በኦሮሚያ ምዕራብ ሸዋ በኖኖ ወረዳ 12 ነዋሪዎች እና 22 ታጣቂዎች መገደላቸውን የአካባቢው አስተዳደር ገለፀ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ከጉራጌ ዞን የተነሱ ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት 12 ሰዎች መገደላቸውን እና የፀጥታ ኃይሎች ደግሞ 22 መግደላቸውን ነዋሪዎች እና የአካባቢው ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናገሩ።
በኖኖ ወረዳ ሀሎ ዲኒቂ መንደር ባለፈው ቅዳሜ ጥቅምት 8/2018 ዓ. ም. ምሽት ላይ በተፈጸመው ጥቃት 22 ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ሲናገሩ የኖኖ ወረዳ አስተዳዳሪ ግን የተገደሉት 12 ሰዎች መሆናቸውን ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ገልጸዋል።
ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በአካባቢው ተሰማርተው እርምጃ መውሰዳቸውን የገለፁት የኖኖ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ወንዳፍራሽ ሉሌሳ "የተገደሉት 22 ናቸው የሚባለው ውሸት ነው። 12 ናቸው የተገደሉት። ከ22 በላይ የተገደሉት ከታጣቂዎቹ ወገን ነው" ብለዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመበት መንደር ነዋሪዎች ጥቃት "ከጉራጌ ዞን ተሻግረው የመጡ በፋኖ ታጣቂዎች" ቅዳሜ ምሽት ላይ "አሰቃቂ ጥቃት" ፈጽመዋል ሲሉ ከስሰዋል።
ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ነዋሪ ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ እንደገለጹት፤ ታጣቂዎቹ "ከጉራጌ ዞን በመነሳት በፈጸሙት ጥቃት ሕጻናትን ጨምሮ ንጹኃን ዜጎች ላይ" ጥቃት ፈጽመዋል።
ከዚህ ቀደም ተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጸምበት በነበረው ኖኖ ወረዳ አሁን በተፈጸመው ጥቃት "ቤታቸው ውስጥ እና ከቤት ውጪም የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 22 ደርሷል" በማለት ነዋሪው ገልጸዋል።
ይህንን የሞችቾች ቁጥርን የሚያስተባብሉት የኖኖ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ወንዳፍራሽ ታጣቂዎቹ ከጉራጌ ዞን መነሳታቸውን ጠቅሰው ጥቃት ፈጻሚዎቹ እንደሚባለው የፋኖ ታጣቂዎች ሳይሆኑ "ተራ ሌቦች ናቸው" ብለዋል።
በአካባቢው ትልቅ የፀጥታ ችግር እየፈጠሩ ያሉት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ናቸው የሚሉት አቶ ወንዳፍራሽ "ለፋኖ መንገድ የከፈቱት እነርሱ ናቸው። ፋኖ በሚል ስም የሚንቀሳቀሱት የመንግሥትን ሥርዓት ለመጣል የሚሞክሩ ሳይሆኑ ተራ ሌቦች ናቸው። በየመጠጥ ቤቱ የሚውሉ እና ማታ ማታ ጠመንጃ አንስተው ጥቃት የሚፈጽሙ ናቸው" ብለዋል።
በተመሳሳይ መልኩ ቢቢሲ ያነጋጋረቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ጥቃቱን የፈጸሙት ታጣቂዎች ከኖኖ ወረዳ ተፈናቅለው ወደ ጉራጌ ዞን ሄደው ከሰፈሩ ሰዎች መካከል ያሉ ታጣቂዎች ወደ ወረዳው ተመልሰው በመምጣት መሆኑን ተናግረዋል።
ከኖኖ ወረዳ ተፈናቅለው ወደ ጉራጌ ዞን የሄዱት ሰዎች የኦሮሞ ነጻነት ጦር የሚፈጽመውን ጥቃት እንዲሁም በአካባቢው አስተዳደር ከመሬት ይዞታ ጋር በተያያዘ በወጣ አዲስ አሠራር ምክንያት መሆኑን ነዋሪዎች አመልክተዋል።
በአካባቢው ከዚህ ቀደምም በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት ያደረሱ ጥቃቶች በነዋሪዎች ላይ የተፈጸሙ ሲሆን፣ የባለፈው ሳምንት ጥቃት "ስድስተኛው" መሆኑን አንድ ነዋሪ አስታውሰዋል።
ጥቃት ፈጻሚዎቹ ወደ አካባቢው ሲደርሱ "ሕጻናት፣ አዛውንት እና ሴቶችን እንኳን አያስተርፉም" ያሉት ነዋሪው ያገኙትን ሰው በሙሉ "በጅምላ ነው የሚገድሉት" ብለዋል።
በቅዳሜ ዕለቱ ጥቃት ከተገደሉት ሰዎች መካከል ሕጻናት፣ አረጋውያን እና ሴቶች እንደሚገኙበት ነዋሪው ጠቅሰው፣ በጥቃቱ ተገድለዋል ብለው የሚሰጡት ቁጥር ግን ከወረዳው አስተዳዳሪ የተለየ ነው።
ሌላ ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ያነጋገራቸው ነዋሪም ጥቃቱን የፈጸሙት ታጣቂዎች "ከጉራጌ ክልል የመጡ ናቸው" በማለት፣ ጥቃቱን የፈጸሙት የኦሮሞ ነጻነት ጦር በሚያደርሰው ጥቃት እና ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ ሳቢያ ከኖኖ ወረዳ የተፈናቀሉ ናቸው ሲሉም አክለዋል።
የአካባቢው ሚሊሻዎች ነዋሪዎቹን ከጥቃት ለመከላከል ቢሞክሩም አቅማቸው ከታጣቂዎቹ ጋር ስላልተመጣጠነ ነዋሪዎቹን ማዳን እንዳልቻሉ ነዋሪው ተናግረዋል።
የኖኖ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ወንድአፍራሽ ሉሌሳ እነዚህ ወገኖች የመንግሥት የፀጥታ አካላት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ላይ ሲዘምት በሚያገኙት አጋጣሚ ጥቃት እንደሚፈጽም ይናገራሉ።
"ዓላማቸው በሕገ ወጥ መንገድ ሰፍረው መሬት በመውረር ግብር የማይከፍሉበት መሬት ማግኘት ነው። ከመሬቱ ተፈናቅለናል አሁን መመለስ አለብን በሚል ነው ጥቃት የፈጸሙት። ይህ ግን ሕልም ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኖኖ ወረዳ "በታጣቂዎች" በተደጋጋሚ ጥቃት ከሚሰነዘርበትና ንጹኃን ከሚገደሉበት የኦሮሚያ አካባቢዎች መካከል አንዱ ሆኗል።
ከዚህ ቀደም በኖኖ ወረዳ ሰርገኞችን ዒላማ ባደረገ ጥቃት ከ20 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።
የአካባቢው ኮማንድ ፖስት ኃላፊ ጥቃቱን የፈጸሙት "ጽንፈኛ የአማራ ታጣቂዎች" ናቸው ያሉ ሲሆን፣ አንድ ነዋሪ ደግሞ ጥቃቱ በማን እና በምን ምክንያት እንደተፈጸመ ግልጽ አይደለም ብለው ነበር።















