በኬንያ የሚሰለጥኑ የዩኬ ወታደሮች ከፍተኛ ጥሰቶች ‘መፈጸማቸውን’ ተከትሎ አገሪቷ ህጓን አሻሻለች

በኬንያ የሚሰለጥኑ የዩናይትድ ኪንግደም ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኬንያ የሚሰለጥኑ የዩናይትድ ኪንግደም ወታደሮች ከፍተኛ ጥሰቶች ፈጽመዋል መባሉን ተከትሎ አገሪቷ ከዩኬ ጋር ያላትን የመከላከያ ስምምነት ህጓን አሻሻለች።

የኬንያ ፓርላማ ባሳለፈው አዲስ ማሻሻያ መሰረት የዩናይትድ ኪንግደም ወታደሮች በአገሪቱ ይከሰሳሉ።

የዩናይትድ ኪንግደም ወታደሮች ግድያን ጨምሮ ፈጽመዋል በተባሉት ከባድ ወንጀሎችም በኬንያ ህግ መሰረት የሚዳኙ ይሆናል።

ይህ ማሻሻያ የወጣው በአውሮፓውያኑ 2012 የተገደለችው ኬንያዊት ወጣት ፍትህ አለመገኘቱ ከፍተኛ ጥያቄ ማጫሩን ተከትሎ።

አግነስ ዋንጂሩ የተባለችው ኬንያዊት በአገሪቱ ከሚሰለጥኑ የዩናይትድ ኪንግደም ወታደሮች ጋር ከአንድ መጠጥ ቤት ስትወጣ አብራ ከታየች በኋላ ደብዛዋ ጠፍቷል።

የ21 ዓመቷ ወጣት ከሶስት ወራት በኋላ በአንድ ሆቴል ውሃ ማጠራቀሚያ ውስጥ አስከሬኗ ተገኝቷል። እስካሁን ድረስም በእርሷ ግድያ ላይ ተጠያቂ የሆነ አካልም ሆነ ለፍርድ የቀረበ የለም።

ሰንደይ ታይምስ በአውሮፓውያኑ 2021 የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚኒስቴር ግድያውን ለመሸፋፈን እየሞከረ ነው በሚል መዘገቡን ተከትሎ ሚኒስቴሩ ከኬንያ ባለስልጣናት ጋር በምርመራው ላይ ትብብር እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

በያዝነው ሳምንት ረቡዕ ሚኒስቴሩ ይህንኑ መልዕክት የደገመው ሲሆን “የዚህ ምርመራ ባለ ስልጣን የኬንያ ፖሊስ ነው። የዩኬ መከላከያ ወንጀል ኮማንድም ከኬንያ ፖሊስ ጋር እየተባበረ ሲሆን ምርመራቸውንም በተገቢው ለመደገፍ እንሳተፋለን” ብሏል።

የምርመራውን ሂደትም ለመጠበቅ ተጨማሪ አስተያየትም እንደማይሰጥም ሚኒስቴሩ አክሏል።

ነገር ግን በዚህ ሳምንት ረቡዕ ኬንያ ያሳለፈችው የመከላከያ ስምምነት ማሻሻያ ወደ ኋላ ተመልሶ ተፈጻሚ አይሆንም ይህም ማለት የዋንጂሩ ግድያ የተያዘበት ሂደት ላይ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም።

የኬንያ ፓርላማ የመከላከያ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኔልሰን ኮይች ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ሬድዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ማሻሻያው እንደ ዋንጂሩ አይነት ግድያዎች እንደገና እንዳይፈጸሙ ያቆማል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ድንገት ግድያውም ከተከሰተ ወንጀለኞችንም ለመክሰስና ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ማሻሻያው ይረዳል ብለዋል።