በመተከል ዞን በተፈጸሙ ተከታታይ ጥቃቶች ምክንያት ከ40 በላይ ባለሀብቶች እርሻዎቻቸውን ጥለው ወጡ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የእርሻ መሬት ላይ የተበላሻ ትራክተር ዙሪያ የቆሙ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Benishangul Gumuz Media

የምስሉ መግለጫ, ባለሀብቶች ጥለው የወጡባቸው ዳንጉር እና ጉባ ወረዳዎች፤ እስከ 80 በመቶ የሚሆነው የክልሉ የእርሻ ኢንቨስትመንት የሚገኝባቸው እንደሆኑ ተገልጿል። (ፎቶ፤ ፋይል)

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን 20 ገደማ ሰዎች የተገደሉባቸው ተከታታይ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ተከትሎ፤ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የቅባት እህሎችን የሚያመርቱ የግል ባለሀብቶች እርሻዎቻቸውን ጥለው ወጡ።

የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ፤ በአካባቢው እየታየ ባለው ትጥቅ የተቀላቀለበት እንቅስቃሴ ምክንያት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ብቻ "45 አካባቢ" የግል ባለሀብቶች ጥለው መውጣታቸውን እንዳሳወቁት ገልጿል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በአንጻራዊነት ሰላም ሰፍኖበት የነበረው መተከል ዞን፤ ካለፈው ግንቦት ጀምሮ ተከታታይ ጥቃቶች የተፈጸሙባቸው ዳንጉር እና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሚገኝበት ጉባ ወረዳዎች ናቸው።

በዞኑ ውስጥ የሚገኙት ቡለን፣ ድባጤ እና ወምበራ ወረዳዎችም ካለፈው ወር አንስቶ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሚፈጸሙ ጥቃቶችን እየተስተዋሉባቸው መሆኑን ሦስት የወረዳዎቹ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በጥቃት እና ግጭቶች ሲታመስ የነበረው መተከል ዞን፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ትጥቅ ትግል ላይ ከነበሩት የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ እና የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ ጋር የፈጸማቸውን የሰላም ስምምነቶችን ተከትሎ መረጋጋት አሳይቶ ቆይቷል።

በመተከል ዞን በሚገኙት ዳንጉር እና ጉባ ወረዳዎች ከመንግሥት መሬት ተረክበው በእርሻ ልማት ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ከስምምነቱ በፊት በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት አካባቢውን ለቅቀው ወጥተው ነበር።

ባለሀብቶቹ በዘንድሮው ዓመት ወደ እርሻዎቻቸው የተመለሱት የክልሉ መንግሥት በ2017 ዓ.ም. ወደ ሥራ የማይገቡ አልሚዎችን መሬት እንደሚነጥቅ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ተከትሎ እንደሆነ አራት ባለሀብቶች ለቢቢሲ ተናግረዋል። የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ አመንቴ ገሺም ይህንን አረጋግጠዋል።

ባለሀብቶቹ የተሰማሩባቸው ዳንጉር እና ጉባ ወረዳዎች "ከክልሉ የእርሻ ልማት ከ70 እስከ 80 በመቶ" የሚገኝባቸው እንደሆኑ አቶ አመንቴ ገልጸዋል። ምርታማ በሆኑ ወረዳዎች መሬት የተሰጣቸው ባለሀብቶች እንደ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር እና ለውዝ ያሉ ለውጭ ገበያ ሚቀርቡ ሰብሎችን ያመርታሉ።

ቢቢሲ ያነገጋራቸው ባለሀብቶች ዘንድሮ ወደ እርሻቸው ከተመለሱ በኋላ ዓመቱን ያሳለፉት ሠራተኞቻቸውን በማደራጀት፣ ግብአቶችን በማሟላት እና የእርሻ መሬቱን በመመንጠር እና በማጽዳት ነው። በሁለቱ ወረዳዎች ጥቃቶች መፈጸም የጀመሩት ባለሀብቶቹ በተወሰነው የእርሻ መሬት ላይ መዝራት ከጀመሩ በኋላ እንደሆነ ገልጸዋል።

የመተከል ዞን ዋና ከተማ ግልገለስ በለስ አስፓልት መንገድ

የፎቶው ባለመብት, Benishangul Gumuz Media

የምስሉ መግለጫ, መተከል ዞን በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ባሻገር ከአማራ ክልል በሚሻገሩ የፋኖ ኃይሎች እና ከኦሮሚያ ክልል በሚነሱ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች የተፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን አስተናግዷል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ግንቦት 21/2017 ዓ.ም. የመጀመሪያው ጥቃት የተፈጸመው በዳንጉር እና ጉባ ወረዳዎች አዋሳኝ በሚገኘው "አሳየ ሙላት እርሻ ልማት" በተባለ እርሻ ካምፕ ላይ ነበር። የእርሻው ባለቤት አቶ አሳየ ሙላት እንደሚናገሩት በዕለቱ ንጋት 11 ሰዓት ገደማ በተፈጸመው ጥቃት ሁለት ሴቶችን ጨምሮ ስምንት ሠራተኞች ተገድለዋል። ሁለት ሰራተኞች ደግሞ ቆስለዋል።

አቶ አሳየ፤ "[የሞቱ ሰዎችን] ሬሳ የሚያነሳ እንኳ ጠፍቶ፤ መከላከያ 'የክልሉ አድማ በታኝ ያንሳ ይላል'፤ አድማ በታኝ ደግሞ 'መከላከያን' ይላል። የወረዳ ፖሊስም ሊያነሳ አልቻለም። ሄደን፤ ሕይወታችንን መስዋዕት አድርገን ገብተን አውጥተን፣ ለቀብር አበቃናቸው። ሁለቱ ቁስለኞች ተርፈዋል" ሲሉ የነበረውን ሁኔታ ገልጸዋል።

"180 ኩንታል የአኩሪ አተር ዘር፣ 48 ኩንታል የሰሊጥ ዘር፣ የእርሻ ማከሚያ ኬሚካል፣ ከ200 ኩንታል በላይ ለሠራተኞች የተገዛ ዱቄት" መዘረፉንም ተናግረዋል።

በ2011 ዓ.ም. በእርሻው ላይ በተፈጸመ ጥቃት "ሦስት ሰዎች ተገድለው" እና "ሦስት ሰዎች ቆስለው" እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ አሳየ፤ በወቅቱ ሁለት ትራክተሮችን ጨምሮ "16 ሚሊዮን ብር" የሚገመት ሀብት እንደወደመባቸው አስረድተዋል። ዘንድሮ 500 ሄክታር ስፋት ወዳለው የእርሻ መሬታቸው ሲመለሱ "ሦስት ሚሊዮን ብር" ወጪ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

የአካባቢውን ባለሀብቶች ያስደነገጠው ሌላኛው ጥቃት የተፈጸመው ሰኔ 11/2017 ዓ.ም. ንጋት 12 ሰዓት ገደማ ላይ ነበር። ጥቃቱ የተፈጸመበት "በሪሁን እጅጉ የተቀናጀ እርሻ ልማት" እንደሌሎቹ የእርሻ ልማቶች ሁሉ በድጋሚ ወደ ሥራ የተመለሰው ዘንድሮ መሆኑን የድርጅቱ ባለቤት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዳንጉር ወረዳ የሚገኘው የእርሻ መሬት ላይ የሰሊጥ እና አኩሪ አተር ምርቶችን መዝራት ተጀምሮ እንደነበረም አስረድተዋል።

አቶ በሪሁን እጅጉ፤ "[እርሻው] ሰፊ ስለነበር ሁለት ካምፕ ነው የነበረኝ። ተደራጅተው መሽገው ነው የመጡት። አንድኛው ካምፕ ላይ ተኩስ ተነሳ። እርሻ ላይም የተሰማሩ ነበሩ። በጣም ከፍተኛ የሆነ የጥይት እሩምታ ሲመጣብን ምንድነው ብለን ተደናግጠን እያለ፤ እኛ ላይም ጥቃት ሲከፈት ነፍስ አውጪ ብለን ወጣን" ሲሉ በዕለቱ የተፈጠረውን ገልጸዋል።

በዚህ ጥቃት 10 የእርሻው ሠራተኞች መገደላቸውን ተናግረዋል። ሰባት ሴቶች እና አንድ ወንድ ሠራተኞች ደግሞ የገቡበት እንደማይታወቅ አስረድተዋል። "ይዘዋቸው ሄደዋል ነው የሚባለው" ሲሉ ታግተው ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

ይህ ጥቃት ከተፈጸመው ከሦስት ቀናት በኋላ ሰኔ 14 በዳንጉር ወረዳ በሚገኝ ሌላ እርሻ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሁለት ሰዎች ተገድለው፤ እናት እና ልጅ በታጣቂዎች መወሰዳቸውን ምንጮች ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ከሁለት ሳምንት በፊት ከአሶሳ ወደ ግልገል በለስ ከተማ እየተጓዘ በነበረ የሕዝብ መጓጓዣ አውቶብስ ላይ ሌላ ጥቃት መፈጸሙን ሁለት ምንጮች ገልጸዋል።

በዚህ ጥቃት 18 ሰዎች መቁሰላቸውን ተቃዋሚውን የፖለቲካ ፓርቲ፤ የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን (ጉሕዴን) ወክለው የክልሉ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ለሜሳ ኔኖ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን እና የጉሕዴን ሊቀ መንበር አቶ ግራኝ ጉደታ ስምምነቱ በተፈረበት ወቅት ተጨባብጠው

የፎቶው ባለመብት, Benishangul-Gumuz Region Communication

የምስሉ መግለጫ, በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት እና በጉሕዴን መካከል የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ተመላሽ ታጣቂዎች የወርቅ ማውጫ ማሽንን ጨምሮ የተለያዩ መቋቋሚያዎችን አግኝተዋል

እነዚህን ተከታታይ ጥቃቶች ተከትሎ በርካታ በእርሻ ልማት ላይ ተሰማሩ ባለሀብቶች አካባቢውን ጥለው መውጣታቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው አምስት ባለሀብቶች ገልጸዋል።

በጉባ ወረዳ በአኩሪ አተር፣ በሰሊጥ እና በለውዝ ምርት ላይ የተሰማሩ አቶ ሙላት አታለል የተባሉ ባለሀብት እነዚህ ጥቃቶች በፈጠሩት ስጋት የተነሳ እርሻቸውን ለቅቀው መውጣታቸውን ተናግረዋል። ለእርሻው ያዘጋጇቸውንም ግብአቶች ጥለው መውጣታቸውን የሚጠቅሱት አቶ ሙላት፤ "ከ28 በላይ ባለሀብት" ለቅቆ እንደወጣ እንደሚያውቁ አስረድተዋል።

ሌሎች ሁለት ባለሀብቶች ደግሞ የወጡ ባለሀብቶችን ቁጥር "ከ40 በላይ" ያደርሱታል።

የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ አመንቴ በበኩላቸው "45 አካባቢ" ባለሀብቶች ለቅቀው መውጣታቸውን ለቢሮው እንዳሳወቁ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ይህ ቁጥር በግል "ሥራ አቋርጫለሁ" ያሉ ባለሀብቶች ድምር መሆኑን የሚያስረዱት ኃላፊው፤ በአካባቢው ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ቢሮው በአካል በመሄድ ምን ያህል ፕሮጀክቶች ለቀው እንደወጡ አለማረጋገጡን አክለዋል።

"አካባቢው ስለተረበሸ እና የእንቅስቃሴ ስጋት ውስጥ ስለገባን በትክክል ስንት ሰዎች ከሥራ ውጪ እንደሆኑ ማረጋገጥ አልቻልንም። የምናገረው በለቀማ ከምናገኘው መረጃ ነው። ከዚህ ቁጥር በላይም ሊጨምር ይችላል" ብለዋል።

ባለሀብቶቹን ስጋት ላይ የጣለው ሁኔታ ከግንቦት ወር አንስቶ መታየት የጀመረ አዲስ እንቅስቃሴ መሆኑን የሚያነሱት አቶ አመንቴ፤ ይሁን እንጂ ቢሮው ይህንን ድርጊት የፈጸሙት ማናቸው የሚለውን በትክክል መናገር እንደማይችል አክለዋል።

"ማናቸው የሚለውን እርግጠኛ መሆን የምንችለው ከፀጥታ አካላት ጋር በምናደርገው የመረጃ ልውውጥ ነው። ግን የታጠቁ ሰዎች መሆናቸውን እና የታጠቁ ወጣቶች መሆናቸውን አረጋግጠናል" ሲሉ ተናግረዋል።

ጥቃት የደረሰባቸውን ጨምሮ ቢቢሲ ያነጋገራቸው አምስት ባለሀብቶችም የታጣቂዎቹን ማንነት በተመለከተ ተመሳሳይ አገላለጽ የላቸውም።

በተወሰኑት ባለሀብቶች፣ በጉባ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ኩምሳሬ እና በምክር ቤት አባሉ አቶ ለሜሳ ተደጋግሞ የተነሳው፤ "ሰላም ስምምነት ሲፈጸም ያልተስማማሙ እና መቀመጫቸውን በሱዳን ያደረጉ ታጣቂዎች" ናቸው የሚል ነው።

በጉባ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ፤ "የግል ፍላጎት ያላቸው፣ እጅ ያልሰጡ፣ ከነጭራሹ ያልገቡ፣ ጫካ ላይ ያሉ [ታጣቂዎች] አሉ" ብለዋል። "የሌላ አካል ተልዕኮ ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ናቸው። አብዛኛው ከሱዳን ነው የሚመጡት። እዚህ ያለ ታጣቂ የለም" ሲሉ ታጣቂዎቹን "በፀረ ሰላም ተልዕኮ አስፈጻሚነት" ከስሰዋል።

"ስምምነቱን ልቡ የተቀበለው ሁሉም አይደለም" የሚሉት የጉሕዴን አመራር እና የምክር ቤት አባሉ አቶ ለሜሳም በበኩላቸው፤ "የተወሰኑ ሱዳን ድንበር አካባቢ ቀርተው ነበር" ሲሉ ተመሳሳይ ሀሳብ ያነሳሉ።

"በፊት የጉሕዴን ታጣቂ ነበሩ። አንዳንዱ ሆን ብሎ ለሌብነት የተደራጀ ቡድን ነበር። ይሄ ቡድን ዝርፊያ እና ሰውን አግቶ ገንዘብ የሚፈልግ ቡድን [ነው]" ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በመተከል እና ካማሺ ዞኖች በትጥቅ ትግል ሲንቀሳቀስ የነበረው ጉሕዴን፤ ከክልሉ መንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት የፈጸመው ጥቅምት 2015 ዓ.ም. ነበር። ስምምነቱ ከተፈጸመ በኋላ የጉሕዴን አመራሮች በክልሉ መንግሥት ውስጥ በተለያዩ እርከኖች ሥልጣን አግኝተዋል።

ባንዲራ የያዘን ጨምሮ ወታደራዊ ልብስ የለበሱ ታጣቂዎች ቆመው

የፎቶው ባለመብት, Guba Woreda Communication

የምስሉ መግለጫ, ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ በመተከል ዞን ጉባ ወረዳ "በሱዳን ድንበር አካባቢ" ሲንቀሳቀሱ እንደነበር እና "አብደላ ኡስማን" በሚባል ግለሰብ የሚመሩ ታጣቂዎች "የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ከእነ ሙሉ ትጥቃቸው" እንደተመለሱ ተገልጾ ነበር

የጉሕዴን ታጣቂዎችም ወርቅ ማውጣትን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል። ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ በክልሉ በተካሄደው ምርጫ የተሳተፈው ጉሕዴን፤ በክልሉ ምክር ቤት ውስጥ ስምንት መቀመጫዎችን አግኝቷል።

በዚህ ምርጫ የምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ለሜሳ፤ ከዚህ ቀደም የጉሕዴን ታጣቂ ነበረ ያሉትን አንድ ግለሰብ ስም በመጥቀስ፤ ግለሰቡ የሚመራው የታጣቂዎች ቡድን "በእርሻ ሥራ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን፣ በወርቅ ቁፋሮ የተሰማሩ በሰላም የተመለሱ ወጣቶችንም እያስቸገረ ነው" ሲሉ ይከስሳሉ።

ታጣቂዎቹ መቀመጫቸው "በሰሜን ሱዳን" እንደሆነ የሚጠቅሱት አቶ ለሜሳ፤ "ወደ ሀገር ሲመጡ አንዴ በጉባ በኩል አድርገው ነው። በጉባ በአልመሃል አድርገው በዚያ አካባቢ ነው የሚገቡት" ይላሉ።

የጉባ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪው አቶ አህመድ፤ የሱዳን ድንበር ላይ የሚገኘው፤ "አልመሃል ክላስተር"፤ "አስተማማኝ ሰላም የሌለው" አካባቢ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ዋና አስተዳዳሪው "ከሱዳን መጥተዋል" ያሏቸው እና ሌሎችም ታጣቂዎች በአካባቢው እንደሚንቀሳቀሱ አስረድተዋል።

እነዚህ ታጣቂዎችን የሚደግፉ "ባለሀብቶች አሉ" የሚሉት አቶ አህመድ፤ እነዚህ ባለሀብቶች የታጣቂዎች እንቅስቃሴን ሽፋን በማድረግ "በተለይ ጠረፍ አካባቢ ወርቅ ቁፋሮ" እንደሚያካሂዱ በመጥቀስ ይከስሳሉ።

"እነዚህ ሰዎች [ታጣቂዎቹ] በሚንቀሳቀሱበት ሰዓት እነሱ ወርቅ ይቁፍራሉ፣ ሌሎች ሌሎች ነገሮችን ይሠራሉ። ባለፈው በተደረገው ኦፕሬሽን የእነሱ ንብረቶች እስከ ስካቫተር፣ ማሽኖች የተያዙበት ሁኔታዎች ነው ያሉት" ብለዋል።

የጉባ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪው በዚህ ምክንያት በእነዚህ አካባቢዎች በእርሻ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ"ጥሪም ሆነ ማስጠንቀቂያ "አለመተላለፉን" ይገልጻሉ። ግንቦት 21 ቀን ጥቃት ለተፈጸመበትን የእርሻ ልማት ባለቤት ስላለው የፀጥታ ስጋት "አስጠንቅቀው" እንደነበር ይናገራሉ።

ከዓመታት የሥራ መስተጓጎል በኋላ ዘንድሮ ወደ ሥራ ተመልሰው የነበሩት ባለሀብቶች ግን ከወረዳ፣ ከዞንም ሆነ ከክልል ባለሥልጣናት ይሄ ነው የሚባል ምላሽ አለማግኘታቸውን ያነሳሉ። የወረዳ እና የቀበሌ መዋቅሮችንም "ዝምታን መርጠዋል" በማለት ይከስሳሉ።

በዚህ የክረምት ወቅት የኤክስፖርት ምርቶችን ለመዝራት የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ለማሟላት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ማውጣታቸውን የሚናገሩት ባለሀብቶች፤ አሁን የሚዘራበት ጊዜ ማለፉን ይገልጻሉ።

ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ከክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ፣ ከሰላም እና ፀጥታ ቢሮ፣ ከመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ እንዲሁም ከመተከል ዞን እና ከዳንጉር ወረዳ አስተዳደሮች መረጃ ለማግኘት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም።