በምዕራብ ጎንደር በአንድ ቀን ቢያንስ 16 ሹፌሮች በታጣቂዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, West Gondar Comm.
በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን "በታቀደ ጥቃት" የአፈር ማዳበሪያ ጭነው ሲጓዙ የነበሩ ቢያንስ 16 ሹፌሮች ሲገደሉ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁት ደግሞ መታገታቸውን የአካባቢው አስተዳደር እና የአሽከርካሪዎች ማኅበር ተናገሩ።
በዞኑ መተማ ወረዳ ልዩ ስሙ መቃ በተባለ አካባቢ ሰኞ ሰኔ 16/2017 ዓ.ም. ከቀኑ 11፡30 ገደማ የአካባቢው አስተዳደር "በቅማንት ታጣቂዎች" ተፈጽሟል ባለው ጥቃት ንፁሃን መንገደኞች እና ሹፌሮች መገደላቸው ተነግሯል።
አብዛኞቹ ሟቾች ከጂቡቲ ማዳበሪያ ጭነው በፀጥታ ኃይሎች ታጅበው ሲጓዙ የነበሩ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች መሆናቸው ተነግሯል።
ስለ ጥቃቱ ሰፋ ያለ መግለጫ ያወጣው የዞኑ አስተዳደር መከላከያ ሠራዊት እና የፀጥታ ኃይሎች ላይ "ታቅዶ፣ ሆን ተብሎ፤ ታስቦበት የተዘጋጀ" ሲል ጥቃቱን የገለፀ ሲሆን፤ ሹፌሮች መገደላቸውን አስታውቋል።
ጽንፈኛ ሲል የጠራቸው እና ለበርካታ ዓመታት አካባቢውን በማወክ የከሰሳቸው የቅማንት ታጣቂዎች "ኪስ ቦታዎችን" በመያዝ የፀጥታ ኃይሎች ላይ ተኩስ መክፈታቸውን ገልጿል።
ታጣቂዎቹ ከአንድ ቀን በኋላም ረቡዕ ሰኔ 18/2017 ዓ.ም. ተመሳሳይ ጥቃት በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ላይ መፈፀማቸውን ዞኑ አስታውቋል።
ምንም እንኳ ጥቃቱ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎችን ዒላማ ያደረገ እና 'የታቀደ ጥቃት' ቢልም፤ ዞኑ የፀጥታ ኃይሎች ላይ ስለደረሰው ጉዳት ያለው ነገር የለም።
"መስመሩ ሁሌም በተደጋጋሚ ሹፌር የሚታገትበት፣ የሚገደልበት እና የሚዘረፍበት ነው" የሚሉት የጣና የከባድ አሽከርካሪዎች ማኅበር የሥራ ኃላፊ፤ በአካባቢው ሦስት ቦታዎች ላይ "በጣም የተደራጁ" ያሏቸው ታጣቂዎች ሹፌሮችን ዒላማ እንደሚያደርጉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን ከሱዳን ጋር የሚያገናኝ እና የአገሪቱ የወጭ እና ገቢ ንግድ መስመር የሆነው የመተማ መንገድ ለአሽከርካሪዎች የስጋት ቀጣና መሆኑን ገልፀው፤ መንገዱ ለሁለት ወራት ያህል ተዘግቶ እንደቆየም ጠቁመዋል።
"ፊት ለፊት፤ በአምስት እና ስድስት ጥይት መስታወት [መመታቱን]" የተናገሩት ኃላፊው፤ "ተኩስ ነው የተከፈተባቸው" ሲሉ ስለጥቃቱ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, West Gondar Comm.
የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳደር ታጣቂዎቹ ሹፌሮችን ከመኪና እያስወረዱ "በጭካኔ ጨፍጭፈዋቸዋል" ብሏል።
ከሟቾቹ ውስጥ ባለትዳር እና የሦስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ሰለሞን ሙሳ የተባሉ የከባድ መኪና አሽከርካሪ እንደሚገኙበት አንድ የቤተሰብ አባል ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የግለሰቡን መገደል ማክሰኞ ሰኔ 17/2017 ዓ.ም. ስልካቸው ላይ ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያደርሱ "ገዳዮቹ" እንዳረዷቸው የተናገሩት የቤተሰብ አባሉ፤ አስከሬን እየጠበቁ መሆኑን ገልፀዋል።
"ደኅንነቱ ላይ ስጋት ነበረን። የነበረው ሁኔታ ጥሩ እንዳልነበር አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። የሥራ እና የሕይወት ጉዳይ ስለሆነ ብቻ ነበር የሄደው፤ ቤተሰብ ስላለ ግዴታ የቤተሰብ አስተዳዳሪ፤ የልጆች አባት ስለሆነ ነው" ብለዋል።
ቤተሰባቸው "ጥልቅ ሐዘን ላይ" መሆኑን የተናገሩት ግለሰቡ፤ አስከሬን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በጥቃቱ "በጣም ብዙ ሰዎች" እንዲሁም ከ20 የማያንሱ ሹፌሮች መገደላቸውን እንደሰሙም አክለው ተናግረዋል።
ሰኞ ዕለት በተፈፀመው ጥቃት ማኅበሩ ባሰባሰበው መረጃ 21 ሹፌሮች ሲገደሉ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሹፌሮች ደግሞ ታግተው ተወስደዋል ብለዋል።
ዞኑ ባወጣው መግለጫ 16 ሹፌሮች መገደላቸውን አስታውቋል።
ሟቾቹ አብዛኞቹ ወደ ገንደውሃ ከተማ ማዳበሪያ የጫኑ አሽከርካሪዎች ሲሆኑ፤ ስድስት የአነስተኛ የሕዝብ ተሽከርካሪ ሹፌሮች፣ ሦስት የጥቁር አባይ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ አሽከርካሪዎች፣ ሸቀጥ የጫኑ ሹፌሮች እንደሚገኙበት የጣና የከባድ አሽከርካሪዎች ማኅበር የሥራ ኃላፊ ተናግረዋል።
ሟቾቹ የቤተሰብ አስተዳዳሪ እንደሆኑ የገለጹም ሲሆን፤ አንድ በግላቸው የሚያውቋቸው የሦስት ልጆች አባት ከሟቾቹ ውስጥ መሆኑን ተናግረዋል።
"የነገ የልጆቹ ዕጣ ፈንታ ምንድን ነው? ማነው የሚያጎርሳቸው? ማነው የሚያለብሳቸው? ኑሮው ይታወቃል። የብዙ ቤተሰቦች ሕይወት በአሽከርካሪው ሥራ ላይ የተወሰነ ነው። ከአገር አገር ስለሚንቀሳቀስ፤ ስለሚዘዋወር ቤት ያለው ሰው ልጆችን ያሳድጋል እንጂ ወጥቶ የመሥራት ልምድ የለም" ሲሉ ግድያው የሚያስከትለውን "ማኅበራዊ ምስቅልቅል" ጠቅሰዋል።
ቢቢሲ ግድያውን ፈፀሙ የተባሉትን የቅማንት ታጣቂዎች ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
ባለፈው ኅዳር 2017 ዓ.ም. በመንግሥት እና በታጣቂ ቡድኑ መካከል በተደረገ ውይይት ስምምነት መደረሱን መከላከያ ሠራዊት አስታውቆ ነበር።
የቅማንት ታጣቂዎች ይህን ስምምነት "ጊዜ መግዣ" እንዳደረጉት የገለፀው የምዕራብ ጎንደር አስተዳደር፤ ቡድኑ የተሰጠውን የሰላም ዕድል አልተቀበለም ሲል ወቅሷል።















