"የዛሬ 6 ዓመት የኦሮሚያ እና የአማራ ጫካዎች ሰላማዊ ነበሩ. . . አሁን ግን ፖለቲካው ጫካ እየገባ ነው" ፕ/ር መረራ ጉዲና

አቶ ዳውድ ኢብሳ እና ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ጋር ውይይት ለማድረግ የሚጠይቅ ይፋዊ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር ደብዳቤው እንደደረሰው አልያም ውይይቱ ስለመካሄዱ የሚጠቁም መረጃ እስካሁን ድረስ አላወጣም።

የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር ፕ/ር መረራ ጉዲና ". . .በአጠቃላይ የቀውሱ ሁኔታ ቁጭ ብለን የማናይበት ሁኔታ ላይ ስለደረሰ መንግሥት ቢያንስ ቢያንስ በኦሮሚያ አካባቢ እየተደረገ ያለውን በውል እንዲመለከት ለማሳሳብ" ደብዳቤውን እንደጻፉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ባለፈው ሳምንት ኦነግ እና ኦፌኮን ጨምሮ 10 አገር አቀፍ እና ክልላዊ ፓርቲዎች በዚህ ዓመት የሚካሄደው ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ተዓማኒ እንዲሆን እና "ከአጃቢነት ያለፈ ተሳትፎ" እንዲኖራቸው የሚጠይቁ ቅድመ ሁኔታዎችን ማቅረባቸው ይታወሳል።

ራሳቸውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች አንድነት መድረክ (መድረክ) ሲሉ የሚጠሩት 10 የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብስብ ኅዳር 3/2018 ዓ. ም. በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ ሰባተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት በሰባት መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ "መሠረታዊ ማሻሻያዎች" እንዲካሄድ ጠይቀዋል።

ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት ፕ/ር መረራ ለኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ለውይይት ጥያቄ ያቀረቡት "ኦሮሚያ ቀውስ ውስጥ በመሆኗ" ነው ብለዋል።

"በየቦታው ያለው እልቂት፣ ሰው በሰላም ወጥቶ መግባት አለመቻሉ፣ በአጠቃላይ የቀውሱ ሁኔታ ቁጭ ብለን የማናይበት ሁኔታ ላይ ደርሷል" ብለዋል።

ቀውሱ "ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱ ጥያቄ የለውም" ያሉት ፕ/ር መረራ "እንዲያውም ዘንድሮ ምርጫ [ይካሄዳል] እየተባለ ስለሆነ ከዚህ የበለጠም ችግር ውስጥ እንገባለን" ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

መንግሥት በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ችግሮችን "እየፈታ እንደሆነ" በተለያዩ ጊዜያት መግለጹን "እንደሚሰሙ" የተናገሩት ፖለቲከኛው፤ መንግሥት ከሚለው በሚጻረር መልኩ አሁን ያለውን ሁኔታ "ሕዝቡ እንደዛ እየተመለከተ እንዳልሆነ" ተናግረዋል።

ሕዝቡም "ለምን ዝም ብላችሁ ታያላችሁ?" ብሎ ስለሚጠይቃቸው ውይይት ለማካሄድ ጥያቄ ማቅረባቸውን አስምረውበታል።

"ከፕሮፓጋንዳ ባለፈ. . .አብዛኛው ኦሮሚያ፣ አብዛኛው ኢትዮጵያ በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እየኖረ እንዳለ. . . እየተሻሻለ ሳይሆን እየባሰበት እንደመጣ ይታወቃል" ብለዋል።

የውይይት ጥያቄ ያቀረቡት ሁለቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዘንድሮው ምርጫ እንደሚሳተፉ ቢያሳውቁም ሰባት መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች ካስቀመጡ ፓርቲዎች መካከል ናቸው።

ባለፈው ሳምንት ባወጡት መግለጫ፤ "ሕጋዊነትን ለመላበስ የሚደረጉ የፖለቲካ ትወናዎች" ሲሉ ከዚህ ቀደም የተደረጉ ምርጫዎችን በመኮነን፤ ምርጫዎቹ "ነፃ፣ ፍትሃዊ እና አሳታፊ፤ በውጤታቸውም ተዓማኒ እና በሕዝብ ተቀባይነት አላገኙም" ሲሉ ተችተዋል።

ፕ/ር መረራ በበኩላቸው ነገሮች እየከፉ ለመምጣታቸው አንድ ማሳያ ብለው የጠቀሱት በገጠሪቱ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ተሽከርካሪዎች "ከዋና ዋና መንገዶች ውጭ" መንቀሳቀስ አለመቻላቸውን ነው።

ከዚህ ቀደም በነበሩት ዓመታት በምዕራብ ኦሮሚያ "በስፋት በጦርነት እልቂት ነበር" ያሉት ተቃዋሚው፣ አሁን ግን "ወደ አርሲ እና ወደ ሐረርጌም አካባቢዎች" እየተስፋፋ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

መንግሥት በበኩሉ በዘረጋው የብሔራዊ ምክክር መድረክ ላይ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እንዲሳተፉ መጋበዙን በመጥቀስ "የውይይት በሮች" ክፍት መሆናቸውን ሲገልጽ ይሰማል።

ከዚህ ቀደም ፕ/ር መረራ ከመንግሥት ጋር በሚደረጉ ውይይቶች ላይ መገኘት "ጉንጭ አልፋ" ነው በሚል ለመሳተፍ እንደማይፈልጉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አሁን ላይ ምን ተለውጦ ነው ለውይይት ጥያቄ ያቀረባችሁት? በሚል ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ". . .እንደ ሠርግ የሆነ ነገር ላይ ተገኙልን ሲባል ነው እንጂ ድርድር እምቢ ብለን አናውቅም" ብለዋል።

". . .ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተሰበሰቡ ጉንጭ አልፋ ነገር ይደረጋል። ብዙ ትርፍ ስለሌለው ነው [የማንሳተፈው] እንጂ ከድርድር መሸሽ አይደለም። በየጊዜው እየሄድን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይዞ የመጣውን ይናገራል። ሌሎቻችን እንደ ጥሩ ተማሪ ጥያቄ እንጠይቃለን ከዚያ መልስ ይሰጣል። ከዚያ ዝም ብለን መበተን ነው። እኛ ከመንግሥት ጋር እንነጋገርም፣ አንደራደርም ያልንበት ጊዜ የለም።"

". . . ፖለቲካው ጫካ እየገባ ነው"

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ግድያዎች እና እገታዎች ሲፈጸሙ እንዲሁም ውጥረት በሚኖርበትም ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጻቸውን እንደማያሰሙ በመጥቀስ፤ ለምን እስከ ዛሬ ዝም አላችሁ? በሚል ከቢቢሲ የተጠየቁት ፕ/ር መረራ፤ እንደ "አቅማቸው" እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል።

አክለውም "አንዳንዴም ያለው ሁኔታ የበለጠ እንዳይበላሽ. . . አንዳንዴ በእሳት ላይ ቤንዚን መጨመርም ስላለ ለሕዝባችን ባለን ስስት አንዳንድ ሁኔታዎችን እናልፋለን" ብለዋል።

በሚፈልጉት መጠን የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ደንቃራ የሆነባቸው "የፖለቲካ ምኅዳሩ መጥበብ" እንደሆነም ገልጸዋል።

ሆኖም ግን "የፖለቲካ ምኅዳሩ ጠበበ" በሚል ሰበብ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጻቸውን ከማሰማት እየተቆጠቡ አይደለም ወይ በሚል ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ "በምንፈልግበት ደረጃ እና ሁኔታ ሕዝቡን ለማነጋገር፣ ስብሰባ ለመጥራት እና ሰላማዊ ሰልፍ ላለማድረግም ፖለቲካዊ ምኅዳሩ ጠቧል" ብለው መልሰዋል።

አክለውም "የአቅማችንን ማደራጀት ቀጥለናል፣ እንቀጥላለን። የኢትዮጵያ ሁኔታ በሚፈቅደው መንገድ እንንቀሳቀሳለን። መንግሥት ሕጋዊ የፖለቲካ መድረክ ላይ ላለነው የፖላቲካ ኃይሎች እያጠበበ ሲሄድ ግን. . . ብዙ ወጣቶች ወደ ጫካ እንዲገቡ [እያደረገ ነው]" ብለዋል።

"ፖለቲካው ተገፍቶ ጫካ ገብቷል" ያሉት ፕ/ር መረራ ለዚህም ምክንያቱ የፖለቲካ ምኅዳሩ መጥበቡ ነው ብለዋል።

"የፖለቲካ ምኅዳሩ እየጠበበ በመምጣቱ፤ የፖለቲካ ትግሉንም እኛ በምንፈልገው መንገድ፣ ሁኔታ እና ደረጃ [እንዳናካሂድ] አጣቦብናል። ብዙ ጊዜ የሚታሰሩት፣ የሚገፉት ደጋፊዎቻችን እና አባሎቻችን ናቸው፤ ተቃዋሚዎች [ናቸው]። ለታሰሩት ስንቅ ማድረስም ይቸግራል።"

ላለፉት ሰባት ዓመታት ገደማ ሰላማዊ ሰልፍ እየተካሄደ እንዳልሆነም ጠቅሰዋል።

"ከአምስት ዓመት በፊት አንዳንድ ቦታ ተንቀሳቅሰን ነበር። ሕዝብ እንደ ጎርፍ ተገልብጦ ሲወጣ መንግሥት ተደናገጠ መሰለኝ ሰላማዊ ሰልፍ ይቅርና ሰው በቤቱ ውስጥም እንዳንድ ነገር ማድረግ እየቸገረው መጣ።"

በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶቻቸው መዘጋታቸው እንቅስቃሴያቸውን እንደገታውም አንስተዋል።

"የዛሬ ስድስት እና ሰባት ዓመት አብዛኛው የኦሮሚያ ጫካዎች ሰላማዊ ነበሩ። የአማራ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ጥይቶች እንደዚህ የሚደረጉበት አልነበረም። [አሁን ግን] ፖለቲካው ጨካ ገባ" ሲሉም ፕ/ር መረራ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"በፖለቲካ ሥርዓቱ ተስፋ የቆረጠ ወጣት የት እንዳለ ይታወቃል። በአንዳንድ ቦታዎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠር. . . በኢትዮጵያ ጫና በተለይ በኦሮሚያ እና በአማራ ምን እንዳለ ይታያል። ችግሩ ወደዛ ሄዷል።"