የውጭ ዜጎች በሊዝ የቤት እና የመሬት ባለቤት እንዲሆኑ የሚፈቅደው ረቂቅ አዋጅ ምን ይዟል?

የአዲስ አበባ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Adanech Abebie Facebook

የምስሉ መግለጫ, የአዲስ አበባ ከተማ

የኢትዮጵያ መንግሥት ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የውጭ ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት እንዳይሆኑ ዕገዳ ጥሎ የነበረውን ሕግ የሚሽር አዋጅ አርቅቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል።

"የውጭ ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ" የሚሆኑበትን አግባብ ለመደንገግ የወጣው አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበው ከሦስት ሳምንት ገደማ በፊት ሚያዝያ 23/2017 ዓ.ም. ነበር።

ረቂቅ አዋጁ ለ65 ዓመታት በውጭ ዜጎች ላይ ለተጣለው የመኖሪያ ቤት ባለመብትነት መብት ክልከላ መሠረት ሆኖ የቆየውን የፍትሀ-ብሔር ሕግ "ስርነቀል በሆነ መልኩ የሚቀይር እና የሚተካ" መሆኑን በማብራሪያው ላይ ሰፍሯል።

በ15 ገጾች የተዘጋጀው ይኸው ማብራሪያ የአዋጁ መሠረታዊ ዓላማ፤ "የውጭ ዜጎችን የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለመብትነት የሚመሠርት፤ እንዲሁም የመብቶችን ፈቃድ እና ምዝገባ አስተዳደርን የሚመራ ሁሉን-አቀፍ ሕግ ማቋቋሚያ" መሆኑን ያትታል።

ማብራሪያው በዚህ አዋጅ እንዲሳኩ ከሚጠበቁ "ዝርዝር ዓላማዎች" መካከል የውጭ ባለሃብቶች "በኢትዮጵያ የውጭ ካፒታልን ሥራ ላይ እንዲያውሉ ማበረታታት" ቀዳሚው ነው። አዋጁ ይህን ዓላማ የሚያሳካው የውጭ ዜጎች እና ባለሃብቶችን "እምነት በማጠናከር" መሆኑን ማብራሪያው ያክላል።

"የቤት ልማት እና ተደራሽነትን ይበልጥ ማነቃቃት፤ እየሰፋ የመጣውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት እና አቅርቦት ሚዛን በተገቢው መንገድ ማስጠበቅ" ሌላው በአዋጁ እንዲሳካ የሚፈለገው ዓላማ ነው።

በአራት ክፍሎች እና በ20 አንቀጾች የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጁ፤ የውጭ አገር ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ስለሚሆኑባቸው ሂደቶች፣ ቅድመ ሁኔታዎች እና አሠራሮችን ይዘረዝራል።

ከዚህ በተጨማሪም የውጭ ዜጎች የሚኖራቸውን መብት እና ግዴታዎች አስፍሯል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በረቂቅ አዋጁ መሠረት የማይንቀሳቀስ ንብረት "በውጭ ዜጋ በሊዝ ባለይዞታነት ወይም ባለቤትነት የሚያዝ መሬት ወይም የመኖሪያ ቤት" እንዲሁም "ተያያዥ ግንባታዎች" ማለት ነው።

መኖሪያ ቤት ደግሞ "ለመኖሪያነት ዓላማ የማከራየት መብት እንደተጠበቀ ሆኖ ለግለሰብ ወይም ለቤተሰብ መኖሪያነት የሚያገለግል፤ ለንግድ ዓላማ ማዋል የማይፈቀድ ቤት" የሚል ትርጓሜ ተሰጥቶታል።

ረቂቅ አዋጁ "ማንኛውም የውጭ ዜጋ. . . የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ መሆን ይችላል" ይላል።

ሆኖም ግን የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በመመሪያ "የተወሰኑ አገራት ዜጎች ወይም ዜግነት የሌላቸው የውጭ አገር ሰዎች" የዚህ መብት ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ሊያግድ እንደሚችል አዋጁ ያታትል።

የውጭ ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ለመሆን መመደብ ያለባቸው አንስተኛ የገንዘብ መጠን በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፍሯል።

ረቂቁ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ለመሆን ማንኛውም የውጭ ዜጋ፤ "የሊዝ ሙሉ ዋጋውን ጨምሮ ለአንድ መኖሪያ ቤት ግንባታ ሙሉ ዋጋ ወይም ለመኖሪያ ቤት ግዢ የሚመድበው አነስተኛ የገንዘብ መጠን ከ150,000 የአሜሪካን ዶላር ያነሰ ሊሆን አይችልም" ሲል ቅድመ ሁኔታ ያስቀምጣል።

የውጭ ዜጎች በአንድ ጊዜ ሊኖራቸው የሚችለው የማይንቀሳቀስ ንብረት ቁጥር በመመሪያ እንደሚወሰን ረቂቁ ያትታል።

ሆኖም ግን የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የአንስተኛ ገንዘብ መጠኑን ከፍ ወይም ዝቅ ሊያደርገው እንደሚችል በረቂቁ ላይ ሰፍሯል።

ሚኒስቴሩ ይህን ማሻሻያ ለማድረግ "የቤቶች ገበያ ወቅታዊ ሁኔታን፣ የከተሞች የማይንቀሳቀስ ንብረት አማካይ ዋጋን፣ የውጭ ዜጎች በቤቶች ገበያ ያላቸውን የተሳትፎ መጠን እና የአዋጁን ዓላማ ለማሳካት የሚረዱ ሌሎች ምክንያቶችን" መሠረት በማድረግ እንደሆነ ረቂቁ ያብራራል።

የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለመብት ለመሆን መሟላት ያለባቸው ተብለው በረቂቅ አዋጁ ከተዘረዘሩ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል "የወንጀል ሪከርድ የሌለበት መሆን" የሚለው አንደኛው ነው።

"የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለመብት ለመሆን የሚያስፈልግ አነስተኛ የገንዘብ መጠን ለማሟላት የሚያስችል በቂ አቅም ያለው መሆን"ም ሌላኛው ቅድመ ሁኔታ ነው።

ረቂቁ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ለሆኑ ውጭ ዜጎች ከሰጣቸው መብቶች መካከል "ከማይንቀሳቀስ ንብረቱ በሕጋዊ መንገድ የሚያገኘውን የኪራይ ወይም የሽያጭ ገቢ በወቅቱ ተመን በውጭ ምንዛሬ ወደ ውጭ አገር የማስተላለፍ መብት" የሚለው ይገኝበታል።

ከዚህ በተጨማሪም ለራሱ እና ለቤተሰቡ "ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲኖሩ የሚያስችል አግባብነት ባለው አካል የሚሰጥ የመኖሪያ ፈቃድ" ሌላኛው መብት ነው።

"ወደ ኢትዮጵያ መመላለስ እንዲችሉ የሚያደርግ አግባብነት ባለው አካል የሚሰጥ ለአምስት ዓመት የሚያገለግል የብዙ ጊዜ መመላለሻ ቪዛ" የማግኘት መብትም በአዋጁ ተሰጥቷቸዋል።

አዋጁ ግዴታዎችንም አስቀምጧል። "የሊዝ፣ የቤት ግዢ፣ የግንባታ ፈቃድ፣ ወይም ተያያዥ የመንግሥታዊ አገልግሎት ክፍያዎችን በኢትዮጵያ ተቀባይነት ባለው የውጭ ምንዛሬ ብቻ መክፈል" አንደኛው ነው።

የውጭ ዜጋ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ መሆን የማይችልባቸው ልዩ ቦታዎች ወይም የድንበር አካባቢዎች በመመሪያ እንደሚወሰኑ ረቂቁ ላይ ተቀምጧል።

ከዚህ በተጨማሪም "በመንግሥት ቀጥተኛ ድጎማ ለዜጎች በሚሠሩ የጋራ መኖሪያ ህንፃዎች ውስጥ" ውጭ ዜጎች የንብረት ባለቤት መሆን አይችሉም።

የውጭ ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ ለመሆን ከአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋም ወይም ምንጭ ገንዘብ መበደር ወይም ካፒታል ማሰባሰብ እንደማይችሉም ረቂቁ ላይ ሰፍሯል።

የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ መሆን የሚፍለጉ የውጭ አገር ዜጎች በቅድሚያ ከሚኒስቴሩ ፈቃድ ማግኘት እንዳለባቸው ረቂቁ አመልክቷል።