በአማራ ክልል በተከሰቱ ተቃውሞዎች በፀጥታ ኃይሎች እርምጃ እና በግለሰቦች ጥቃት የሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገለጸ

በጎንደር ከተማ ለተቃውሞ የወጡ

የፎቶው ባለመብት, social media

የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ውሳኔን ተከትሎ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በተነሳው ተቃውሞ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ እና ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ሰዎች መሞታቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።

በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች፣ በተወሰዱ እርምጃዎች እና በተፈጸሙ ጥቃቶች የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅት ሠራተኞችን ጨምሮ የሲቪል ሰዎች ሞት እና የአካል ጉዳት መከሰቱን ኢሰመኮ ሚያዝያ 4/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ኢሰመኮ የፀጥታ አካላት ያልተመጣጠነ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠቡ፣ ሁሉም ሰው ሃሳቡን በሕጋዊ እና በሰላማዊ መንገድ እንዲገልጽ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ መንግሥት ለደረሰው ጉዳት አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነት እንዲሰፍንም ጠይቋል።

ኢሰመኮ የፀጥታ ላይሎች በወሰዱት እርምጃ የምን ያህል ሰዎች ሕይወት እንደጠፋ በዚህ መግለጫው አልጠቀሰም፣ ሆኖም የካቶሊክ ተራድኦ አገልግሎት ሁለት ሠራተኞቹ ባለፈው እሁድ በአማራ ክልል፣ ቆቦ አካባቢ መገደላቸውን ድርጅቱ መግለጹ ይታወቃል።

እንዲሁም ቢቢሲ በደብረ ብርሃን ውስጥ በተከሰተው ግጭት ሁለት ሰዎች መሞታቸውን ከነዋሪዎች ሰምቷል። በተኩስ ልውውጡ በከተማዋ የተፈናቃዮች መጣለያ ጣቢያ ውስጥ ተጠልለው የነበሩ ሁለት ሰዎች መገደላቸው እንዲሁም አንዲት ሴት ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባት አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በቆቦ እሁድ ሚያዝ 1/2015 ዓ.ም. በአማራ ኃይሎች እና በመካላከያ ሠራዊት አባላት መካከል ግጭት ተከስቶ የሰዎች ሕይወት መጥፋቱንም ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ከቆቦ ሁለት ነዋሪዎች እንደተረዳው ሦስት የፋኖ አባላት በግጭቱ ስለመገደላቸው መስማታቸውን ሲሆን፣ ተጨማሪ መረጃ ከሚመለከታቸው አካላት ማግኘት አልተቻለም።

ካርታ

መከላከያ ሠራዊት በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ ክልክ ያለፈ ኃይል በመጠቀም በክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳር አቅራቢያ በምትገኝ መራዊ በተባለች ከተማ ቢያንስ ሁለት ሰላማዊ ሰዎችን ገድሏል ሲል የአማራ ማኅበር በሰሜን አሜሪካ አስታውቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በፌደራል መንግሥት የመከላከያ ሠራዊት ላይ የቀረበውን ክስ በተመለከተ ከጦሩ ወይም ከመንግሥት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም።

ከሰሞኑ የክልል ልዩ ኃይሎችን ለማደራጀት መንግሥት ካሳለፈው ውሳኔ ጋር በተያያዘ የአማራ ልዩ ኃይል ትጥቅ ሊፈታ ነው በሚል በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ተቃውሞዎች ተነስተዋል። በአንዳንድ አካባቢዎችም በመከላከያ ሠራዊት እና በልዩ ኃይሉ መካከል ፍጥጫዎችም ተከስተዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች ያጋጠሙ የፀጥታ መደፍረሶች እና ግጭቶች ያስከተሉትን ጉዳቶችን በተመለከተ ክትትልም እያደረገ እንደሚገኝ ኢሰመኮ አስታውቋል።

ኢሰመኮ በቆቦ፣ በባሕር ዳር፣ በወረታ፣ በኮምቦልቻ፣ በደብረ ብርሃን እና በመራዊ ከተሞች በተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች መንገድ መዝጋት፣ የአገልግሎቶች መቋረጥ እንዲሁም በፀጥታ ኃይሎች መካከል ፍጥጫዎች መከሰታቸውንም መረዳቱን አስታውቋል።

የተጠቀሱትን ከተሞች ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች በተፈጠረው ውጥረት እና አለመረጋጋት ምክንያት፣ የአገልግሎት መቋረጥ እና የእንቅስቃሴ እገዳዎች በማጋጠሙ በነዋሪዎች መደበኛ እና ሥራ ላይ እንቅፋት መፈጠሩን የመብት ድርጅቱ አመልክቷል።

በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ውጥረት መንገሱን ተከትሎ የደብረ ብርሃን፣ የጎደር፣ የደሴ፣ የኮምቦልቻ እና የወልዲያ ከተሞች የፀጥታ ኮማንድ ፖስት ጥብቅ ክልከላዎችን ጥለዋል።

ከተሞቹ ሰላም እና የሕግ የበላይነት ለማረጋጋጥ ከፀጥታ ኃይል አባላት ውጭ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስን ጨምሮ ሌሎች ገደቦችን ካላፈው ሳምንት ምብቂያ ጀምሮ ጥለዋል።

በአጠቃላይ የክልሎችን ልዩ ኃይሎች መልሶ የማደራጀት ውሳኔ እና ተግባራዊነት ጋር ተያይዞ የተከሰተው ችግር እና የፀጥታ መደፍረስ አስቸኳይ እልባት ካልተበጀለት ለከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አደጋ በመሆኑ በውይይት እና በምከክር ሊፈታ እንደሚገባ ኢሰመኮ መክሯል።

“አጠቃላይ የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታው የፈጠረውን ሥጋት እና የአለመተማመን ስሜትን ከግምት በማስገባት መንግሥት የፖሊሲ ውሳኔውን አስፈላጊነት እና ጠቀሜታ ለሚመለከታቸው ሁሉ በትዕግሥት እና በጽሞና የሚያስረዳበትን ሁኔታ እንዲያመቻችም” ኢሰመኮ ጠይቋል።