ስለ አነጋጋሪው አዋጅ አስተያየት የሰጠችው ጠበቃ ሐሰተኛ መረጃ በማሠራጨት ተከሰሰች

የፎቶው ባለመብት, social media
ባለፈው ሳምንት በቁጥጥር ስር የዋለችው የሕግ ባለሙያ ሰብለ አሰፋ ሐሰተኛ መረጃ በማሠራጨት እንደተከሰሰች ጠበቃዋ ለቢቢሲ ተናገሩ።
የሕግ ባለሙያዋ በወንጀል የተገኘን ንብረት ሕጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን ለመቆጣጠር በፀደቀው ማሻሻያ አዋጅ ዙሪያ በማኅበራዊ የትስስር ገፅ ላይ አስተያየት መስጠቷን ተከትሎ ነበር ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ሰኔ 12/2017 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር የዋለችው።
አርብ ሰኔ 13 ልደታ ፍርድ ቤት 11ኛ መደበኛ ችሎት የቀረበችው የሕግ ባለሞያዋ ሰብለ የዋስትና መብቷ ተክብሮ በ30 ሺህ ብር ዋስ በማግስቱ ቅዳሜ ከእስር ተፈትታለች።
በማሻሻያው በሽፋን ስር ምርመራ የሚያከናውኑ መርማሪዎች ከአቅማቸው በላይ ሆኖ ከግድያ ወንጀል በስተቀር በሚፈፀሟቸው ወንጀሎች እንደማይከሰሱ መደንገጉን ተከትሎ መነጋገሪያ ሆኗል።
ጠበቃዋ በመቶ ሺህዎች ተከታይ ባላቸው እና በስሟ በተከፈቱ የቲክቶክ እና የፌስቡክ ገፆቿ ላይ ስለ ድንጋጌው ሁለት አስተያየቶችን ሰጥታለች።
ይህን ተከትሎ ሐሙስ ሰኔ 12/2017 ከቀኑ 07፡00 አካባቢ በፖሊስ 'እንፈልግሻለን' ተብላ ሜክሲኮ በሚገኘው ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ መታሰሯን ጠበቃዋ አቶ አንዱዓለም በእውቀቱ ለቢቢሲ ተነግረዋል።
በማግስቱ አርብ ሰኔ 13/2017 ዓ.ም ልደት ፍርድ ቤት 11ኛ ምድብ ችሎት የቀረበች ሲሆን፤ የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ሥጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ 1185/2012 አንቀፅ ሁለት፣ ሦስት፣ አምስት እና ሰባትን ተላልፋ ተገኝታለች በሚል ክስ ተመሥርቶባታል።
የወንጀል ዝርዝሩ ተከሳሿ የወንጀል ድርጊት ስለመፈፀሟ አምና የተጠጣሪነት ቃል መስጠቷን የሚያስረዳ ሲሆን፣ ጠበቃዋ ይህን ቃል "በፖሊስ ጫና ስር፤ ጠበቃ እና አማካሪዋ በሌለበት" የተሰጠ በመሆኑ አንቀበለውም ብለዋል።
"[ተከሳሿ] ጥፋተኛ ነኝ ብላ አታምንም" ሲሉ የደንበኛቸውን አቋም የተናገሩት ጠበቃው፤ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እና በተከሰሰችበት አዋጅ የማያስከሰስ ተብሎ የተቀመጡ ሁኔታዎች ጥበቃ እንደሚሰጧት ገልፀዋል።
"አንድ ሰው ሙያዊ ትንታኔ በሰጠበት ጉዳይ ላይ ሊጠየቅ አይገባም፤ አዋጁም ላይ አለ። . . . አንድ አስተያየት ሐሰተኛ እና የጥላቻ ንግግር ተብሎ የማይወሰደው በዜና ትንታኔ፣ በሙያ፣ በፖለቲካ ትችት ሲቀርብ [ነው]" በማለት ስለ ክሱ አብራርተዋል።
"ሁላችንም አዋጅ ተመልክተን የየራሳችንን አስተያየት እንይዛለን። እንደ ሕግ ባለሙያ በተናገርን ቁጥር መንግሥትን ካልጣመው ጥፋተኛ ናችሁ ልንባል ነው ማለት ነው" በማለት ተከሳሷ የራሷን አስተያት ማንፀባረቋን ጠቁመዋል።
"ትንታኔ ነው የምትሠራው። ትንታኔ ላይ ሰው ተሳሳተ ተብሎ ጥላቻ ተብሎ አይከሰስም። ፍላጎቱ መታየት አለበት። በየቀኑ የምታደርገው ነው" ሲሉ ክሱን አጣጥለዋል።
ክሱ "ውድቅ መረግ ያለበት ነው" ያሉት አቶ አንዱአለም፤ ክሱ እንዲቋረጥ አቤቱታ እንደሚያቀርቡ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጠበቃው በአወዛጋቢው አዋጅ ዙሪያ በግል ከተከሳሿ የተለየ ሀሳብ እንዳላቸው ጠቁመው፤ አስተያየቱ "የሚያሳስር ቀርቶ የሚያስወቅስም፤ የሚያነጋግርም አይደለም" ብለዋል።
የክሱን አንደምታ በሚመለከት በቢቢሲ የተጠየቁት አቶ አንዱአለም፤ "በጣም አሳሳቢ" እና "መጥፎ አዝማሚያ" ብለውታል።
"መንግሥትን በሚረዳ መልኩ አልተነተነችም ማለት የሚያሳስር ከሆነ በጣም አሳሳቢ ነው። መጥፎ አዝማሚያም ነው" ሲሉ አብራርተዋል።
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ለመስማት ለሐምሌ 4/2017 ዓ.ም. ቀተሮ ሰጥቷል።
ጠበቃ ሰብለ አሰፋ የተከሰሰችበት አዋጅ የወንጀል ተጠያቂነትን ሲገልፅ "ወንጀሉ የተፈጸመው ከአምስት ሺህ በላይ ተከታይ ባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ከሆነ . . . ቅጣቱ እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት እና ከብር 100 ሺህ ያልበለጠ መቀጮ ይሆናል" ይላል፡፡
ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው በሽፋን ሥር ምርመራ የሚያከናውን ሰው "ከአቅሙ በላይ" እና "ከፈቃዱ ውጪ" ለሚፈጽመው ከግድያ ውጪ የሆነ ወንጀል ክስ እንዳያቀርብበት የሚያደርግ ነው።
ይህ የአዋጁ አካል ከተወሰኑ የምክር ቤቱ አባላት ተቃውሞ እና ጥያቄ የቀረበበት ሲሆን፣ የመብት ተቆርቆሪዎችም ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት በር ይከፍታል በሚል ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።















