በሽፋን ስር ምርመራ ለሚያከናወኑ የተሰጠው በወንጀል ያለመጠየቅ መብት የፈጠረው ስጋት

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አዋጁን ባጸደቁበት ወቅት

የፎቶው ባለመብት, House of Peoples Representatives of FDRE

የምስሉ መግለጫ, ምክር ቤቱ ማሻሻያ አዋጁን በሶስት ተቃዉሞ በአንድ ድምጽ ተአቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽፋን ሥር (under cover) ምርመራ የሚያከናውን ሰው "ከአቅሙ በላይ" እና "ከፈቃዱ ውጪ" ለሚፈጽመው ከግድያ ውጪ የሆነ ወንጀል ክስ እንዳያቀርብበት የሚያደርግ የአዋጅ ማሻሻያ ማክሰኞ ሰኔ 10/2017 ዓ.ም. አጽድቋል።

ከተወሰኑ የምክር ቤቱ አባላት መጠነኛ ተቃውሞ የገጠመው አዋጅ "በወንጀል የተገኘ ንብረት ሕጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር" የወጣ ነው።

ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት 12 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየው ባለ 58 አንቀጽ አዋጅ ላይ ከመጠነኛ እስከ ጉልህ ማሻሻያዎች ተደርገዋል።

ከእነዚህ ማሻሻያዎች መካከል በሽፋን ሥር ስለሚደርግ ምርመራ እና በቁጥጥር ሥር የሚደረግ ማስተላለፍን የሚመለከተው ድንጋጌ ላይ የተደረገው ለውጥ በምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ ተነስቶበታል።

አዋጁ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብን ወይም ሽብርተኝነት በገንዘብ መርዳትን በተመለከተ ማስረጃ ለማግኘት በሽፋን ምርመራ ሊደረግ እንደሚችል ያስቀምጣል።

አዋጁ በሽፋን ሥር የሚደረግ ምርመራን የሚያከናውን ሰው "ከአቅሙ በላይ" ወይም "ከፈቃዱ ውጪ" ሆኖ "ከግድያ ወንጀል በስተቀር ለሚፈጽመው የወንጀል ድርጊት የወንጀል ክስ አይቀርብበትም" ይላል።

አዋጁን ለማጽደቅ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ለዚህ ድንጋጌ አንድ አንቀጽ ማብራሪያ አካትቷል።

ልዩ የምርመራ ዘዴን የሚያከናውን ሰው "የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚሠራ" መሆኑን የጠቆመው ባለ አንድ አንቀጽ ማብራሪያው፤ "ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያት. . . ወንጀል ቢፈጽም"፤ "ከወንጀል ክስ ነጻ ስለሚሆንበት አግባብ መደንገግ ሥራውን ውጤታማ የሚያደርገው" መሆኑን ይገልጻል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ማሻሻያው ይህን ቢልም ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ግን ድንጋጌው "ለሰብዓዊ መብት ጥሰት በር ይከፍታል" ሲሉ ይሞግታሉ።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያም "ይህ ድንጋጌ ለአስፈጻሚው አካል ያልተገራ፣ ክፍት የሆነ ለቁጥጥር የማይመች ሥልጣን ሰጥቷል" ይላሉ።

አዋጁ "ከአቅም በላይ የሚለውን ሐረግ በግልጽ እና በዝርዝር ማስቀመጥ ነበረበት" የሚሉት አቶ ያሬድ፤ "ይህ ለተሳሳተ ክፍተት በተለይ ለመርማሪ አካላት በእንዝህላልነት ወይም ሆነ ብለው ለሚፈጽሟቸው ሕገ ወጥ ሥራዎች የሕግ ሽፋን መስጠት ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ከግድያ ወንጀል በስተቀር" የሚለው የአንቀጹ ሐረግም እንዲሁ ለትርጉም የተጋለጠ መሆኑን አቶ ያሬድ ያነሳሉ። "ከምርመራ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ስቅየት (torture)" መሆኑን የጠቆሙት አቶ ያሬድ፤ "እስረኞችን ወይም በምርመራ ላይ ያሉ ሰዎችን በማሰቃየት ተግባር ውስጥ በጣም ቋሚ የሆኑ እና መለስተኛ የአካል ጉዳቶችን ማድረስ ሊኖር ይችላል" ሲሉ ሕጉ ለሰብዓዊ መብት ጥሰት መንገድ ሊያበጅ እንደሚችል ይጠቁማሉ።

ከዚህ በተጨማሪም "በማናቸውም ሁኔታ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ባለ አገር ውስጥ እንኳን መፈጸም ከሌለባቸው ወንጀሎች አንዱ ስቅየት ነው፤ እና ይሄ አዋጅ ግን የማይገባ ንብረት አፍርቷል የተባለን ሰው በስቅየት ምርመራ ማድረግን ይፈቅዳል" ሲሉ ስጋታቸውን ለቢቢሲ አጋርተዋል።

"አገሪቷ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለ፤ እስረኞች የማሰቃየት ተግባር ይፈጸምባቸዋል፤ ፖሊሶች ጠርጥረው የያዟቸውን ሰዎች ይደበድባሉ ያሰቃያሉ፤ በምርመራ ጊዜ እነዚህን ሕጋዊ የማድረግ ያህል ነው። የዓለም አቀፍ ሕጎችን ጭምር የሚጥስ ድንጋጌ ነው" ሲሉ ያክላሉ።

ሌላኛው ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዓለም አቀፍ ወንጀል ሕግ ባለሙያው አቶ ካሳሁን ሞላ ይልማ የአቶ ያሬድን ስጋት ይጋራሉ።

አቶ ካሳሁን ይህ ድንጋጌ አንድ በሽፋን ምርመራ የሚያደርግ ግለሰብ "ሕገ ወጥ ሊሆኑ የሚችሉ ድርጊቶችን ከመፈጸሙ በፊት በቅድሚያ ፈቃድ እንደሚያስፈልገው በግልጽ አላስቀመጠም" ይላሉ።

"እንዲህ ዓይነት ጥበቃ ከሌለ፣ የዳኝነት ወይም የዐቃቤ ሕግ ቁጥጥር ዘዴ የለም" የሚሉት አቶ ካሳሁን፤ "በሌሎች አገራት ያሉ ሕጎች የወንጀል ተጠያቂነት ከመቅረቱ በፊት ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ወይም ከፍትህ አካላት ፈቃድ እንዲኖር ያስገድዳሉ" ሲሉ የሌሎች አገራትን ተሞክሮ ያነሳሉ።

ድንጋጌው በግልጽ "ከግድያ ወንጀል በስተቀር" የሚል ሐረግ ቢያካትትም "እንደ ስቅየት፣ ኢ-ሰብአዊ ወይም ክብርን የሚያዋርድ አያያዝን የመሳሰሉ ከባድ ወንጀሎችን መጥቀስ አልቻለም" ይላሉ።

እነዚህ ድርጊቶች በዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና ድንጋጌዎች "በማናቸውም ሁኔታ ሊፈጸሙ የማይገባቸው" መሆናቸውን የሚጠቅሱት ባለሙያው፤ ሊፈጸሙ የማይገባቸው ወንጀሎች ካልተዘረዘሩ "አዋጁ ላይ ያለው የቃላት አገባብ መርማሪዎችን ከከባድ ጥሰቶች ተጠያቂነት እንደመጠበቅ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ሕጉ ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢፈጠር ሊጣሱ ወይም ምክንያት ሊቀርብባቸው የማይችሉ ወንጀሎችን በግልጽ መዘርዝር ይገባዋል" ሲሉም ያክላሉ።

መርማሪው የወንጀል ክስ የማይቀርብበት ድርጊቱ የተፈፀመው "ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያት እና ከፈቃዱ ውጪ" ከሆነ የሚለው አሻሚ እና ግልጽነት ጎደለው መሆኑን አቶ ካሳሁን ይጠቁማሉ።

"ይህ የአተረጓጎም ክፍተቶችን ይፈጥራል። ሌሎች አገራት 'አስፈላጊነት እና ተመጣጣኝነት' ያሉ በደንብ የተረጋገጡ የሕግ መስፈርቶችን ይጠቀማሉ፤ይህም ከክስ ነጻ የመሆኑ መብት በጠባብ መተርጎማቸውን ያረጋግጣሉ" ሲሉ ያብራራሉ።

"የሕግ አስከባሪ ተቋማት ሥልጣናቸውን አላግባብ መጠቀም የተለመደ በሆነባት ኢትዮጵያ ለመርማሪዎች ሰፊ እና ግልጽነት የጎደለው ያለመከሰስ መብት ያለ ግልጽ ጥበቃ መስጠት አደገኛ ነው" ሲሉ አቶ ካሳሁን ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ቢቢሲ ካነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች በተጨማሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ማክሰኞ ዕለት ነበረው ስብሰባ ድንጋጌው ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

ከኦሮሚያ ክልል ዳኖ ምርጫ ክልል ብልጽግና ፓርቲን ወክለው የምክር ቤት አባል የሆኑት የገቡት ዶ/ር አለሙ ጎንፋ ድንጋጌው "ትንሽ ከባድ መስሎ ታይቶኛል" ብለዋል።

"ወንጀል ፈጽሞ አለመጠየቅ ትክክለኛ አይመስለኝም" ያሉት ዶ/ር አለሙ፤ "ወይም ድርጊቶቹ ተዘርዝረው ሕጋዊ መብት የተሰጠው ሰው የሚወስዳቸው እርምጃዎች ወንጀል አይደሉም ማለት አለብን" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የተቃዋሚው አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ተወካይ የሆኑት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔም በተመሳሳይ ድንጋጌው ላይ ያላቸውን ተቃውሞ አሰምተዋል።

ዶ/ር ደሳለኝ "ለምሳሌ የሽፋን መርማሪው ከወንጀለኛው ጋር ተደራድሮ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መቀበሉን ብናውቅ አይጠየቅም ማለት ነው። ስቅየት (torture) ቢፈጽም ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ ቢፈጽም አይጠየቅም ማለት ነው?" የሚል ጥያቄ አቅርበዋል።

የምክር ቤት አባሉ አክለውም "መሆን ካለበት የሰብዓዊ መብቶች እና ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ላይ የተካተቱ ወንጀሎችን አለመፈጸሙ [ነው]። እንዲሁም ደግሞ ድርጊቱ ራስን የመከላከል መሆኑ ታይቶ እንጂ ያልተገደበ ሥልጣን መስጠት ለእነዚህ መርማሪዎች የዜጎችን መብት በከፍተኛ ሁኔታ የሚጋፋ ነው ብዬ አስባለሁ" ብለዋል።

"ምርመራ ለሚያካሂዱ ሰዎች ከለላ የሰጠንበት መንገድ እንደገና ቢታይ የሚል ሃሳብ አለኝ" ያሉ አንድ ሌላ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው፤ "[መርማሪው] ከመግደል ውጪ ያለውን የፈለገውን እንዲፈጽም ዕድል እየሰጠነው ነው፤ እየቀጠቀጠ ምርመራ አካሂዳለው ቢል መብቱ ነው ማለት ነው?" ሲሉ ጠይቀዋል።

አባሉ አክለውም "እንደዚህ ዓይነት መብቶች የምንሰጥ ከሆነ በከፍተኛ ሁኔታ የዜጎችን የሰብዓዊ መብት የሚጥስ በመሆኑ ይህ አንቀጽ ቢሻሻል የሚል ሃሳብ አለኝ፤ ካልሆነ ግን ያልተገደበ መብት ሰጥተን የዜጎችን መብት የሚጥስ ነው" ብለዋል።

ማሻሻያ አዋጁ እንዲጸድቅ ለፓርላማ ያቀረበው የሕግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኢሳ ቦሩ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

አቶ ኢሳ "ይሄ ከመደበኛ ውጪ ጥላ ውስጥ ሆኖ የሚደረግ እጅግ በጣም የተወሳሰበ ልዩ ምርመራ ነው። ከአቅም በላይ በሆነ እና ከዕውቀቱ በላይ' የሚለው ሐረግ ብቻ በቂ ነው። እኛ እንደውም ያልግባብ ጥቅም ላይ ይውላል [abuse]፤ በዚያ ምክንያት የሰው ሕይወት መጥፋት የለበትም፤ ስለዚህ ከግድያ ውጪ መሆን አለበት የሚለውን ጨምረንበታል" ሲሉ አብራርተዋል።

"በአብዛኛው ኢትዮጵያ በራሷ ተነስታ አንድ የፖለቲካ ቡድን ለማጥቃት ያደረገችው አይደለም፤ ሽብርተኝነት አምርረው የሚዋጉ አገራት በአጠቃላይ ጠንካራ ሕግ አላቸው። ኢትዮጵያም ጠንካራ ሕግ ነበራት ከጥቂት አንቀጾች ውጪ" ሲሉ አቶ ኢሳ አክለዋል።

"'ለabuse የተጋለጠ ነው' ለሚለው ከግድያ ውጪ የሚለው የገባው ለዚያ ነው" ያሉት አቶ ኢሳ፤ "ሁለት ነገር ነው የሚታየው፤ አውቆ ነው ወይስ በቸልተኝነት ነው የፈጸመው? የሚለው ከዚህ ውጪ ከሆነ ግን ጥፋተኛ አይደለም ማለት ነው" ብለዋል።