የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከምርጫ ጋር ለተያያዙ ሥራዎች ከውጭ ምንጭ ገንዘብ እንዳያገኙ የሚከለክል ሕግ ተረቀቀ

ለመምረጥ ሰልፍ የያዙ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ፤ አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለ'ፖለቲካ አድቮኬሲ'፣ የመራጮች ትምህርት፣ ምርጫ መታዘብ እና ማንኛውም ከምርጫ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ለመሥራት ከውጭ የፋይናንስ ምንጭ ገንዘብ እንዳይቀበሉ የሚከልክል ድንጋጌ ተካቶበት ሊሻሻል ነው።

የማሻሻያውን ረቂቅ የፍትህ ሚኒስቴር እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በጋራ እንዳዘጋጁት የፍትህ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግ እና ፍትህ አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ በላይነህ ይርጋ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ገልጸዋል።

አቶ በላይነህ ይህ የገለጹት ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ከመንግሥት ተቋማት የተውጣጡ ተወካዮች በተሳተፉበት እና ማሻሻያ ረቂቁ ላይ በተደረገ ውይይት ነው።

በዚህ ውይይት ለተሳታፊዎች የቀረበው እና ቢቢሲ አማርኛ የተመለከተው የ'ፓወር ፖይንት' ሰነድ ከስድስት ዓመታት በፊት የወጣው አዋጅ ላይ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈለገበትን ምክንያት እና የሚደረጉ ማሻሻያዎችን በዝርዝር ያሳያል።

ሰነዱን ለተሳታፊዎች ያቀረቡት በፍትህ ሚኒስቴር የሕግ ጥናትና ማርቀቅ ዳይሬክተር ጄነራል፣ አቶ አዲሱ ጌትነት "አዋጁ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ የተስተዋሉ ክፍተቶችን ለማስተከካል" ማሻሻያ ማድረግ ማስፈለጉን ገልጸዋል።

"የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንቅስቃሴ የሕዝብ እና የአገርን ጥቅም ባረጋገጠ መልኩ እንዲሆን ማድረግ" ሌላው አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገበት ምክንያት መሆኑ በሰነዱ ላይ ሰፍሯል።

ዓለም አቀፉ የመብቶች ተቆርቋሪ ድርጅት የሆነው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይህ ረቂቅ ሕግ ከዚህ ቀደም በአገሪቱ ውስጥ የነበረውን ቁጥጥር የበዛበት ለተቃውሞ እና ለሁከትን ምክንያት ከሆኑ ሕጎች ትምህርት አለመወሰዱን እንዲሁም የተካሄዱ ማሻሻያዎችን ወደ ኋላ የሚመልስ ነው በማለት ስጋቱን ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ካደረጓቸው ጉልህ ለውጦች መካከል፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን የሚመለከተውን አዋጅ ማሻሻል ቀዳሚው ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሥራ ላይ ያለው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ጸድቆ ወደ ሥራ የገባው ጠ/ሚ ዐቢይ ሥልጣን ላይ ከወጡ አንድ ዓመት በኋላ ነው።

አዋጁ ከዚያ በፊት የነበረውን እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን 'አያሠራም' የሚል ትችት ሲቀርብበት የነበረውን የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ ሽሮታል።

ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማትን የሚመለከቱ አዋጆች እንዲሁም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅም ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አዎንታዊ ተጽዕኖ ያሳርፋል የሚል ግምት ተይዞ ነበር።

ነገር ግን ከአምስት ወራት በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን "አላሠራ ያሉ አዋጆችን" እንዲያሻሽል "አቅጣጫ" አስቀምጦ ነበር።

ቋሚ ኮሚቴው ይህን አቅጣጫ ያስቀመጠው በጥር ወር መጀመሪያ በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ባደረገው "የመስክ ምልከታ" ነው።

በጊዜው የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ "መሥሪያ ቤቱ የሚሠራቸው ሥራዎች ይበልጥ ውጤታማ እንዳይሆኑ የሚያደርግ የሕግ ክፍተት" መኖሩን ለቋሚ ኮሚቴው ተናግረው ነበር።

አቶ ሳምሶን አክለውም የሚመሩት መሥሪያ ቤት "አዋጁ እንዲሻሻል እየሠራ መሆኑን" ስለመናገራቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወቅቱ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።

ከሰባት ዓመት በፊት የሕግ እና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ ተቋቁሞ የሕግ ማሻሻያዎችን በሚያከናውንበት ወቅት፣ በጊዜው ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ከሚባለው ተቋም ከፍተኛ ተቃውሞ ይገጥማቸው እንደነበር ሕጎችን የማርቀቅ ኃላፊነት ተሰጥቶት የነበረው የባለሙያዎች ቡድን አባላት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አንድ የቡድኑ አባል የነበሩ ግለሰብ "ኤጀንሲው ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማኅበራት አዋጅ ማሻሻያ ጋር በተያያዘ የተቀናጀ የግል እና የሕዝብ ዘመቻዎችን አድርጓል" ሲሉ ያስታውሳሉ።

ከዚህ በተጨማሪም "በርካታ ዛቻዎችን የስም ማጥፋት ዘመቻዎችን ጨምሮ የኤጀንሲው ሠራተኞች ሕዝባዊ ቅስቀሳ ከማድረግ ጀምሮ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን እስከማውጣት እንዲሁም በብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው ረቂቁን በመቃወም ቃለ መጠይቅ እስከ መስጠት ደርሰዋል" ይላሉ።

የኢትዮጵያ ባንዲራ እና ኮሮጆ

የፎቶው ባለመብት, Vepar5

አሁን በሥራ ላይ ያለው ረቂቅ እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት "ኤጀንሲው የከፍተኛ ደረጃ ባለሥልጣናትን በተሳካ ሁኔታ ማግባባት እና ተፎካካሪ ረቂቅ ሕግ ለማውጣት ፍቃድ እንደተሰጠው" የቡድኑ አባል ያክላሉ።

ሕጉ ከጸደቀም በኋላ ግን ስያሜውን ወደ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የለወጠው ተቋም ተቃውሞውን እንዳላቋረጠ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ "አዋጁ ያስገኛቸውን ለውጦች ወደ ኋላ የሚመልሱ ተደጋጋሚ ረቂቅ መመሪያዎችን አቅርቧል" የሚሉት ቢቢሲ ያነጋገራቸው ባለሙያ፤ "ምንም እንኳን እንደ ቀድሞው ሕግ አፋኝ ባይሆንም የተቋምን አስተዳደራዊ ሥልጣኖች የሚያጠናክሩ ደንቦች እና መመሪያዎችን አውጥቷል" ሲሉ ያስረዳሉ።

ከጅምሩ በባለሥልጣኑ ተቃውሞ የገጠመው አዋጅ ከጸደቀ ስድስት ዓመት በኋላ አዋጁ እንዲሻሻል" ቋሚ ኮሚቴው "አቅጣጫ" ካስቀመጠ አምስት ወራት በኋላ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ የማሻሻያ ረቂቁ ላይ ውይይት ተደርጓል።

ውይይት የተደረገበት ረቂቅ በሥራ ላይ ካለው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ውስጥ 12 አንቀጾች ላይ ሙሉ በሙሉ እና በከፊል ማሻሻያዎችን አድርጓል።

ረቂቁ ሙሉ በሙሉ ሰርዞ በአዲስ የተካው ቀዳሚው ክፍል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ቦርድን የተመለከተው ድንጋጌ ነው።

ማሻሻያ ረቂቁ 11 የነበሩትን የቦርዱን አባላት ቁጥር ወደ ሰባት ዝቅ አድርጓቸዋል።

ከእነዚህ ሰባት የቦርድ አባላት መካከል አራቱ በፍትህ ሚኒስትሩ የሚሰየሙ የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች ናቸው። በሥራ ላይ ባለው አዋጅ የመንግሥት ተወካዮች ቁጥር ሦስት ነበር።

በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ይሰየሙ የነበሩ የቦርድ አባላት ደግሞ ከሦስት ወደ ሁለት ዝቅ ተደርጓል።

ከዚህ በተጨማሪም የአካል ጉዳተኞች እንዲሁም ሴቶች እና ወጣት ማኅበራት በቦርዱ ውስጥ የነበራቸው ውክልና በማሻሻያ ረቂቁ ቀርቷል።

ቀሪዎቹ ጉልህ ማሻሻያዎች የተደረጉት የድርጅቶች ምዝገባ፣ የሒሳብ ሪፖርት እና ሕግን ማስከበር የተመለከቱ ድንጋጌዎች ላይ ነው።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የድርጅቶችን ምዝገባ ጥያቄ የማይቀበልባቸውን ምክንያቶች በሚያትተው የአዋጁ ክፍል ላይ ሁለት አዳዲስ መስፈርቶች ተካትተዋል።

በረቂቁ ውስጥ በተካተተው አዲስ ድንጋጌ መሠረት "ድርጅቱ ለአገር ደኅንነት ስጋት መሆኑ በባለሥልጣኑ የሚታመንበት ከሆነ" የምዝገባ ጥያቄው ውድቅ ሊደርግ ይችላል።

ባለሥልጣኑ "ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር የአገር ደኅንነት ስጋት መሆኑን" እንደሚወስን እንዲሁም "ለዚህ አፈጻጸም ሲባል አስፈላጊውን መመሪያ" እንደሚያወጣ ረቂቁ ማሻሻያው ላይ ሰፍሯል።

አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የሰብዓዊ መብት ባለሙያ እና ተመራማሪ ይህ የማሻሻያ ረቂቁ ድንጋጌ በ2001 ዓ.ም. ወጥቶ የነበረውን እና ብዙ ትችት ሲቀርብበት የነበረው አዋጅ ላይ ያለውን "የቅድመ ምዝገባ ፈቃድ እንደገና ማምጣት ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በማሻሻያው የተካተተው ድንጋጌ ከ2001ዱ ድንጋጌ በቃላት አጠቃቀም የተለያየ ቢሆንም "ከሚያስከትለው ሕጋዊ ውጤት፣ ተግባራዊነቱ እና ተጽዕኖው አንጻር ተመሳሳይ ይሆናል" ሲሉ ያክላሉ።

ከ16 ዓመታት በፊት ወጥቶ በነበረው አዋጅ መሠረት "የሕዝብን ሠላም ለሚያደፈርስ ተግባር ወይም የኢትዮጵያን ደኅንነት እና መረጋጋት ለመጉዳት መጠቀሚያ ሊሆን ይችላል የሚያሰኝ በቂ ምክንያት ሲኖር" ድርጅቱ አይመዘገብም ነበር።

ሌላው በማሻሻያው ጉልህ ለውጥ ያደረገበት የአዋጅ ድንጋጌ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን የሥራ ነጻነት የሚመለከተውን ክፍል ነው።

ረቂቁ የነባሩን አዋጅ ሁለት ንዑስ አንቀጾች ሰርዞ በአዲስ ተክቷቸዋል።

በአዳዲሶቹ የረቂቁ ንዑስ አንቀጽ መሠረት የውጭ ድርጅቶች እና ኢትዮጵያ ውስጥ በሚኖሩ የውጭ አገር ዜጎች የተመሠረቱ አገር በቀል ድርጅቶች ማድርግ የሚችሏቸውን የገንዘብ ድጋፎች ዘርዝሯል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ህበረት ለምርጫ መለያ ሎጎ

የፎቶው ባለመብት, Coalition of Ethiopian Civil Society Organizations for Election

እነዚህ ድርጅቶች "በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ" ለአገር በቀል ድርጅቶች "የፋይናንስ ወይም የቴክኒካል ድጋፎችን በመስጠት የፖለቲካ አድቮኬሲ፣ በመራጮች ትምህርት፣ በምርጫ መታዘብ ወይም ማንኛውም ከምርጫ ጋር የተያያዘ ሥራ ላይ መሰማራት አይችሉም" የሚል ከልካይ ድንጋጌ በረቂቁ ውስጥ ተካትቷል።

ከዚህ በተጨማሪም ማንኛውም አገር በቀል ድርጅት እነዚህን ተግባራት ለማከናወን "ከውጭ የፋይናንስ ምንጭ ገንዘብ ወይም ሃብት መቀበል አይችልም።"

የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያው "ይህ ድንጋጌ 'የፖለቲካ አድቮኬሲ' በሚለው ሐረግ ትርጉም እና አተገባበር ላይ መሠረት ያደረገ የተለየ ሥልጣን ለመንግሥት ሰዎች እየሰጠ ይመስላል" ይላሉ።

'የፖለቲካ አድቮኬሲ' በሚለው ሐረግ የተፈጠረው የሕጉ ለትርጉም መጋለጥ ድንጋጌው "ኢ-ሕገ መንግሥታዊ እና የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶችን የሚጥስ ያደርገዋል" ሲሉ ያክላሉ።

ሌላው "ሕገ መንግሥታዊ ጥሰት"፤ "ኢትዮጵያ ውስጥ በሚኖሩ የውጭ አገር ዜጎች የተመሠረቱ አገር በቀል ድርጅቶች" ከሚለው ክልከላ ሊመጣ እንደሚችል ባለሙያው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ባለሙያው ይህን ሲያብራሩ "መምረጥ እና መመረጥን ሳይጨምር አብዛኞቹ የፖለቲካ መደራጀቶች እና ሃሳብን መግለጽ በሕገ መንግሥቱ፣ በአፍሪካ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መስፈርቶች ለውጭ አገር ዜጎች የተረጋገጡ ናቸው" ይላሉ።

የድርጅቶች ዕድሳት እና ህልውና ማረጋገጥን የሚመለከተው የአዋጁ ክፍል ላይ ደግሞ አዳዲስ ንዑስ አንቀጾች ተካትተዋል።

በባለሥልጣኑ ተመዝግበው የምዝገባ ምስክር ወረቀት የተሰጣቸው ድርጅቶች፣ የምዝገባ ምስክር ወረቀቱ በተሰጣቸው በአራት ዓመት የመጨረሻ አንድ ወር ሲቀረው ጀምሮ ማሳደስ ይጠበቅባቸዋል።

ድርጅቶች በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ካላሳደሱ ጥሪ እንደሚደረግላቸው የሚጠቅሰው ረቂቁ "ጥሪው በተደረገ 30 ቀናት ውስጥ የድርጅቱ ኃላፊ ወይም ሕጋዊ ተወካይ የምዝገባ ምስክር ወረቀት በወቅቱ ያላሳደሰበትን ምክንያት ለባለሥልጣኑ ማስረዳት አለበት" ይላል።

ሆኖም ድርጅቱ "ያላሳደሰበትን በቂ ምክንያት ካላቀረበ ባለሥልጣኑ ድርጅቱ እንዲሰረዝ እና እንዲፈርስ ሊወስን ይችላል" ሲል ረቂቁ ይደነግጋል።

ረቂቅ ማሻሻያው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ድርጅቶች ላይ ምርመራዎች የሚያከናውንበት አካሄድ ላይም ማሻሻያ አድርጓል።

በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ባለሥልጣኑ ምርመራ በሚያከናውንበት ወቅት "ከባድ የሕግ ጥሰት መፈጸሙን ሲያረጋግጥ" እንዲሁም "የድርጅቱ እንቅስቃሴ ማገድ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው" ዋና ዳይሬክተሩ ከሦስት ወር ላልበለጠ ጊዜ የዕገዳ ትዕዛዝ ሊሰጥ እንደሚችል ያትታል።

ማሻሻያ ረቂቁ ይህን ድንጋጌ "ከባድ የሕግ ጥሰት ስለመፈጸማቸው አጠራጣሪ ሁኔታ ሲያጋጥም" እንዲሁም "ድርጅቱ ካልታገደ የማይመለስ ጉዳት ይደርሳል ብሎ ካመነ" በሚሉ ሐረጋት ለውጦታል።

ከዚህ በተጨማሪ ማሻሻያ ረቂቁ የምርመራ ሥራው በሦስት ወር የዕግድ ጊዜ ካልተጠናቀቀ ቦርዱ ለተጨማሪ ሦስት ወራት ሊያራዝመው እንደሚችል ያትታል።

ባለሥልጣኑ የድርጅቶችን የባንክ ሂሳብ "በከፊል ወይም በሙሉ" የማገድ ሥልጣን አለው።

በሥራ ላይ ባለው አዋጅ በዕግዱ ቅር የተሰኙ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቅሬታቸውን ለቦርዱ፤ በቦርዱ ካልተፈታ ደግሞ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማቅርብ ይችሉ ነበር።

በማሻሻያ ረቂቁ ግን "ቦርዱ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ይሆናል" የሚል ድንጋጌ ይዟል።

በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቸ ላይ በባለሥልጣኑ የሚወሰዱ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን የሚዘረዘርው የአዋጁ አንቀጽ ሙሉ በመሉ በአዲስ ከተተኩት የአዋጁ ድንጋጌዎች መካከል አንዱ ነው።

ይህ ድንጋጌ ከ2011 በፊት የነበረውን እና ቀድሞ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ የሚባለውን ተቋም የአስተዳደር ሥልጣን የሚመልስ መሆኑን ባለሙያው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ከባድ የሕግ ጥሰት ስለመፈጸማቸው አጠራጣሪ ሁኔታ ሲያጋጥም" ድርጅቶችን ማገድ የሚፈቅደው ድንጋጌ "የሲቪል ማኅበራትን ለማንበርከክ የፈለገውን እንዲያደርግ የሚፈቅድ ብቻ ሳይሆን በሙስና የተዘፈቁ ተዋናዮች ሲወተውቱት የቆዩት ነገር ነው፤ መንግሥት አንዳንዶቹን ለፖለቲካ ፍጆታ አላግባብ ሊጠቅምባቸው ይችላል፤ ነገር ግን ለሙስና ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል" ሲሉ ባለሙያው ያስረዳሉ።

በማሻሻያ ረቂቁ የተካተተው ድንጋጌ በሥራ ላይ ካለው አዋጅ በተለየ መልኩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ከጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እስከ መሰረዝ የሚያደርሱት ጥፋቶች በዝርዝር ተቀምጠዋል።

በረቂቁ መሠረት ድርጅቶችን ለስረዛ የሚዳርጉ ሰባት "ጥፋቶች" ተዘርዝረዋል።

ከእነዚህ ውስጥ "ሐሰተኛ ሰነድ በማቅረብ ወይም የተሳሳተ መረጃ መስጠት ወይም በማጭበርበር መመዝገብ" አንደኛው ነው።

አንድ ድርጅት "በከፍተኛ ደረጃ የሕዝብ እና የአገር ሰላም ጥቅም ወይም ደኅንነት አደጋ ላይ በሚጥል ሕገ ወጥ ተግባር መፈጸሙ ወይም መሳተፉ ከተረጋገጠ" እንደሚሰረዝ ረቂቁ ያስረዳል።

"በወንጀል ድርጊት የተሰማራን ማንኛውም ሰው ወይም ቡድን በገንዘብ፣ በቁሳቁስ፣ በሃሳብ ወይም በቴክኒክ የሚደግፍ መሆኑ" እንዲሁም "ሽብርተኝነት በገንዘብ መርዳቱ ከተረጋገጠ" ሌሎቹ ድርጅቶችን እንዲሰረዙ የሚያደርጉ ተግባራት ናቸው።

አንድ ድርጅት "በወንጀል የተገኘ ሃብትን ሕጋዊ አስመስሎ ካቀረበ ወይም ከተጠቀመ" በባለሥልጣኑ እንደሚሰረዝ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል።

ከዚህ በተጨማሪ አንድ ድርጅት የስድስት ወር የዕግድ እርምጃ ተወስዶበት ተመሳሳይ እርምጃ የሚያስወስድ ጥፋት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በድጋሚ ከፈጸመ ይሰረዛል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ቀንድ ክልላዊ ተመራማሪ ሐይማኖት አሸናፊ ከአሁኑ ረቂቅ ባሻገር የሕግ ማሻሻያዎች "በኢትዮጵያ የፈላጭ ቆራጭ (authoritarian) ልምምዶችን ሕጋዊ ሊያደርጉ የሚችሉ" መሆናቸውን ትገልጸች።

ከዚህ በተጨማሪም እነዚህ ማሻሻያዎች ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ተስፋ ተጥሎበት ነበረውን የሽግግር ሂደት ወደ ኋላ የሚመልስ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግራለች።

አምነስቲ "የሲቪል ከባቢዎች መዘጋት በኢትዮጵያ ከሰላማዊ ተቃውሞዎች ይልቅ ሁከት እና ብጥብጥ ግዘፍ የሚነሱባቸው የቀድሞ ልምዶች እንዲደገሙ ያደርጋል" የሚል ስጋት እንዳለው ገልጻለች።

ተመራማሪዋ "በሥልጣን ላይ ያለው አስተዳደር የሰዎችን ሰርክ ኑሮ ለመቆጣጠር እና ተቃውሞዎችን ለማስወገድ ሲጥር ከነበረው የቀድሞ ፈላጭ ቆራጭ ልምምዶች ለመማር አለመፈለጉ" ያሳዝናል ስትል አክላለች።

አምነስቲ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና የመብት ተሟጋቾች ረቂቅ ማሻሻያዎቹን "በአደባባይ እንዲያወግዙ እና አሁን በኢትዮጵያ እየታየ ያለው አምባገነናዊ ልምምድ ሕጋዊ እና ተቋማዊ ከመሆኑ በፊት እንዲገታ ያረጋግጡ ዘንድ" ጥሪ አቅርቧል።