በምያንማር ታጣቂዎች ተይዘው የነበሩ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ወደ አገር ተመለሱ

የፎቶው ባለመብት, THAI NEWS PIX
ከምያንማር የሳይበር ወንጀል ካምፖች አምልጠው በታጣቂዎች እጅ ከወደቁት 751 ኢትዮጵያውያን መካከል የሆኑት የመጨረሻዎቹ 49 ተጎጂዎች ትናንት ወደ አገር መግባታቸውን የወላጆች ኮሚቴ አስተባባሪ እና በታይላንድ የሚገኙ ምንጮች ተናገሩ።
ከወንጀል ካምፖቹ መውጣት ያልቻሉ 42 ተጎጂዎች ግን አሁንም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሲሆን "ከፎቅ ላይ ራሱን ወረወረ" የተባለ አንድ ኢትዮጵያዊ ሕይወቱ እንዳለፈም ተገልጿል።
ወደ አገራቸው ተመልሰው የተጠናቀቁት ኢትዮጵያውያን ከየካቲት ወር አንስቶ "ዴሞክራቲክ ካረን ቤነቮለንት አርሚ" (DKBA) እና "ቦርደር ጋርድ ፎርስ" (BGF) በተባሉት የምያንማር አማጺያን እጅ ነበሩ።
ኢትዮጵያውያኑ ከሌሎች አገራት ዜጎች ጋር በመሆን ታጣቂዎቹ እጅ የገቡት በግዳጅ ሠራተኝነት ተይዘው ከነበሩባቸው የሳይበር ወንጀል ካምፖች ካመለጡ በኋላ ነበር።
ኢትዮጵያውያኑ ወደ እነዚህ ካምፖች የገቡት ጥሩ ገንዘብ እንደሚያገኙ ተነግሯቸው ወደ ታይላንድ ከተወሰዱ በኋላ በምያንማር ለሚገኙ የወንጀል ቡድኖች በመሸጣቸው ነው።
በካምፖቹ ውስጥ የማጭበርበር ወንጀል እንዲፈጽሙ ሲገደዱ የነበረ ሲሆን የተለያዩ የስቅይት ድርጊቶች ተፈጽመውባቸዋል።
በታጣቂዎች እጅ የነበሩትን ተጎጂዎች ለማስወጣት በጃፓን ቶኪዮ እና በሕንድ ኒው ዴልሂ በሚገኙ ኤምባሲዎች እንዲሁም በአጎራባቿ አገር ታይላንድ የሚገኙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በኅብረት ሲሰሩ ነበር።
በሁለቱ ታጣቂዎች እጅ የነበሩትን 751 ኢትዮጵያውያን ወደ አገር መመለስ የተጀመረው ሚያዝያ ላይ ነበር።
ባለፈው ሁለት ወር ገደማ ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያውያኑ በተለያዩ ቡድኖች እየተከፈሉ ከምያንማር ወደ ታይላድ ከተሻገሩ በኋላ፤ ወደ አዲስ አበባ እንዲበሩ መደረጉን የተጎጂዎች ቤተሰቦች ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አበበች ሲመል ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የመጨረሻው ቡድን ውስጥ የነበሩት 49 ኢትዮጵያውያን ትናንት ማክሰኞ ሰኔ 17/2017 ዓ.ም. ንጋት ላይ አዲስ አበባ መድረሳቸውንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያኑን ወደ አገራቸው ለመመለስ ለተወሰኑት የትኬት ወጪን መሸፈንን ጨምሮ የተለያዩ እገዛ ካደረጉ በታይላንድ የሚገኙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ የአንዱ አመራር የሆኑ ምንጭ፤ "ዛሬ ጠዋት የመጨረሻዎቹን ኢትዮጵያውያን ወደ ቤታቸው ልከናል። ይህ ታሪክ የሚቀጥል ነው፤ አንዱ ምዕራፍ ግን ተጠናቋል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እነዚህ ተጎጂዎች በሙሉ ወደ አገራቸው ቢመለሱም አሁንም ድረስ ከወንጀል ቡድኖቹ ማምለጥ ያልቻሉ 42 ኢትዮጵያውያን በሦስት የተለያዩ ካምፖች ውስጥ እንደሚገኙ ወ/ሮ አበበች ገልጸዋል።
እነዚህ ተጎጂዎች እንደ ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ለማምለጥ ሲሞክሩ የተያዙ እንደሆኑም አክለዋል።
"በጣም አስቸጋሪ፣አስከፊ የሚባሉት ካምፓኒዎች እጅ ነው ያሉት።ይሰቀላሉ፣ግድግዳ ላይ ቀኝ እና ግራ እጃቸው፤ምዕራብ እና ምሥራቅ ተወጥሮ ከሁለት ሰዓት በላይ ይታሰራሉ። በተለይ አስራ አራቱ ያሉበት [ካምፕ]፤ ጫማቸውን አስወልቀው፤ ኮረኮንች ላይ አስኪደዋቸው 14ቱም እግራቸው ቆሳስሏል" ሲሉ ኢትዮጵያውያኑ ያሉበትን ሁኔታ አስረድተዋል።
"የእነዚህን ልጆች ሕይወት ካጣን፤ለቤተሰብም ይህንን፣ ለሚያውቅ ማኅበረሰብ ጠቅላላ ከባድ ሐዘን ነው የሚሆነው" የሚሉት ወ/ሮ አበበች፤ ባለፈው ወር ግንቦት መጨረሻ ላይ በሌላ ካምፕ ውስጥ የነበረ ኢትዮጵያዊ ሕይወት ማለፉን ገልጸዋል።
የተጎጂው ሕይወት ማለፉን ያስታወቁት አብረውት የነበሩ ሌሎች ሁለት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሁለቱ ኢትዮጵያውያን የተጎጂው ሕይወት ማለፉን ያወቁት አስከሬኑን ተመልክተው መሆኑን አስረድተዋል።
በካምፑ ውስጥ የያዟቸው ሰዎች "በነገሯቸው መሠረት"፤ "በጭንቀት ራሱን ከሰባተኛ ፎቅ ላይ ወርውሮ ሞተ" ብለው መናገራቸው ገልጸዋል።
ወ/ሮ አበበች፤ "የልጁን ሬሳ ስናይ ከሰባተኛ ፎቅ ወድቅ የሞተ አይመስልም። እንግዲህ ጥቃትም ሊሆን ይችላል። ሲሞት ራሱን አጠፋ ሊሉም ይችላሉ።ምን ማረጋጫ አለ?" ሲሉ ጠይቀዋል።
የሟቹ ቤተሰቦች የአስከሬኑን ፎቶግራፍ ተመልክተው ማንነቱን ማረጋገጣቸውን አክለዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ የሟች ቤተሰብ አባል ሕይወቱ ማለፉን ቢያረጋግጡም በጉዳይ ላይ አስተያየት የመስጠት ፍላጎት እንደሌላቸው ገልጸዋል።
የቤተሰቦች ኮሚቴ ሰብሳቢዋ ወ/ሮ አበበች፤ሕይወቱ ያለፈውን ኢትዮጵያዊ "አስከሬን ለማምጣት ምንም ጥረት አለመደረጉን" ገልጸዋል።
ካምፑ ውስጥ አብረውት የነበሩት ሁለት ኢትዮጵያውያን "አምልጠው መውጣታቸውን" እና "ያሉበት እንደማይታወቅ" አክለዋል።















