በኦሮሚያ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ24 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኦሮሚያ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች በደረሰ ጥቃት እና ይህንን ተከትሎ በተፈጸመ የአጸፋ ጥቃት ቢያንስ 24 ሰዎች መገደላቸውን የሟች ቤተሰቦች እና ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
ነዋሪዎች፤ በኦሮሚያ ክልል ለተፈጸመው ጥቃት "ፋኖ" ሲሉ የጠሯቸውን ታጣቂዎች ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ነዋሪዎች ደግሞ ሌላኛው ጥቃት የተፈጸመው "በኦሮሚያ ክልል ፀጥታ ኃይሎች" እንደሆነ ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን ተከታታይ ጥቃቶች የተፈጸሙት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ሐምሌ 3 እና አርብ ሐምሌ 4/2017 ዓ.ም. እንደሆነ ነዋሪዎች ገልጸዋል። ሐሙስ ምሽት የመጀመሪያው ጥቃት የተፈጸመው በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ዳርጌ ከተማ ውስጥ ጉዲና በተባለ አካባቢ እንደሆነ ነዋሪዎች አስረድተዋል።
ስማቸውን እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ ነዋሪ፤ "በግምት ከምሽቱ 1፡30 አካባቢ ነው ተኩስ የተጀመረው ። ይህ ጥቃት የተፈፀመው በፅንፈኛ እና በሽብርተኛ ቡድኖች ነው። በዚያ ሰዓት እኛ ቤት ውስጥ ሆነን ነው ተኩስ የሰማነው" ሲሉ ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ተናግረዋል።
ተኩሱ ለ30 ደቂቃ ያህል የዘለቀ እንደነበር የሚናገሩት ነዋሪው፤ ሁለት ሰዓት ገደማ ላይ ከቤታቸው ሲወጡ የተገደሉ ሰዎችን እንደተመለከቱ ገልጸዋል።
"የተገደሉት ሰዎች 14 ናቸው። ሌሎች አምስት ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ወሊሶ ሆስፒታል ገብተው ነበር። ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ ሕይወታቸው አልፏል። ሦስቱ ናቸው በሕክምና ላይ ያሉት" ብለዋል።
ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው "ከስምንት ወር ሕጻን" እስከ "የ60 ዓመት አዛውንት" ድረስ ያሉ ነዋሪዎች መገደላቸውን ተናግረዋል። ከተገደሉት ነዋሪዎች መካከልም አቶ ብርሃኑ ሸምሰዲን የተባሉ ግለሰብ እንዲሁም የግለሰቡ ባለቤት እና አምስት ልጆች እንደሚገኙበት አክለዋል።
ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በኦሮሚያ ክልል ለደረሰው ጥቃት ተጠያቂ ያደረጉት በአጎራባቹ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ይገኛሉ ያሏቸውን ታጣቂዎች ነው።
አንድ ነዋሪ፤ "እነዚህ ቡድኖች ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ጥቃት ፈፅመው ሰዎች ተገድለዋል። ቡድኖቹ በወልቂጤ እና በዳርጌ ድንበር ላይ ነው የሚገኙት። ራሳቸውን ፋኖ ብለው ነው የሚጠሩት" ብለዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአጎራባቹ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ ሦስት ነዋሪዎች ሐሙስ ዕለት በኦሮሚያ ክልል ይህ ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጠዋል።
የአበሽጌ ወረዳ ነዋሪዎቹ እንደሚናገሩት ይህ ጥቃት ከተፈፀመ በኋላ በማግስቱ አርብ፤ በወረዳው ዳርጌ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ ሰዎች "በኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ኃይሎች" ከመኖሪያቸው ተወስደው ተገድለዋል።
እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ አርብ ዕለት ወደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አበሽጌ ወረዳ የተሻገሩ "የኦሮሚያ ክልል አድማ በታኝ ፖሊስ እና ሚሊሻ አባላት" የወሰዷቸው ነዋሪዎች ብዛት "ከ20 በላይ" ነው።
ከአበሽጌ ወረዳ የተወሰዱት ሰዎች ሐሙስ ዕለት በተፈጸመው ጥቃት "ሰዎች የሞቱበት ቦታ ተወስደው እንደተገደሉም" ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች አስረድተዋል።
ነዋሪዎቹ ከተወሰዱ በኋላ በአጎራባቹ ኦሮሚያ ክልል አካባቢ በሚገኘው "ኖኖ ቆንዳላ ፖሊስ ጣቢያ" እንዲቆዩ ተደርገው እንደነበር ተናግረዋል።
በዚህ ጥቃት ከተገደሉ ሰዎች መካከል አስከሬናቸው የተገኘ ስምንት ሰዎች የቀብር ሥነ ሥርዓት መፈጸሙን ሦስት ነዋሪዎች ገልጸዋል። አንድ ነዋሪ፤ ሟቾቹ ቅዳሜ ዕለት የተቀበሩት በአበሽጌ ወረዳ በሚገኙት ዳርጌ ቅድስት ማርያም፣ ሁዳድ ሰባት መድኃኔዓለም እና ሁዳድ አራት ሚካኤል ቤተ ክርስቲያኖች እንደሆነ ዘርዝረዋል።
የቤተሰብ አባሉ የተገደለበት አንድ ነዋሪ፤ "የኋሊት እጁን አስረው ገድለውት ያገኘነው ጫካ ውስጥ ነው። ለዚያውም አናስነሳም ብለው መከላከያ ይዘን ገብተን አስከሬን ያነሳነው" ሲል ሁኔታውን ገልጿል።
ሌላ ነዋሪም በተመሳሳይ ወደ ኦሮሚያ ክልል ተወስደው የተገደሉት ሰዎች አስከሬን የተገኘው የመከላከያ ሠራዊት አባላት አርብ ዕለት ከጥቃቱ በኋላ ወደ አካባቢው ከገቡ በኋላ መሆኑን ተናግሯል።
የቅርብ ዘመድ የተገደለበት ይህ ነዋሪ እንደሚናገረው ከተቀበሩት ሰዎች ውስጥ የአራቱ አስከሬን የተገኘው "አውሬ በልቶት" ነው። "መከላከያ ከቤተሰብ ጋር ሄዶ ያመጣቸው በሸራ ጥቅልል አድርጎ ነው። እኛ ደግሞ [ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል] ላይ ትንሽ ሰላም ስላለ ቀበርናቸው" ብሏል።
ይህ ጥቃት የተፈጸመው ሐሙስ ዕለት በኦሮሚያ ክልል ለተፈጸመው ግድያ በአጸፋ ምላሽነት እንደሆነ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
አንድ ነዋሪ፤ "አሁን ፀጥታ ችግር የመጣው ብለው የሚያስቡት ኦሮሚያ ላይ የመጣው የአማራ ፋኖ እኛን እየገደለ እየጨፈጨ የሚኖረው [ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል] ላይ ነው" ሲሉ በተፈጸመው ጥቃት ምክንያት ነው ያሉትን ጉዳይ ጠቅሰዋል።
ኦሮሚያ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ በሚጎራበቱበት በዚህ አካባቢ ጥቃት ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ሰርግ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ከ20 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው አስተዳደር ባለሥልጣን እና ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
የኖኖ ወረዳ ኮማንድ ፖስት ኃላፊ አቶ ተሾመ ሰቦቃ ጥቃቱን ፈጸሙት "ጽንፈኛ የአማራ ታጣቂዎች" ናቸው ሲሉ በወቅቱ ከስሰው ነበር። በወቅቱ ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ ነዋሪ፤ "የጥቃቱን ምክንያት ለማወቅ አዳጋች ነው። በመሬት ይገባኛል ነው ያሉ አሉ። ነገር ግን እርግጠኛ መሆን አልቻልንም" ሲሉ ተናግረው ነበር።
አሁን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሦስት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ነዋሪዎቹም በተመሳሳይ በአካባቢው ጥቃቶች እየተፈጸሙ ያለው ከመሬት ጋር በተያያዘ ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ።
ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ በኦሮሚያ ክልል ኖኖ ወረዳ ይኖሩ ነበሩ "የአማራ ተወላጆች ለዓመታት ከኖሩበት ቤት እና መሬት መፈናቀላቸውን" የሚያስታውሱት ነዋሪዎቹ፤ የተፈናቀሉት ሰዎች በአጎራባቹ ጉራጌ ዞን መኖር እንደጀመሩ ያስረዳሉ።
እነዚህ ነዋሪዎች ቤታቸው ለሌሎች ነዋሪዎች "ተላልፎ እንደተሰጠ" እና መሬታቸው እንዲመለስላቸው በተደጋጋሚ ቢጠይቁም መፍትሔ እንዳላገኙ ተናግረዋል። አንድ ነዋሪ፤ "የቸገረው መሄጃ ያጣ ሄዶ ይተነኩሳቸዋል፤ ለምን መሬቴን ወስደው፣ ቤቱን የተፈናቃይ ነው ብለው… ወጣት በሙሉ ቤታቸውን ገብተዋል" ብሏል።
ቢቢሲ የተፈጸሙትን ጥቃቶች በተመለከተ ከኦሮሚያ እና ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባለስልጣናት ምላሽ ለማግኘት ያደረጋቸው ተደጋጋሚ ጥረቶች አልተሳኩም።















