ወራት የቀሩት ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ስጋት

ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛው አገራዊ ምርጫ ግንቦት 24/2018 ዓ.ም. እንደሚካሄድ ጊዜያዊ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ ለውይይት አቅርቧል።
ምርጫ ቦርድ ሰኞ ጥቅምት 10/2018 ዓ.ም. ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባካሄደው ዝግ ስብሰባ የዘንድሮውን ምርጫ ለማካሄድ የያዛቸውን ዕቅዶች በጊዜያዊ የጊዜ ሰሌዳ ላይ አስቀምጧል።
ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳው የምርጫ ጽሕፈት ቤቶችን ከማደራጀት ጀምሮ እስከ የምርጫ ውጤት ማሳወቂያ ድረስ ያሉትን ተግባራት የሸፈነ ነው።
ይህም የምርጫ አስፈፃሚዎች ምልመላዎች ይካሄድበታል ካለው ከጥቅምት 17 ጀምሮ የምርጫው አጠቃላይ ውጤት ይፋ ይሆንባታል ብሎ እስካቀደበት ሰኔ 3/2018 ዓ.ም. ድረስ የሚዘልቅ ነው።
ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጋብዞ የነበረው በዚህ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ውይይት ለማድረግ አልሞ የነበረ ቢሆንም ከፓርቲዎች የቀረበውን የጊዜ ሰሌዳ ወደ ጎን ያሉ ጠንካራ ሃሳቦችን አስተናግዷል።
ፓርቲዎቹ ከረቂቅ የጊዜ ሰሌዳው በፊት የሚቀድሙ ሌሎች መልስ የሚያሹ አንገብጋቢ የሰላም እና የፀጥታ ጉዳዮች መኖራቸውን አንስተዋል።
ይህም በግማሽ ቀን ለማጠናቀቅ ታቅዶ የነበረውን ስብሰባ ሙሉ ቀን እንዲወስድ ምክንያት ሆኗል።
ቦርዱ ያቀረበው የመወያያ አጀንዳም አቅጣጫውን ለውጦ በአብዛኛው በአገሪቷ ባለው የፀጥታ ችግር ላይ ያጠነጠነ እንደነበርም ቢቢሲ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገልጸዋል።
ስብሰባው "በቦርዱ እና በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተካሄደ ሳይሆን የፀጥታ አካላት የሚወያዩ ይመስል ነበር" ሲሉ አንድ ተሳታፊ ስለነበረው ሁኔታ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር እንደተናገሩት በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይቱን የተካፈሉ ሲሆን፣ ወደ አርባ የሚደርሱ ተናጋሪዎችም ሃሳብ ሰጥተዋል።
አብዛኞቹ የተሰነዘሩ ሃሳቦች መጪውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ አስቻይ ሁኔታዎች አለመኖር ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ፣ አገሪቷ አሁን ያለችበት ሁኔታ ምርጫ ቦርድ ያወጣውን የጊዜ ሰሌዳ ለማሳካት እንደማይችል ተሳታፊዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም ከምርጫው በፊት ወሳኝ የሆነውን የአገሪቷ የፀጥታ ችግርን ጨምሮ መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ፓርቲዎቹ አስምረውበታል።
ፓርቲዎቹ ያነሷቸው ስጋቶች አወዛጋቢ ከነበረው እና የግጭት መካረር መነሻ ከሆነው 6ኛው አገራዊ ምርጫ አስቀድሞም ሲነሱ የነበሩ ናቸው።
ከአንድ የሥልጣን ዘመን በኋላም በአዳዲስ አካባቢዎች ግጭቶች ተቀስቅሰው እና በአገሪቷ ውስጥ ያለው የፀጥታ ችግር ሳይፈታ የዚህ ዓመቱ ምርጫ የወራቶች ዕድሜ ቀርቶታል።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሊቀ መንበር የሆኑት ዶ/ር ራሔል ባፌ፣ ምርጫ ቦርድ ለውይይት ያቀረበው ሃሳብ "ቦርዱ እና ፓርቲዎች የተለያየ ክፍለ ዓለማት ላይ ነው ወይ የምንኖረው የሚል ጥያቄ የፈጠረ ነው" ብለዋል።
በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በትግራይ ክልሎች ግጭቶች ባሉበት፣ በሌሎችም አካባቢዎች የሰላም እጦት በሚታይበት ሕዝቡ ለአምስት ዓመት የሚመራውን መሪ ይመርጣል ተብሎ የጊዜ ሰሌዳ እስከ ማውጣት መደረሱ እንዳስገረማቸውም ዶ/ር ራሔል አክለዋል።
"በሕይወት የመኖር መብቱ ያልተረጋገጠለት ብዙ ዜጋ ነው ያለው፤ ሌላው ቀርቶ ውሃ ለመቅዳት፣ እንጨት ለመልቀም ደኅንነት የማይሰማው ሕዝብ ነው ያለው" ያሉት ዶ/ር ራሔል፣ ከምርጫው በፊት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ሊስተካከሉ የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ አንስተዋል።
የእናት ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ጌትነት ወርቁም ከዚህ የተለየ ሃሳብ አይደለም ያላቸው።
ከፍተኛውን የምክር ቤት መቀመጫ የሚይዙት ክልሎች በግጭት ውስጥ አሊያም በጦርነት ማግስት ላይ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ጌትነት፣ "ይህ በሆነበት ሁኔታ ከ50 በመቶ በላይ ውጤት አምጥቶ ሕጋዊ መንግሥት መመሥረት ይቻላል የሚል እምነት እንደሌላቸው" ገልጸዋል።
በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ ያለው አለመረጋጋት እና ግጭት በሌላውም አካባቢ ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር በመግለጽም፣ በመላ አገሪቱ ሰላም እንዳለ ማሰብ አይቻልም የሚሉ ሃሳቦችም መሰንዘራቸውን አቶ ጌትነት ተናግረዋል።
"የባለፈው ምርጫም መንግሥት የላችሁም ከሚባል የሚያነክስ መንግሥት ይኑረን በሚል ብልጽግናን ተሸክመን ነው ያለፍነው" ያሉት አቶ ጌትነት፣ በዘንድሮም ምርጫ ይህ እንዲደገም እንደማይፈልጉ ፓርቲያቸውን ጨምሮ ከበርካቶች ጽኑ አቋም ተንጸባርቋል ብለዋል።
ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ሆኖ ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ ካልቻለም በ2019 ዓ.ም. "አገር ላይኖር ይችላል" የሚል ስጋቶችም መነሳታቸውንም አቶ ጌትነት ጠቅሰዋል።
አገሪቷ ያለችበት ሁኔታ እንደሚያሳስበው በተለያየ ጊዜ ባወጣቸው መግለጫዎች መግለጹን ያስታወሱት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፀሐፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬም፣ ከምርጫው በፊት መቅደም ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ያምናሉ።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ታጠቅ አሰፋ "የአገሪቷ ሰላም ባልተረጋገጠበት ሁኔታ የይስሙላ ምርጫ መካሄዱ የመራጩን ሕዝብ ፍላጎት ያላሟላ እና መብትን የነፈገ ነው የሚሆነው" ብለዋል።
ከሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮች በተጨማሪም በሒደት ላይ ያለውና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን ጨምሮ በርካታ ጥያቄዎች የቀረቡለት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጥረቶች ባልተቋጨበት ሁኔታ ምርጫ እንዴት ሊካሄድ ይችላል የሚሉ ስጋቶችም ተነስተዋል።
በቅርቡ የጀርመን ድምጽ ራዲዮ ዘጋቢዎች ፈቃድ መከልከላቸውን የጠቀሱት የእናት ፓርቲ አመራርም ጋዜጠኞች በሚሳደዱባት፣ ገለልተኛ የሆኑ ሚዲያዎች እንዳይዘግቡ እየተከለከሉ ባለበት እና ነጻ ሚዲያዎች በሌሉበት ምርጫ ማካሄድም ፈታኝ ነው ብለዋል።
አቶ ጌትነት ከምርጫው በፊት የታሰሩ ፖለቲከኞችም መፈታት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, NEBE
ቦርዱ ለዚህ ምን ምላሽ ሰጠ?
እንደ ተሳታፊዎቹ ከሆነ ምርጫ ቦርድ በአገሪቷ ያለውን የፀጥታ ችግር ባይክድም ረቂቅ መርሃ ግብሩን ማውጣት ሚናው በመሆኑ ልወቀስ አይገባም ብሏል።
ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ መኖሩን ለማረጋገጥም እንደሚሠራም ገልጿል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ "አስቻይ ሁኔታ በሌለበት እኛም እራሳችንን አደጋ ውስጥ ለማስገባት ፍላጎት የለንም" ማለታቸውን የገለጹት ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተሳታፊዎች፤በመንግሥት፣ በምርጫ ቦርድ እና በፓርቲዎች መካከል ምክክር ተደርጎ ስምምነት ላይ እንደሚደረስ እና ቀጣይ ውይይቶች እንደሚደረጉ አስታውቀዋል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በነበረው አገራዊ ምርጫ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች በፀጥታ እና የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች ምርጫ ያልተደረገ ሲሆን፣ እስካሁንም ምርጫ ያልተካሄደባቸው ቦታዎች አሉ።
ወራት በቀሩት በዘንድሮው አገራዊ ምርጫም ግጭት ውስጥ ባሉ እና የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ቦርዱ ምርጫ ሊያካሂድ የሚችልባቸውን አማራጮች በግልፅ አላስቀመጠም።
ሆኖም የኔትወርክ አገልግሎት ያለባቸውን ቦታዎች ለመለየት ጥረት ማድረጉን እና የምርጫ ጣቢያዎችን ማቋቋም የሚቻለው 3ጂ፣ 4ጂ እና 5ጂ የኢንተርኔት አገልግሎት ባለባቸው አካባቢዎች እንደሆነ የጠቀሱ ሲሆን፤ ነገር ግን ይህን አገልግሎት እያገኙ ነው በተባሉ የተወሰኑ አካባቢዎች ጭምር አገልግሎቱ በተግባር እንደሌለ ሰብሳቢዋ መጥቀሳቸውን ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች እንደገለጹት ቦርዱ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች በኢንተርኔት በመታገዝ (በዲጂታል) ምርጫውን አካሂዳለሁ የሚል ፍንጭ አልሰጠም።
"መረጃ እያሰባሰብን ነው።መጀመሪያ እናንተን አነጋግረናል፤ ከዚያም ባለድርሻ አካላትን እናነጋግራለን ነው ያሉት። በቀረበው ረቂቅ የጊዜ መርሃ ግብር ላይ፤ ከውሳኔ ላይ የተደረሰበት ሁኔታ የለም" ብለዋል ዶ/ር ራሔል።
ገዢው ብልጽግና ፓርቲ በበኩሉ ቀድሞ በአገሪቱ የነበረውን የማይመች ሁኔታን በመቀየር ሰፊ የዲሞክራሲ ምኅዳር እየፈጠረ መሆኑን ገልጿል።
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ አደም ፋራህ ይህን ያሉት በባሕር ዳር ከተማ በተካሄደ ከፖለቲካ ፓርቲ የጋራ ምክር ቤት አባላት ጋር በተደረገ ምክክር ወቅት ነው።
ምርጫው ይራዘም ወይስ አይራዘም?
ባለፈው ሳምንት ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባካሄደው ውይይት የምርጫው መራዘም አለመራዘም ጉዳይ በቀጥታ አልተነሳም።
የውይይቱ ትኩረት ከምርጫው በፊት ሊከናወኑ ይገባል ባሏቸው ወሳኝ እና አንገብጋቢ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ነበር።
"አስቻይ ሁኔታ ተፈጥሮ ምርጫው በጊዜው ይካሄድ የሚል አቋም ነው ያለው" ያሉት የእናት ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌትነት፤ ጦርነቶች በድርድር እንዲቆሙ፣ በአማራ እና በኦሮሚያ የሚካሄዱ ግጭቶች በገለልተኛ ወገን ድርድር እንዲደረግ እና እንዲቋጭ መጠየቁን ገልጸዋል።
ምርጫው በየአምስት ዓመቱ ማካሄድ የግድ ነው ያሉት ዶ/ር ራሄል ባፌም ፓርቲያቸው፣ ገዢው ፓርቲ ለአንድም ቀን እንዲቀጥል እንደማይፈልግ እና መቀጠሉም ሕጋዊ አለመሆኑንም ገልጸዋል።
"ጥያቄያችን በአስቸኳይ ጠመንጃ ይዘቅዘቅ፣ ግጭት ይቁም፣ በየቦታው ያሉ ሰላም አሰናካዮች እና የሕዝብን ደኅንነት ስጋት ላይ የጣሉ ነገሮች የመንግሥት ቀዳሚ ጉዳዮች ናቸው፤ መንግሥት ይህን ሕገ መንግሥታዊ ግዴታውን እንዲያስፈጽም ነው በቅድመ ሁኔታ እየጠየቅን ነው ያለነው" ብለዋል።
የኢዜማው አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ በበኩላቸው ምርጫ የምናካሂደው የጊዜ ሰሌዳውን ለማሟላት ባለመሆኑ የሕዝብን ውክልና እና የምርጫ መስፈርቶችን ያሟላ መሆን እንዳለበት አስረግጠዋል።
ምርጫው ይራዝም የሚል አቋም ለመያዝ ጊዜው አሁን አይደለም ያሉት አቶ ታጠቅም፣ እስከዚያ ድረስ ውሳኔዎችን ለመወሰን የሚያስችሉ መደላድሎች መፈጠር አለባቸው ብለዋል።
ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት በአንድ ዓመት ተራዝሞ መካሄዱ አይዘነጋም።
የምርጫው መራዘም ሕገ መንግሥታዊ አይደለም በሚል በአገሪቷ ለተከሰተው ደም አፋሳሽ ጦርነት መነሻ ምክንያቶች አንዱ ሆኗል።
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ምርጫ በየአምስት ዓመቱ መካሄድ እንዳለበት የሚደነግግ ሲሆን፣ በሕዝብ ሳይመረጥ ሥልጣን ላይ የቆየ መንግሥት ሕጋዊ አይደለም።
በወቅቱም የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ምክትል አቃቤ ሕግ የነበሩት ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ሳይፋለስ ምርጫ ለማካሄድ ሕገ መንግሥትን እስከ ማሻሻል የሚደርሱ የመፍትሔ አማራጮች አስቀምጠው ነበር።
የምርጫው መራዘምም በአንዳንድ ፖለቲከኞች ዘንድ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም የሚሉ ጥያቄዎች እንዲነሱ በር የከፈተ ሲሆን፣ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረንስን (ኦፌኮ) ጨምሮ ራሳቸውን ከምርጫው ያገለሉ ፓርቲዎችም ነበሩ።
ከአምስት ዓመታት በኋላም የዘንድሮውን ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታዎች በአገሪቱ ውስጥ እንደሌለ የፖለቲካ ፓርቲዎች እየገለጹ ነው።
መፍትሔው ምንድን ነው ?
"የምንመራውም፣ የምንመራውም ኢትዮጵያዊያን ነን፤ በመከራ ውስጥ ያለውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው" የሚሉት አቶ ታጠቅ፣ ምርጫ በባሕርይው የተረጋጋ ሁኔታን የሚፈልግ በመሆኑ የትኛውም ቦታ ላይ ያሉ ግጭቶች መፈታት አለባቸው ብለዋል።
"ቅድሚያ የሚሰጠው የማኅበረሰቡ ሰላም ነው፤ ይህንን ሳናረጋግጥ ምርጫ ማካሄድ በቤንዚን ላይ ክብሪት እንደ መጫር ነው" ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች የሚካሄዱ ግጭቶችን ለማስቆም መንግሥት የሕግ ማስከበር እርምጃ እየወሰደ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገልጽ የቆየ ሲሆን፣ ለታጣቂ ቡድኖች የሰላም ጥሪዎችንም ሲያቀርብ ተደምጧል።
ሆኖም እስካሁን ይህ ነው የተባለ ውጤት አላስገኘም። በተለይ በአማራ ክልል ያለው ግጭት ተባብሶ መቀጠሉ እየተነገረ ነው።
ታዲያ የወራት ዕድሜ በቀረው ምርጫ ለዓመታት ጥረት ሲደረግበት የቆየውን ሰላም በአጭር ጊዜ ማምጣት ይቻላል ወይ ተብለው የተጠየቁት አቶ ታጠቅ "ምርጫም ስለተደረገ ለውጥ አለ ማለት አይቻልም። ሁሉም ነገር አብቅቷል ማለትም አይቻልም" ብለዋል።
ምርጫ በራሱ ሌላ ችግር ይዞ እንደሚመጣ ታስቦ በውይይት መፍትሔ ማምጣት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
የእናት ፓርቲ አመራር አቶ ጌትነትም ጊዜው አጭር ቢሆንም መንግሥት ቁርጠኛ ከሆነ ያለውን አገራዊ ሁኔታ ማስተካከል ይቻላል የሚል እምነት ነው ያላቸው።
"ሰላማዊ ሰዎች በድሮን እና በከባድ መሣሪያ ይገዳላሉ፤ በወጡበት የሚታገቱ ሰዎች አሉ። ስለ ዲሞክራሲ ለማውራት መሠረት የለም፤ ይህ ባልሆነበት ሁኔታም ስለ ምርጫ ማውራት ቅንጦት ነው" ብለዋል።
"በአዲስ አበባ ውስጥ እንኳን መሰብሰብ አይቻልም፤ በገዛ ቢሯችን መሰብሰብ ተከልክለን ነው ያለነው" የሚሉት ዶ/ር ራሔል፣ መንግሥት ቁርጠኛ ከሆነ ባሉት ጊዜያት ሰላም ማምጣት ይችላል የሚል ጠንካራ እምነት አላቸው።
"የፖለቲካ ጥያቄዎች ምላሽ ማጣት ነው ሰዎችን ጫካ ያስገባው። ጫካ ውስጥ የተወለደ ወይም ከጫካ የመጣ የለም።በመሆኑም መንግሥት ይህንን የፖለቲካ ጥያቄ በቅንነት እና በቁርጠኝነት መመለስ ከቻለ መፍታት ይቻላል" ብለዋል ዶ/ር ራሔል።
"ለዚህ ደግሞ ተዓማኒ የሆነ አካሄድ ከመንግሥት ይጠበቃል፤ ይህ ካላደረገ ሳንፈልግም ቢሆን ችግር ውስጥ እንገባለን" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት የምርጫ መራዘም በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ባለሥልጣናት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እንዲካረር ምክንያት ሆኗል።
ምርጫው ለአንድ ዓመት መራዘሙን አገሪቷን ለ30 ዓመታት ገደማ ሲመራ በነበረው ኢህአዴግ ውስጥ ጉልህ ሚና በነበረው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ዘንድ ተቀባይነት አልነበረውም።
በዚህም ምክንያት የትግራይ ክልል ከሕግ ውጪ ነው የተባለውን የራሱን ክልላዊ ምርጫ ያካሄደ ሲሆን፣ ይህም በፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል የነበረውን ፍጥጫ በማካራር በወራት ውስጥ ደም አፋሳሹ ጦርነት እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆኗል።
ጦርነቱም ወደ አማራ እና አፋር ክልል ተስፋፍቶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የተቀጠፉ ሲሆን፣ ከሰው ሕይወት መጥፋት እና ከንብረት ውድመት ባሻገር ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ እስካሁንም ድረስ መፍትሔ አላገኘም።
በግጭት ውስጥ የቆየው ኦሮሚያ ክልል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተደጋግመው የሚሰሙ የፀጥታ ችግሮች አሁን ላይ ጋብ ቢሉም የሰላም ሁኔታው ወደ ቀድሞው አልተመለሰም።
ግጭቶች ተጠናክረው በቀጠሉበት የአማራ ክልልም ላለፉት ሁለት ዓመታት የፀጥታ ችግር ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ በክልሉ በርካታ አካባቢዎች ውስጥ ማኅበራዊ አገልግሎቶች እና መደበኛ እንቅስቃሴዎች ተስተጓጉለው ቀጥለዋል።















