የውጭ ባለሀብቶች ችርቻሮ ንግድ ላይ ለመሰማራት ሱፐር ማርኬቶችን እንዲያቋቁሙ የሚያስገድደው ቅድመ ሁኔታ ተነሳ

ኩዊንስ ሱፐርማርኬት አዲስ አበባ

የፎቶው ባለመብት, MIDROC Investment Group/facebook

ኢትዮጵያ ውስጥ በችርቻሮ ንግድ ላይ መሰማራት በሚፈልጉ የውጭ ባለሀብቶች ላይ ተጥሎ የነበረው አምስት ሱፐርማርኬት ወይም ሁለት ሀይፐርማርኬት የማቋቋም ቅድመ ሁኔታ ተነስቶ፤ "2.5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ካፒታል ማስመዝገብ" በሚል ተተካ።

እንደ ቡና እና የቅባት እህል ያሉ ምርቶችን ኤክስፖርት ለማድረግ ፈቃድ በሚሰጣቸው የውጭ ባለሀብቶች ላይ ተቀምጦ የነበረው ወደ ውጭ መላክ ያለበት አስገዳጅ ዓመታዊ የምርት መጠንም እንዲነሳ ተደርጓል።

በውጭ ባለሀብቶች ላይ ተጥለው የነበሩት እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች የተነሱት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ባወጣው አዲስ መመሪያ ነው።

"በተከለሉ የወጪ፣ ገቢ፣ ጅምላ እና ችርቻሮ ንግድ ስራዎች የውጭ ባለሀብቶች ኢንቨስትመንት ተሳትፎ አፈፃፀም መመሪያ" የተባለው ይህ ህግ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ስም የወጣውን መመሪያ የሚሽር ነው።

የኢንቨስትመንት ቦርድ አዲሱን መመሪያ ያወጣው፤ በነባሩ ህግ "አቅሙ ያላቸው" ውጭ ባለሀብቶች በወጪ፣ የገቢ፣ የጅምላ እና የችርቻሮ ንግድ ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ ቢፈቀድም "እርምጃው በቂ ሆኖ ባለመገኘቱ" እንደሆነ በህጉ ላይ ሰፍሯል።

"የአገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች እኩል የውድድር ሜዳ እንዲያገኙ ማድረግ" እንዲሁም "የሚቀመጡ የፈቃድ ቅድመ-ሁኔታዎችን ግልፅ፣ ቀላል እና ተገማች" ማድረግ የሚሉትን ለህጉ መሻሻል በምክንያትነት የተጠቀሱ ጉዳዮች ናቸው።

ማሻሻያው፤ የውጭ ባለሀብቶችን "መተማመን ይበልጥ ማሳደግ" እና "ተጨማሪ የውጭ ካፒታል የሚሳብበትን አሰራር መዘርጋት" የሚል ዓላማዎች አሉት።

መጋቢት 2016 ዓ.ም. የወጣው የቀድሞው መመሪያ፤ ለአስርት ዓመታት ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ ተከልለው የቆዩትን የወጪ እና ገቢ እንዲሁም የጅምላ እና ችርቻሮ ንግዶች ለውጭ ሀገር ባለሀብቶችም ክፍት እንዲሆኑ የፈቀደ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሚመሩት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ የወጣው የቀድሞው መመሪያ፤ እነዚህን ዘርፎች ለውጭ ሀገር ባለሀብቶች ክፍት ሲያደርግ የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጦ ነበር።

የአዲስ አበባ ከተማ ህንጻዎች

የፎቶው ባለመብት, Mayor Office of Addis Ababa

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በችርቻሮ ንግድ ላይ ለመሰማራት ፈቃድ በሚጠይቁ የውጭ ባለሀብቶች ላይ ተጥለው የነበሩት ቅድመ ሁኔታዎች፤ ባለሀብቶቹ ምን ያህል ብዛት የንግድ ስፍራዎችን መገንባት እንዳለባቸው እና ስፋታቸው ምን ያህል መሆን እንዳለበት ጭምር የሚወስኑ ነበሩ።

በቀድሞው መመሪያ የውጭ ባለሀብቶች የችርቻሮ ንግድ ፈቃድ ለማግኘት በቅድመ ሁኔታነት ከተቀመጡት ሶስት አይነት የገበያ ስፍራዎች ቢያንስ አንዱን ማቋቋም ይጠበቅባቸው ነበር። የሚቋቋሙት የገበያ ስፍራዎች "በአንድ የባለቤትነት መዋቅር ስር የሚተዳደሩ" መሆን እንዳለባቸውም ተጠቅሷል።

በመመሪያው ላይ በቀዳሚነት የተቀመጠው የገበያ ስፍራ ሱፐር ማርኬት ነበር። በመመሪያው መሰረት ፈቃድ የሚጠይቅ የውጭ ባለሀብት በሶስት ዓመት ውስጥ "ቢያንስ በ2,000 ስኩዌር ሜትር" ስፋት ላይ ያረፉ አምስት ሱፐር ማርኬቶችን ለማቋቋም መስማማት አለበት።

ከእነዚህ ሱፐር ማርኬቶች ውስጥ ቢያንስ ሁለቱ ፈቃዱ ከመሰጠቱ በፊት መቋቋም እንዳለባቸው የሚደነግገው ህጉ፤ ቀሪዎቹ በሶስት ዓመት ውስጥ መቋቋም እንዳለባቸው አስፍሯል።

በሁለተኛነት የተቀመጠው አማራጭ ቅድመ ሁኔታ በሶስት ዓመት ውስጥ ሁለት ሀይፐር ማርኬቶች እንዲያቋቁሙ የሚያስገድድ ነው። ፈቃዱ ከመሰጠቱ በፊት ቢያንስ አንዱ ሀይፐር ማርኬት መቋቋም ያለበት ሲሆን ይህ አይነቱ የገበያ ስፍራ አምስት ሺህ ስኩዌር ሜትር ላይ ያረፈ መሆን እንዳለበት ተደንግጎ ነበር።

መመሪያው በሶስተኛ አማራጭነት ያስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ የውጭ ባለሀብቶች በአስር ሺህ ስኩዌር ሜትር ላይ ያረፈ አንድ ግዙፍ የገበያ ስፍራ መገንባት የሚያስገድድ ነበር።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ያወጣው አዲሱ መመሪያ፤ ከአንድ ዓመት በፊት የተቀመጡትን እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች ሽሯል።

በአዲሱ መመሪያ በችርቻሮ ንግድ ላይ የሚሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ተጥሎባቸው የነበረው የገበያ ስፍራ የማቋቋም ቅድመ ሁኔታ በአስገዳጅ የካፒታል መጠን ተተክቷል።

በአዲሱ መመሪያ የውጭ ባለሀብቶች ቢያንስ 2.5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ካፒታል እንዲኖራቸው ያስገድዳል። ይህ ካፒታል "በዓይነት እና በጥሬ ገንዘብ የተከፈለ" መሆን እንዳለበትም መመሪያው ያስረዳል።

ይህ ቢኖርም ግን "አነስተኛ ካፒታል" በመያዝ "መልካም ስም" ያላቸውን "ነጠላ ምርቶች" በችርቻሮ በመሸጥ መሰማራት የሚፈልጉ የውጭ ባሀብቶች ፈቃድ የሚያገኙበት መንገድ እንደሚኖር በመመሪያው ላይ ሰፍሯል። በዚህ መልኩ መሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች ፈቃድ የሚያገኙት የኢንቨስትመንት ቦርድ "በጉዳይ ላይ እየተመሰረተ ውሳኔ" ሲሰጥ ነው።

ቡና የሚለቅሙ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አዲሱ መመሪያ ጉልህ ማሻሻያ ያደረገበት ሌላኛው ጉዳይ በወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) ላይ መሰማራት የሚፈልጉ የውጭ ባለሀብቶች ተጥሎባቸው ከነበረው ቅድመ ሁኔታ ጋር የሚያያዝ ነው።

የውጭ ባለሀብቶች "ከገበያ በመግዛት" ኤክስፖርት ማድረግ የሚችሉት ጥሬ ቡና፣ የቅባት እህል፣ ጫት፣ ጥራጥሬ፣ የደን ውጤቶች፣ ቆዳ እና ሌጦ እንዲሁም ዶሮ እና የቁም እንስሳትን ነው።

ቀድሞው መመሪያ የውጭ ባለሀብቶች እነዚህን ምርቶች ኤክስፖርት ማድረግ የሚችሉት ፈቃዱን ባገኙበት ዓመት በህጉ የተቀመጠላቸውን አስገዳጅ የምርት መጠን ወደ ውጭ ለመላክ የሚስማሙ ከሆነ ነበር።

በዚህም መሰረት ጥሬ ቡና ለመላክ የሚፈልጉ የውጭ ባለሀብቶች ፈቃዱን ባገኙበት ዓመት "ቢያንስ 10 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምርት" ለመላክ መስማማት ነበረባቸው።

የቅባት እህሎችን መላክ የሚፈልጉ የውጭ ባለሀብቶች አምስት ሚሊዮን ዶላር፣ ጫት እና ጥራጥሬ ለሚልኩ ደግሞ አንድ ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምርት ለውጭ ገበያ የማቅረብ ግዴታ ተጥሎባቸው ነበር።

ቆዳ እና ሌጦ ለሚልኩ ባለሀብቶች የተቀመጠው ቅድመ ሁኔታ ፈቃድ ባገኙበት ዓመት ቢያንስ 500 ሺህ ዶላር የሚያወጣ ምርት ኤክስፖርት እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ነበር።

አዲሱ መመሪያ እነዚህን አስገዳጅ የኤክፖርት የምርት መጠን አስቀርቷል። በዚህ ምትክ የተቀመጠው ቅድመ ሁኔታ ባለሀብቱ፤ "በራሱ ወይም በታወቀ አገራዊ ወይም አለም አቀፍ አረጋጋጭ ተቋም የተዘጋጀ ዝርዝር የስብእና እና የአቅም መግለጫ ሪፖርት ማቅረብ አለበት" የሚል ነው።

ይህ ሪፖርት፤ "ባለሀብቱ በኢትዮጵያ መንግሥት ተቀባይነት በሚኖራቸው የማእቀብ ወይም ተመሳሳይ ገደቦች ዝርዝር ውስጥ ያለ መሆን አለመሆኑን የሚያረጋግጥ" መሆን እንዳለበት በመመሪያው ላይ ተጠቅሷል።

በተጨማሪም ሪፖርቱ፤ ባለሀብቱ "በተለይም በህገ-ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን፣ የእፅ ዝውውርን፣ ወይም ሽብርተኝነትን በገንዘብ ማገዝን" በተመለከተ ያሉትን "ያለውን ማናቸውም ተመክሮ ምርመራ" ያካተተ መሆን አለበት።