሏል።

በዚህ ሂደት ውስጥም በርካታ ሰዎች አባቶቻቸው በኬንያ ባቱክ ግዛት ውስጥ በሚገኘው በአፍሪካ ትልቁ የብሪታኒያ ሠራዊት ካምፕ ውስጥ የነበሩ ወታደሮች እንደሆኑ እንደሚያምኑ ገልጸዋል ተብሏል።

የእነዚህ ሰዎች የቤተሰብ አባላት ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ይገኙ እንደሆን ለማረጋገጥ ለሕዝብ ይፋ የሆነ የዲኤንኤ የመረጃ ቋትን ተጠቅመዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከኬንያውያኑ መካከል አንዱ የሆነው ፒተር ዋምቡጉ፤ አባቱ የብሪታኒያ ወታደር እንደሆነ እየተነገረው ቢያድግም እስካሁን ድረስ እንዳላገኘው ለቢቢሲ ተናግሯል። የ33 ዓመቲ ሼፍ እንደሚገልጸው ድብልቅ ዘር ያለው መሆኑ በልጅነቱ መዘባበቻ እንዲሆን አድርጎታል።

አባቱ "ጥሩ ሰው እንደነበር" እናቱ እንደነገሩት የሚያነሳው ፒተር፤ "አንድ ቀን እመጣለሁ እንዳላት ነግራኛለኝ፤ ግን ጭራሽኑ አልመጣም" ብሏል።

ፒተር በአሁኑ ሰዓት ከአባቱ ጋር ተገናኝቷል። አባቱ በበኩሉ ልጅ እንዳለው እንደማያውቅ ተናግሯል።

ፒተር ከአባቱ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ከተገናኘ በኋላ ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ "ላለፉት 30 ዓመታት የተሸከምኩትን ስቃይ፣ በሰዎች የደረሰብኝ መድልዎ፣ ያ ሕመም ሁሉ ወደ ደስታ ተለወጠ" ብሏል።

ከሕግ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች የተነሳ ማንነቷ የማይገለጽ ሌላ አቤቱታ አቅራቢ ደግሞ አራት ዓመቷ እያለ አንድ ጊዜ ብቻ አባቷን እንዳገኘች እና ከዚያ በኋላ ተመልክታው እንደማታውቅ ተናግራለች።

ያለ አባት ማደግ ከባድ እንደሆነ የምታስረዳው ኬንያዊቷ፤ "ጭራሹን እንደደተወች ይሰማት" እንደነበር አክላለች።

ጠበቃው ጄምስ ኔቶ፤ "የዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ ለረዥም ጊዜ ለበርካታ ቤተሰቦች የማይቻል መስሎ የታየው እጅግ አስቸጋሪ ጉዞ ማብቃቱን ያመለክታል። ከዚህ በፊት ከጥያቄ ውጪ ምንም ያልነበራቸው ልጆች እና ወጣቶች አሁን መልስ አግኝተዋል" ሲል ከውሳኔው በኋላ ተናግሯል።

በኬንያ ባቱክ ግዛት አቅራቢያ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሌሎች በርካታ ሰዎች እንዳሉ የሚያስረዳው ጠበቃው፤ ቀጣዩ እርምጃ ስለ አባቶቻቸው ወይም ስለቤተሰባቸው ጥቂት ወይም ምንም መረጃ ያላቸውን ሰዎች በፍርድ ቤት መወከል እንደሆነ ገልጿል።

በዲኤንኤ ምርመራ ሂደቱ ላይ የተሳተፈው ጠበቃ እና ተሟጋቹ አንድሪው ማክላውድ በበኩሉ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የእንግሊዝ መከላከያ ሚኒስቴር ባቱክ በሚገኙ ወታደሮች ላይ የሚቀርቡ የአባትነት ጥያቄዎችን በተመለከተ ይበልጥ ኃላፊነት እንዲወስድ ያደርጋል የሚል ተስፋ እንዳለው አስረድቷል።

የመከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ "ዩናይትድ ኪንግደም ወታደሮች ላይ የሚቀርቡ የአባትነት ጥያቄዎች የሰዎች የግል ሕይወት ጉዳይ ቢሆኑም፤ መንግሥት ከአባትነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች በሚኖሩበት ጊዜ ከአካባቢው ባለሥልጣናት ጋር ይተባበራል" ሲል ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥቷል።